በትናንትናው
ዕለት ከአዲስ አበባ 46 ተሳፋሪዎችን ይዞ ወደ ጐንደር በመጓዝ ላይ በነበረው የሰሌዳ ቁጥር 40411 በሆነው ስካይ ባስ፣ ዓባይ በረሃ ሕዳሴ ድልድይ መዳረሻ ሲደርስ መስመሩን ስቶ ገደል በመግባቱ፣ 43 ሰዎች መሞታቸውን በስፍራው የተገኘው የሪፖርተር ዘጋቢ ለማወቅ ችሏል፡፡
አውቶቡሱ
ከሾፌሩ፣ ከረዳቱና ከአንዲት አስተናጋጅ ውጭ 46 ተሳፋሪዎች ይዞ በመጓዝ ላይ እያለ ምክንያቱ ባልታወቀበት ሁኔታ ወደ ሕዳሴ ድልድይ መቃረቡን የሚያመለክቱ አንፀባራቂ ምልክቶችን ጥሶ በግምት ከ80 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው ገደል ውስጥ ገብቷል፡፡
አውቶቡሱ
ገደል መግባቱን ተከትሎ በተሰማው የፍንዳታ ድምፅ ምክንያት የሕዳሴውን ድልድይ የሚጠብቁ ታጣቂዎች ፈጥነው ቢደርሱም፣ ተሽከርካሪው በእሳት በመያያዙ በሕይወት የተረፉትን ለመርዳት መቸገራቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
አደጋው
ከደረሰ በኋላ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችና ከጐንደርና ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ጐንደርና ባህር ዳር በመጓዝ ላይ ያሉ መንገደኞች ሁሉ ባደረጉት መረባረብ፣ በእሳት የተቃጠሉና በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰባት ሰዎች ለማውጣት መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከአደጋው
ከተረፉት ስድስት ተጓዦች መካከል አንደኛው ከአውስትራሊያ መጥቶ የጥምቀትን በዓል ለማክበር ወደ ጐንደር እየተጓዘ እንደነበር፣ “ወንድሜን ጥሩልኝ ስልክ ደውሉልኝ” ብሎ በመናገር ላይ እያለ ሕይወቱ ማለፉን ዘጋቢው ማየቱን ተናግሯል፡፡ አውቶቡሱ ውስጡ ሙሉ በሙሉ በእሳት በመያያዙ አደጋው የደረሰባቸውና ሕይወታቸው ያለፈው ተጓዦች አስከሬንም ሳይቃጠል እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
ከባድ
አደጋ የደረሰባቸውና በሕይወት የተረፉት አንዲት ሴትና አምስት ወንዶች፣ በአካባቢው በተገኙ የቀይ መስቀል ሠራተኞች የመጀመርያ ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ሕክምና ቦታ መወሰዳቸው ታውቋል፡፡ በግምት ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ የተከሰተው አደጋ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ እንደቆየ ታውቋል፡፡
አዲስ
አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የስካይ ባስ አክሲዮን ማኅበር ኃላፊዎችን አነጋግረናቸው፣ በደረሰው አደጋ እጅግ በጣም መደንገጣቸውንና ስለ አደጋው የሚያጣራ የቴክኒክ ቡድን ወደ ስፍራው መላካቸውን ተናግረዋል፡፡
አውቶቡሱ
አንድ ጊዜ ተጉዞ ሲመለስ ሙሉ ምርመራ እንደሚደረግለት፣ መስተዋቶቹ አደጋ እንኳን ቢከሰት በቀላሉ የሚሰበሩ፣ አላስፈላጊ የሆነ ነገር ቢገጥም በሚል ደግሞ በእያንዳንዱ ተሳፋሪ መስታወት አቅራቢያ መስተዋት መስበሪያ መዶሻ እንደሚሰቀል ኃላፊዎቹ ተናግረው፣ አደጋው በምን ሁኔታና ምክንያት እንደደረሰ መናገር የሚችሉት የቴክኒክ ቡድኑ ለሚመለከተው አካል ካሳወቀ በኋላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ስካይ
ባስ ከሦስት ዓመታት በፊት ከሦስት ሺሕ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመ የግል ማኅበር ነው፡፡ አሁን ከተገለበጠው አውቶቡስ ጋር 14 አውቶቡሶች ሲኖሩት ከሁለቱ በስተቀር 12ቱ መፀዳጃ ቤት፣ የአየር መቅዘፊያ ባግና የተለያዩ መስተንግዶዎች አሏቸው፡፡ ሁለቱ አውቶቡሶችም መኝታ ክፍሎች አሏቸው፡፡ እያንዳንዳቸው አውቶቡሶች በ3.5 ሚሊዮን ብር የተገዙ ሲሆን፣ በቀጥታ ከፋብሪካው ተገዝተው የመጡ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment