ለመጀመርያ
ጊዜ በአፍሪካ አኅጉር በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ውድድር በርካታ ሰዎችን ደቡብ አፍሪካ ለመላክ የገባውን ቃል ባለመፈጸም በወንጀል የተከሰሰው፣ የአስካሉካን ትሬዲንግ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ግርማይ ገብረ ሚካኤል፣ ባለፈው ረቡዕ በተከሰሰበት የከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ልደታ ምድብ ችሎት በመቅረብ፣ በዋስትና ወይም በአጃቢ ፖሊስ ወጥቶ መረጃ ለማሰባሰብ ቢያመለክትም በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደረገ፡፡ ፍርድ ቤቱ ማመልከቻውን ውድቅ ያደረገው ግለሰቡ ወደ ጀርመን ኮብልሎ በጀርመን መንግሥትና በኢንተርፖል አማካኝነት ተይዞ መምጣቱ እምነት እንዳይጣልበት የሚያደርግ በመሆኑ ነው፡፡
ከቀኑ
በ9፡00 ሰዓት አካባቢ የጀመረው ችሎት በአብዛኛው በተጐጂ ወገኖች በመሞላቱ ሌሎች በርካታ የግል ተበዳዮች ችሎቱን ከደጅ ሆነው ለመከታተ ግድ ሆኖባቸው ነበር፡፡
ችሎቱ
የተቀጠረው የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ለመስማት ቢሆንም፣ ቀኑ በመምሸቱ ከአሥራ አንዱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የቀረቡትን አሥር ምስክሮች መስማት እንደማይችል የገለጹት የችሎቱ ዳኛ፣ አሥራ አንዱንም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ለመስማት መዝገቡን ለህዳር 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ቀጥረውታል፡፡
ሆኖም
ግን ከቀረቡት አሥር ምስክሮች ውስጥ አራቱ ከተለያዩ የደብብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዞኖች የመጡ በመሆናቸው፣ ችሎቱ መዝገቡን መቅጠሩ ለወጪ እንደሚዳርጋቸው በመግለጻቸውና ዳኛው ቅር ለተሰኙት ምስክሮች የሁለት ቀን ተኩል የውሎ አበል፣ ደረሰኝ ካቀረቡም የትራንስፖርት ወጪያቸው እንዲከፈላቸው አዘዋል፡፡
ችሎቱ
ከመጠናቀቁ በፊት ከሦስቱ የአቶ ግርማይ ጠበቆች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ሞላልኝ መለስ፣ በምስክሮቹ ስድብና የኃይል ጥቃት ዛቻ እየተደረገባቸው በመሆኑ ሥራቸውን ለመሥራት አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡
ዳኛውም
በችሎቱ ውስጥ የሚገኙትን የግል ተበዳዮችና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጉዳዩ በሕግ እጅ ስለሚገኝ በኃይል ሊመጣ የሚችል ነገር ባለመኖሩ፣ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በትዕግስት እንዲጠባበቁ ካሳሰቡ በኋላ፣ አንድ ምስክር ጠበቆቹ ስማቸውን እያጠፉት መሆኑን በመግለጽ ችግር ካለባቸው ሊከሷቸው እንደሚችሉ ሲገልጹ የተፈጠረውን ጫጫታ በማስቆም ችሎቱን አጠናቀዋል፡፡
የፌዴራል
ዓቃቤ ሕግ ነሐሴ 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ አቶ ግርማይ ሰባት የማጭበርበር ክሶችና አንድ ከንግድ ፈቃድ ውጭ ሰዎችን ወደ ውጭ አገር በመላክ ሥራ ላይ መሰማራት ክስ ቀርቦበታል፡፡
ፍርድ
ቤቱ ነሐሴ 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ክሶቹን የሰማ ሲሆን፣ የአቶ ግርማይ ጠበቆች በቀረበው ክስ ላይ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ የቀረቡት ሰባት ክሶች ከተበዳዮች ስም በስተቀር አንድ ዓይነት በመሆናቸው በአንድ ክስ ተጠቃለው መቅረብ እንደነበረባቸው ገልጸው፣ የክሶቹ መነጣጠል የመከላከል መብታቸውን እንደሚያጣብባቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚህም
በተጨማሪ ወንጀሉ እንዴት እንደተፈጸመ እንደማያሳይ ገልጸው ተበዳዮቹ የትና መቼ እንደተታለሉ በግልጽ እንደማያሳይ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ስምንተኛው ክስ የቀረበው አቶ በግርማይ ላይ ሳይሆን ድርጅታቸው ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ድርጅቱ ቀደም ሲል የ30,000 ብር ቅጣት ስለተላለፈበት ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው አመልክተዋል፡፡
ዓቃቤ
ሕግ ክሱን ያቀረበው በሰባት የግል ተበዳዮች ላይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ተበዳይ ነን የሚሉ ሰዎች 900 ሰዎች በመሆናቸው "ዓቃቤ ሕግ በሁሉም ላይ የተለያዩ ክሶች ሊያቀርብ ነው ወይ?" በማለትም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ
ሕግ ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ የግል ተበዳዮች 900 ሳይሆኑ፣ ቁጥራቸው 1,200 መሆናቸውን ገልጸው፣ አስፈላጊ ከሆነ በ1,200 ክሶች የማያቀርቡበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ምክንያት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
ፍርድ
ቤቱም በጠበቆቹ የቀረቡትን መቃወሚያዎች በማለፍ አቶ ግርማይን የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ጠይቋቸው፣ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውንና ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የተከሳሹ
ጠበቆች በመቀጠል አቶ ግርማይ ከዚህ በፊት ከአገር የወጣው ተበዳዮች ነን ባዮችን በመፍራት የራሱንና የቤተሰቡ ሕይወት ለማዳን መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ከአገር እንዳይወጡ ማገድ ስለሚቻል የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ
ሕግ በበኩሉ አቶ ግርማይ የተያዘው በኢትዮጵያ ፖሊስና ኢንተርፖል ትብብር መሆኑንና ከአገር የወጣውም በሕጋዊ መንገድ እዳልነበር በማስታወስ የዋስትና መብቱ እንዲከለከል ጠይቋል፡፡
ፍርድ
ቤቱም የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ እንደገለጸው፣ ምንም እንኳ አቶ ግርማይ የተከሰሰበት ወንጀል የዋስትና መብት የማያስነፍግ ቢሆንም፣ ተከሳሹ ከአገር በሕገወጥ መንገድ የመውጣት ታሪክ ስላለው ሊታመን ስለማይችል ተበዳዮችን ሸሽቶ ነው ከአገር የወጣው የሚለውን ምክንያት አሳማኝ ሆኖ ስላላገኘው የዋስትና መብቱን ነፍጐታል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com
http://www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment