Sunday, October 23, 2011

“እምጵ”…የጋዳፊ ጓደኞች ለጋዳፊ


እሸቴ በቀለ

ጋዳፊ ተሸነፉ፡፡ሽሽትም ኣላዋጣቸውም፡፡መጨረሻቸው እርሳቸው እንዳሉት መስዋዕትነት አልሆነም፡፡እጅጉን ባጥላሏቸው የሃገራቸው ሰዎች እጅ ተማረኩ፡፡በወርቅ የተለበጠች ሽጉጣቸው እንኳ ምንም አልፈየደችም፡፡ሰውየው በስተመጨረሻ ግን ልመናን ተማሩ፡፡"አትተኩስ…አትተኩስ" ልመናቸው አልተሳካም፡፡የለመኑትም አልሰማቸውም፡፡ተተከሰ፡ቆሰሉ፤አቃሰቱ ሞታቸውም እውነት ሆነ፡፡
የሞኣመር ጋዳፊ ህልፈተ ህይወት ለሊቢያውያን ብቻ ሳይሆን ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ሃገራት ጭምር አንዳች ትርጉም ሰጥቶ አልፏል፡፡የሰውየው የአገዛዝ ስርዓት፤ለአፍሪካ ኢኮኖሚም ያበረከቱት ጥቂት አስተዋፅኦ ፤እጅጉን ሲያወዛግብ የነበረው ህልማቸው የሚረሱ አይሆኑም፡፡የሙአመር ጋዳፊ ሞት ከሃዘን ይልቅ እፎይታን ፈጥሯል፡፡
በርካታ አፍሪካውያን የሙኣመር ጋዳፊ ሞት የፈጠረባቸውን ደስታ ፌስቡክ እና ተዊተርን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረ ገፆች እየገለፁ ነው፡፡የማህበራዊ ድረ ገፆቹ አፍሪካውያን ግን በዚህ ብቻ አላቆሙም፡፡ማነው ባለሳምንት…የተባለ ይመስል በስልጣን ላይ የሸመገሉ መሪዎችን እየጠቆሙ ናቸው፡፡በኬንያ የሚገኘው የአሜሪካን ድምፅ ጋዜጠኛ ጋቤ ጆስሎው የአፍሪካውያኑ እጆች ወደ ዩጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የዙምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ ተቀስረዋል ይላል፡፡ የሙኣመር ጋዳፊ አሟሟት በመንበረ ስልጣናቸው ለዘላለም መቆየት የሚፈልጉት የአፍሪካ መሪዎች ማሳያ እንደሆነ የምትናገረው ናይጄሪያዊቷ ሜሪ ኤን ከዚህም አሁን በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎች የሚማሩት ነገር ሊኖር እንደሚገባ ትናገራለች፡፡የህዝብን ሃብት እና ንብረት ለግል እና ቤተሰባቸው ከማግበስበስ ይልቅ ቆም ብለው የሚያስቡበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነም ታምናለች፡፡
የዙምባብዌው ገዢ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍ በጋዳፊ ሞት የተሰማውን ሃዘን ለመግለፅ ከንፈር በመምጠጥ የቀደመው አልነበረም፡፡እንዲያውም ጋዳፊን ከሞት ለመታደግ የአፍሪካ ህብረት መስራት እንደነበረበት ለአሜሪካን ድምፅ ተናግረዋል፡፡የኡጋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ፍሬድ ኦፖሎት በመንግስታቸው ስም በጋዳፊ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል፡፡እንደ ኦፖሎት ገለፃ ጋዳፊ በህይወት ዘመናቸው ባቀነቀኑት የፓን አፍሪካ ፍልስፍና እና በአፍሪካ ህብረት  ለተጫወቱት ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡እንደ ኦፖሎት እምነት በተለያዩ ሃገሮች የነበሯቸው ኢንቨስትመንቶች እና ለአንዲት አፍሪካ መዋሃድ እና መጠናከር ያደረጉት ትግል ለዘላለም እዲታወሱ ያደርጓቸዋል፡፡ የጋዳፊ መንግስት ከኡጋንዳ ወዳጆች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን በሀገሪቱ የ375 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ነበራቸው፡፡
የጋዳፊ እንቁላል…ካርቱም 
ሙኣመር ጋዳፊ በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ ሀገሮች የሆቴል ኢንቨስትመንት ነበራቸው፡፡ከእነዚህም መካከል በሱዳን ዋና ከተማ በእንቁላል ቅርፅ የተገነባው ሆቴል ይጠቀሳል፡፡ሆቴሉ ‘’የጋደፊ እንቁላል’’ በሚል ቅፅል ስም ይጠራል፡፡በኬንያ እና ሩዋንዳም ቅንጡ ሆቴሎችን አስገንብተው ነበር፡፡
በዋሽንግተን የአትላንቲክ ካውንስልየአፍሪካ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፒተር ፋም ሙኣመር ጋዳፊ ከወደቁ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ኢንቨስትመንቶቻቸው አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ተናግረው ነበር፡፡እንደርሳቸው አባባል ሙኣመር ለ42 አመታት የረሱትን የሊቢያ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት እና በጦርነቱ የደረሱ ውድመቶችን ለማስተካከል ሊቢያ ከነዳጅ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ በሃገር ውስጥ ግንባታ ማዋል ትጀምራለች፡፡ለዚህም በውጭ ሀገራት የሚገኙት እነዚህ የሊቢያ ሃብቶች በገንዘብ ምንጭነት እንዲያገለግሉ ይፈለጋል፡፡ይህም ማለት ሊሸጡ ይችላሉ፡፡እንደ ፋም አባባል የአሁኑ የሊቢያ አስተዳደር በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት እንደ ሙኣመር ጋዳፊ ኢንቨስት እንዲያደርግ መጠበቅ ሞኝነት ይሆናል፡፡
ሊቢያ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር የሚኖራት ግንኙነት በራሱ ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ይሆናል፡፡የአፍሪካ ህብረት እና በርካታ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች በሊቢያ አብዮት ወቅት ከሊቢያ ህዝብ ይልቅ ሙኣመር ጋዳፊ መወገናቸው መፃኢ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ የሚያጠላው ጥላ ይኖራል፡፡
አንዲት አፍሪካን የመመስረት በዚያች አፍሪካም የመንገስ ሃሳባቸው ባይሳካም ሙአመር ጋዳፊ በአፍሪካ ህብርት ተደማጭ ነበሩ፡፡የተዋሃደች አፍሪካ ሃሳባቸውም በርካታ ተከታዮችን አፍርቶላቸው ነበር፡፡ አሁን ወደ ስልጣን የመጣው የሽግግር መንግስት በአንፃሩ  በአፍሪካ ህብረትም ሆነ አለም አቀፉ ማህበረሰብ  ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ ወስዶበታል፡፡የሽግግር መንግስቱ ታግቶ የነበረው በአፍሪካ ህብረት የሊቢያ መቀመጫ የተፈቀደለት የሙኣመር ጋዳፊ ሞት እርግጥ መሆኑን ካወቀ በኋላ ነበር፡፡ የአፍሪካ ህብረት ለሽግግር መንግስቱ እውቅና የሰጠው ባለፈው ወር ሲሆን አዲሱን ሰንደቅ አላማ ያውለበለበው ደግሞ ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡   

No comments:

Post a Comment