በእሸቴ
በቀለ
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መንግስቱ ሃይለማርያም መፅሃፍ ለህትመት በቃ፡፡በዙምባብዌ በስደት ላይ የሚገኙት የቀድሞው አብዮታዊ መሪ መፅሃፍ የመጀመሪያ ቅፅ ሲሆን 514 ገፆች አሉት፡፡በጸሃይ አሳታሚ አማካኝነት በያዝንው አመት ወርሃ ጥቅምት የታተመው ይህ መፅሃፍ ትግላችን፡የኢትዮጵያ ህዝብ አብታዊ የትግል ታሪክ የሚል ርዕስ አለው፡፡ዋጋውም 39.95 የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡በመፅሃፍ መግቢያ ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት ኮሎኔሉ የኢትዮጵያን አብዮት ከመነሾው እስከ አወዳደቁ ለመዳደሰስ ባደረጉት ጥረት መፅሃፍን በሶስት ቅፅ ለማሳተም መገደዳቸውን ያስረዳሉ፡፡ የታሪክ ፀሃፊነታቸው ከቀድሞው ፖለቲካዊ ማንነታቸው ጋር እንዳይቀላቀልባቸው የሰጉት መንግስቱ በመግቢያው “በአብዮት የትግል ጎራ ወይም አሰላለፍ ላይ ብቻ በማተኮር ፤በብቀላ የአጥቂነት ወይም የተከላካይነት ስሜት አጥቅቶኝ በማጋነን ወይም በማቃለል ታሪኩን ላለማዛባት በተቻለኝ መጠን ከራሴ ጋር ታግያለሁ፤ከህሊናዬም ጋር ተሟግቻለሁ፡፡” ይላሉ፡፡
ካሁን
ቀደም ከገነት አየለ ጋር በሁለት ቅፆ ች ባደረጉት
ቃለምልልስ ከፍተኛ መነጋገሪያ የነበሩት የቀድሞው “ጓድ”አሁን የዚምባብዌ ጥገኛ ናቸው፡፡መንግስቱ እስካሁን በግልፅ መልስ ላልተገኘላቸው የነ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ፤አማን አንዶም፤ተፈሪ በንቲ፤በዓሉ ግርማ እና ሌሎች በርካታ ፖለቲካዊ ግድያዎች እርሳቸው ተሳትፎ እንዳልነበራቸው በገነት አየለ መፅሃፍ የተናገሩ ሲሆን በአሁኑ የግል መፅሃፋቸው የተሻለ መረጃ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ከምድራዊ ህይወት ማምሻቸው ላይ የሚገኙት መንግስቱ በሌሉበት ከሌሎች የደርግ ባለስልጣናት ጋር ተከሰው በኢትዮጵያ በጥብቅ ቢፈለጉም ወደ ስምንት ሺህ በሚጠጋ ገፅ ማስረጃ የተበየነባቸው ውሳኔ እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በሞትና በዕድሜ ልክ እስር እንዲቀጡ ከተወሰነባቸው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል 16ቱ ተፈተዋል፡፡የደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሻምበል ፍቅረ
ሥላሴ ወግደረስ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው፣ ኮሎኔል እንዳለ ተሰማ፣ ሜጀር ጀነራል ውብሸት ደሴ፣ ሌተና ኮሎኔል ናደው ዘካሪያስ፣ መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ፣ መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣ ሻለቃ ደጀኔ ወንድማገኘሁ፣ አቶ እሸቱ ሸንቁጤ፣ አቶ ልሳኑ ሞላ፣ ብርጋዴር ጄነራል ለገሰ በላይነህ፣ አቶ ገስግስ ገብረ መስቀል፣ አቶ አበበ እሸቱ፣ አቶ በሪሁን ማሞና መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ ቤተሰባቸውን የተቀላቀሉ ሲሆን ቀሪዎቹም ባለሥልጣናት 20 ዓመት ሲሞላቸው ጊዜያቸውን ጠብቀው ይለቀቃሉ ተብሏል፡፡ የቀድሞውን“ጓድ” በጥገኝነት ያስጠለሉት የዙምባቤው ሮበርት ሙጋቤ የቀድሞ ወዳጃቸውን አሳልፈው የመስጠት ሃሳብ ያላቸው አይመስልም፡፡
ዛሬም
ድረስ በሃራሬ አቅራቢያ ገንሂል በተባለ መንደር የሚኖርት መንግስቱ ከአስራስድስት አመታት በፊት ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ውባንቺ ቢሻው ጋር በመኖሪያ መንደራቸው አቅራቢያ የእግር ጉዞ በማድረግ ላይ ሳሉ በሁለት ኤርትራውያን የመግደል ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር፡፡ሆኖም ከጥቃቱ እርሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ካለጉዳት ማምለጥ ችለዋል፡፡
የ17ቱን የስልጣን ዘመናቸውን አስመለክቶ በርካታ የታሪክ ፀሃፊዎች በተለይም ደግሞ የጦሩ አመራር አባላት ባለፉት ጥቂት አመታት ሃገሪቱ ያለፈችበትን የታሪክ ውጥንቅጥ እና የደም መፋሰስ የሚዳስሱ መፃህፍት ለንባብ ያበቁ ሲሆን አብዛኞቹ ደፍረው ሃላፊነቱን እና ተጠያቂነቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ሆነው አልታዩም፡፡
ኮሎኔል
መንግስቱ ሃይለማሪያም አሁን ለህትመት ባበቁት መፅሃፋቸው በማርክሲዝም ሌኒንዝም ፍልስፍና ፤በስልጣን ሽኩቻ እና ሌሎች ግልፅ ባልሆኑ ምክንያቶች(ይህ ግለሰባዊ ጥላቻ እና በእርሳቸው ዘንድ ለመወደድ ይደረጉ የነበሩ ፉክክሮችን ይጨምራል) ከተፈፀሙ ግድያዎች ጀርባ ያሉ ሚስጥሮችን የምናነብበት ይሆና ብዬ አስባለሁ፡፡መንግስቱ በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ያቀነቀኑትን አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት አጀማመር እና መጨረሻ፤ተስፋ እና ፈተናቸውን ስኬት እና ስህተታቸውን ለመመልከትም ያስችለን ይሆናል፡፡
No comments:
Post a Comment