Wednesday, October 8, 2014

ዋሊያዎቹ ቅዳሜ ማሊን ያስተናግዳሉ


ብዙ ድካምና ጉልበት ብቻ ሳይሆን፣ ከውጤቱ አንፃር ብዙ ገንዘብም እየፈሰሰበት የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚፈለገውን ነጥብ ማስገኘት ሳይችል ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡

ቡድኑ የምድቡን ሦስተኛ ጨዋታ ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የማሊ አቻውን ያስተናግዳል፡፡ የማሊ ቡድን ከነገ በስቲያ ዓርብ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በሜዳቸው በአልጄሪያ፣ ከሜዳቸው ውጪ ደግሞ በማላዊ ሁለት ሽንፈቶችን ያስተናገዱት የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ፣ ለቅዳሜው ጨዋታ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ 27 ተጨዋቾችን ይዘው በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ የሚቀንሷቸውን ተጨዋቾች አስመልክቶ አሠልጣኙም ሆነ ፌዴሬሽኑ ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ግን ደግሞ የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ከአምስት ቀን በኋላ ረቡዕ ጥቅምት 5 ቀን ስለሚሆን በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ አሠልጣኙ የመጨረሻዎቹን ተጨዋቾች ለፌዴሬሽኑ እንዲያሳውቁ በፌዴሬሽኑ በኩል ጥያቄ መቅረቡ እንደማይቀር የሚገልጹ አሉ፡፡


አሠልጣኝ ማሪያኖ ቀደም ሲል ከመረጧቸው ተጨዋቾ በተጨማሪ በግብፅ የሚጫወቱት ሽመልስ በቀለና ኡመድ ኡክሪ፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደ፣ በአውሮፓ ከሚጫወቱት ደግሞ የሱፍ ሳላህ፣ አሚን አስካርና ዋሊድ አታ ዋሊያዎቹን የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ የኢትዮጵያ ቡናው ዴቪድ በሻህና የደደቢቱ ሔኖክ ካሳሁን በተመሳሳይ በአዲስ መልክ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴሬሽን ምንጮች አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶና የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ በቡድኑ ውጤት ዙሪያ መግባባት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡

አሠልጣኙ በበኩላቸው፣ ከደጋፊውም ሆነ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አካላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች የሰላ ትችት እየሰነዘሩ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ አሠልጣኙ የመጨረሻዎቹን ተጨዋቾች ለማሳወቅ ያልቻሉበት ምክንያት ይኼው ጉዳይ ሳይሆን እንደማይቀር ጭምር ያስረዳሉ፡፡

እንደምንጮቹ ከሆነ፣ ቡድኑ ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተጫውቶ 3 ለ2 ተሸንፎ መምጣቱ በመንተራስ የፌዴሬሽን ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አሠልጣኙን ለግምገማ ይጠራል፡፡ በግምገማው ወቅት አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ሒደቱ ትክክል ነው ብለው ቢያምኑም፣ ግን ደግሞ የአልጄሪያውን ጨዋታ ሳይገመገም ለማላዊው ጨዋታ እንገምገም ማለታቸውን ነቅፈዋል፡፡

በዚህ ያላበቁት አሠልጣኙ፣ ዋሊያዎቹን ተረክበው በሐዋሳ ሲያዘጋጁ በቆዩባቸው ሳምንታት እነዚሁ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ስለ ቡድኑ ሳይጠይቋቸውና ሳይነጋገሩ መቆየታቸውን ገልጸው፣ ለአገሪቱ የእግር ኳስ ስፖርት የምናስብ ከሆነ መላ አገሪቱ ያሉ ታዳጊዎች በአግባቡና በዕቅድ ተመልምለው በእነዚያ ላይ አብረው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን መናገራቸውንም ምንጮች ተናግረዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment