Saturday, August 2, 2014

ከደመወዝ ጭማሪው በፊትም ሆነ በኋላ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ በቀድሞው ዋጋ እንዲሸጡ ታዘዙ

መንግሥት ለመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ከመግለጹ በፊትም ሆነ በኋላ አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖራቸው ዋጋ የጨመሩ አምራቾች፣ ቀድሞ ሲሸጡበት ወደነበረው ዋጋ እንዲመለሱ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ባለፈው ዓርብ ከታሸገ ውኃ፣ ከለስላሳ መጠጥና ከቢራ ፋብሪካዎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እንዳስታወቀው፣ የደመወዝ ጭማሪው ሊደረግ መሆኑ ከመነገሩ በፊትም ሆነ በኋላ የተደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች አግባብነት የሌላቸው በመሆኑ፣ አምራቾች የማምረቻ ዋጋቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡

የዓርቡን ውይይት የመሩት የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ዘለቀ፣ አንዳንድ አምራቾች ያደረጉት ጭማሪ አግባብነት የሌለው ነው፡፡ መንግሥት  ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት አምራቾች ዕርምት እንዲያደርጉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወደሕጋዊ ዕርምጃ የሚገባ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ በንግድ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው በዚሁ ውይይት ላይ በተለይ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል የተባሉ የለስላሳ፣ የታሸገ ውኃና የቢራ ምርቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡


የተለያዩ የታሸጉ መጠጦችን የሚቸረችሩ ድርጅቶች ‹‹የዋጋ ጭማሪ ያደረግነው ከማከፋፈያ ወይም አምራቾቹ ዋጋ ስለጨመሩብን ነው፤›› የሚል ምክንያት እንዳቀረቡ የንግድ ሚኒስቴርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች ሰበሰብን ያሉት መረጃ ይጠቁማል፡፡

በተለይ ወቅታዊ ጭማሪዎችን በተመለከተ አጭር ማብራሪያ የሰጡት የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ኑረዲን መሐመድ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የለስላሳ መጠጦች፣ የታሸጉ ውኃዎችና የቢራ ምርቶች ዋጋ ጨምሯል፡፡ ባለፈው ወር ብቻ የቢራ የችርቻሮ ዋጋ ከአሥር  በመቶ በላይ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡  ይህም የዋጋ ጭማሪ በተለይ ሰኔ ወር ላይ ጎልቶ ታይቶ እስካሁን መቀጠሉንም አመልክተዋል፡፡

አቶ መርከቡም የዋጋ ጭማሪ ያላደረጉ አንዳንድ የታሸጉ ውኃዎች አምራቾች መኖራቸውን፣ እንዲያውም የቀነሱም ቢኖሩም ዋጋ የጨመሩም መኖራቸው በመረጋገጡ ሊስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም አንዳንድ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለቸርቻሪዎች ሲሰጡ ለአንዱ እየሰጡ ለሌላው በመከልከል ያልተገባ ተግባር መፈጸሙንም ጠቅሰዋል፡፡

የውይይቱን ዓላማ ለምን ዋጋ ተጨመረ በመሆኑ በውይይቱ ላይ የነበሩ አምራቾች ተደረገ ለተባለው የዋጋ ጭማሪ ምንክንያታቸውን አቅርበዋል፡፡ ዋጋ ጨምራችኋል የተባሉ አንዳንድ ፋብሪካዎችም ዋጋ ያለመጨመራቸውን ተናግረዋል፡፡ የሞሐ ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ ተወካይ ኩባንያቸው ዋጋ ያልጨመረ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ከሦስት ሳምንት በላይ ፋብሪካዎቻቸው በስኳር እጥረት ሳቢያ አለማምረቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ችግር ሳቢያ ገበያ ውስጥ የነበረውን ምርት ሌሎች ዋጋ ጨምረው እየሸጡት ሊሆን ይችላል እንጂ፣ ድርጅታቸው ዋጋ ያልጨመረ መሆኑን ተናግረው በስኳር እጥረት ለተፈጠረው ችግር መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ተወካይም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፋብሪካቸው የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ ሆኖም የተደረገው የዋጋ ጭማሪ የቢራ ማምረቻ የግብዓት ዕቃዎች ዋጋ በመጨመራቸው ነው ብለዋል፡፡ የዋጋ ጭማሪ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግ ነው በተባለ ሰሞን በመሆኑ፣ የቢራ ፋብሪካው ከንግድ ሚኒቴር በተነገረው መሠረት ጭማሪውን ወዲያው በማንሳት ቀድሞ በነበረው ዋጋ እንዲሸጥ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ተወካይ ገለጻ፣ የዋጋ ጭማሪን ተግባራዊ ባደረጉ በግማሽ ቀን ልዩነት ዋጋውን ወደነበረበት ያወረዱት ያላግባብ ዋጋ  በመጨመራቸው ሳይሆን፣ ወቅታዊውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

በሌላ በኩል ፋብሪካው አዲሱን የዋጋ ተመን ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ወዲያው ወደነበረበት በመመለሱ ምክንያት የዳሽን ቢራ ፋብሪካን በተቀላቀለው የውጭ ኩባንያ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የውጪ ኩባንያዎች በመሆናቸውና የዋጋ ጭማሪ የተደረገው በአግባቡ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ቢያሳዩም፣ ዕርምጃው አገራዊ በመሆኑ ወደነበረበት ዋጋ እንዲመለስ ማድረጋቸውን ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳሸን ቢራ ሁሉ በዕለቱ ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡት የቢጂአይ ኢትዮጵያ ተወካይ ናቸው፡፡ ቢጂአይ ኢትዮጵያ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ያስታወሱት ተወካዩ፣ የዋጋ ጭማሪው የተደረገው ግን የደመወዝ ጭማሪው ሊደረግ ነው ከመባሉ አሥራ አምስት ቀን በፊት በመሆኑ፣ ‹‹ኩባንያችን ያደረገው የዋጋ ጭማሪ የደመወዝ ጭማሪውን ተከትሎ የተደረገ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ተወካዩ በፋብሪካው የዋጋ ማስተካከያ ያደረገበት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንዳለው ገልጸው፣ በተለይ እንደ ብቅልና ጌሾ ያሉ ለቢራ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ዋጋ በመጨመራቸው እነሱም ማስተካከያ ማድረጋቸው ግድ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋም በተመሳሳይ የሚታይ እንደሆነና ለምሳሌም የዩሮ ምንዛሪ በአንድ ዓመት 7.9 በመቶ መጨመሩ ለዋጋ ማስተካከያው ሌላ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 ከዚህም ሌላ መንግሥታዊው የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ሳይቀር ከአንድ ወር በፊት በብቅል ላይ ስድስት በመቶ ዋጋ መጨመሩን፣ ፋብሪካው የ15 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉን፣ ስለዚህ ዋጋ ማስተካከያ ማድረግ ግድ እንደነበር ተወካዩ አስረድተዋል፡፡ የብቅል ዋጋ 21 በመቶ የመጨመረ ቢሆንም ከአንድ ወር በፊት የተደረገው ጭማሪ ስምንት በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ኩባንያው የውጪ እንደመሆኑና ትርፍ አስቦ እየሠራ በመሆኑ አግባብ ያለው ጭማሪ አድርጎ ጭማሪው አግባብ አይደለም መባሉ ለውጭ ኩባንያዎች የሚሰጠው ትርጉም የተለየ በመሆኑ ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል ተብሏል፡፡

የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ተወካይ እንዳሉትም 60 በመቶ የሚደርሰው የቢራ ፋብሪካቸው ግብዓት ብቅል በመሆኑ በዚህ ላይ የተደረገን የዋጋ ጭማሪ ለማካካስ የሚደረግ ማስተካከያ በቂ ምክንያት እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ የሁለቱም ቢራ ፋብሪካዎች አስተያየት የማምረቻ ግብዓት ዕቃዎች መጨመራቸውን ያመለክታል፡፡ ለአከፋፋዮች የሚሰጡበት ዋጋም የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከአከፋፋዮች ውጪ በየሆቴሉ የሚሸጥበትን ዋጋ መተመን የማይችሉ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ዋና አከፋፋዮች ግን የትርፍ መጠናቸው የተገደበ ነው፡፡ ይህንን ፋብሪካዎቹ ይከታተላሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን  ቢራ እንደ ቅንጦት የሚታይና 50 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት በመሆኑ እንደ መሠረታዊ ፍላጎት መታየት የለበትም ብለዋል፡፡

ከዕለቱ ውይይት መገንዘብ እንደተቻለው ግን መንግሥት ወደ ቀድሞ የመሸጫ ዋጋቸው መመለስ እንደሚኖባቸው ፍላጎቱ ነው፡፡ ሆኖም አሳማኝ ምክንያት አለን ካሉ መረጃቸውን ይዘው ሊቀርቡ ይችላሉ የተባለ ሲሆን፣ ይህንንም የሚመለከት አካል እየተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዋጋ የጨመሩ የታሸጉ መጠጦች አምራቾች ወደነበሩበት ዋጋ እንዲመለሱ የአንድ ሳምንት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ሌሎች ተሳታፊዎችም ተመሳሳይነት ያለው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አለ የሚባለውን ችግር ለመቅረፍ የሚተባበሩ ቢሆንም፣ ከማምረቻ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ምን መደረግ እንዳለበት መመካከር ያሻልም ይላሉ፡፡

አንዳንድ አምራቾች ግን ይህንን ማድረግ የሚከብድ መሆኑንና ከወራት በፊት ያደረጉትም የዋጋ ጭማሪ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ዋጋን የመወሰን ሐሳብ የለኝም ቢልም ወደ ቀድሞ የመሸጫ ዋጋችሁ ተመለሱ ማለቱ ዋጋ መወሰን ነው የሚል አስተያየት የሰጡ አሉ፡፡

አቶ መርከቡ በዕለቱ እንደገለጹት፣ መንግሥት ዋጋ የመወሰን ዓላማ የለውም  መንግሥታዊው የብቅል ፋብሪካ ዋጋ ጨምሮ ለቢራ ፋብሪካዎች የዋጋ መጨመር አንድ ምክንያት ሆኖ ሳለ፣ ፋብሪካዎቹ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም ሊባል አይችልም የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ አቶ ኑረዲን ለዚህ አስተያየት በሰጡት ምላሽ፣ የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጭማሪ እየታየ እንደሆነና ተጣርቶ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ገልጸው፣ በቢራ ላይ የተደረገው ጭማሪ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደሌለው ግን አስምረውበታል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment