Thursday, February 13, 2014

መከፋት እና መገፋት...አስናቁ
ሳዑዲ አረቢያ ሁለት አመት ሰርታለች፡፡ሰርታ ያጠራቀመችው፤ያካበተችው ጥሪት ግን የለም፡፡አዲስ አበባ ስትመለስ ቤተሰቦቿ ከቀደመ ህይወታቸው የተቀየረ ነገር አልነበረም፡፡እናቷ ዛሬም ወገባቸውን እያመማቸው በአንድ የድር እና ማግ ፋብሪካ በአቅላሚነት ያገለግላሉ፡፡ደሞዛቸው 400 ብር ብቻ ነው፡፡ታናሽ እህቷ ጠዋት ትወጣለች ማታ ትገባለች፡፡ከቤተሰቡ ጋርም ይሁን ከሰፈሩ ሰው ተግባቦት የላትም፡፡የእሷ ታናሽ ከምትሰራበት የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ተቀንሳ ቤት ተቀምጣለች፡፡
ለአራት ለሚኖሩበት ቤት 1200 ብር የቤት ኪራይ ይከፍላሉ፡፡እናታቸው ሶስቱንም ሴቶች ልጆቻቸውን የወለዱት ከሶስት የተለያዩ ወንዶች ነበር፡፡ያሳደጓቸውም ብቻቸውን ነው፡፡ቤተሰቡ ሰላም የለውም፡፡ስድብ፤ጥል፤ግጭት፤ንትርክ ይበዛል፡፡ሴቶቹ ለድብድብ ከተያያዙ ብዙ ገላጋይ ያስፈልጋል፡፡ጠቡ በቀላሉ አይበርድም፡፡

ከሳዑዲ አረቢያ ተጠርንፋ የተባረረችው አስናቁ(እውነተኛ ስሟ አይደለም) በ33 አመቷ ህይወቷ እንደ ቀላል ድንገት መቆሙ ያብሰለስላታል፡፡የእናቷ የትናንት ልፋት ሳያንስ ዛሬም እፎይ ማለት አለመቻላቸው ይቆጫታል፡፡ሁሌም ብቻዋን ታወራለች፡፡በእናቷ ጉዳይ ከእህቶቿ ጋር አተካራ ትገጥማለች፡፡

የሴቶች ፀጉር ቤት በፅዳት ሰራተኝነት፤ሰፈራችን የሚገኝ ካፌ በአስተናጋጅነት ስራ ጀምራ ነበር፡፡ከሁለቱም ተባረረች፡፡“ምነው?” ስላት “ስታወሪ ትጮሂያለሽ፤ስራ ጥለሽ ቆመሽ ብቻሽን ታወሪያለሽ፤ደምበኛ ታመናጭቂያለሽ ይሉኛል፡፡” አለችኝ፡፡እውነታቸውን ነው፡፡ስታወራ ሰው የሚሰማት አይመስላትም፡፡ይደብታታል፡፡ብቻዋን ታወራለች፡፡ቁጡ ናት፡፡ቶሎ ይከፋታል፡፡ሲከፋት ደግሞ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ አትልም፡፡ግን የክፋት አይመስለኝም፡፡አንዳንድ ጊዜ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋት ይመስለኛል፡፡እናቷ “ልጄ ሳውዲ ሄዳ ከመጣች በኋላ ወሰድ መለስ ያደርጋታል፡፡እባካችሁ ብትናገራችሁም እንዳልሰማ ሆናችሁ ታገሷት” እያሉ የግቢውን ተከራይ ይለማመጣሉ፡፡ከእህቶቿ ስትጋጭ የሚደርስባት ውርጅብኝ “እብድ” የሚል ስድብ ነው፡፡
አስናቁ ሳዑዲ አረቢያ ስለነበረው ህይወቷ ብዙም ማውራት አይሆንላትም፡፡ወይም አትፈልግም፡፡አልፎ አልፎ ካወራችም በድንገት ወደ ሃሳቧ የመጡ ትዝታዎች ገጣጥማ የተሸራረፈ ነገር እንጂ ጥርት ያለ ነገር አይደለም፡፡“አል-ሚትና ነበርኩ፡፡ፅዳት ሰራተኛ….አሰሪዬ በለሊት ቀስቅሳ በረንዳ ታስወለውለኛለች፤ግድግዳ ታሳጥበኛለች፤ባሏ ያልነዳውን መኪና አስር ጊዜ ያሳጥበኛል፡፡ገንዘብ አይሰጡኝም ሲሰጡኝ ደግሞ ለእናቴ እልክላታለሁ…ምግቡ አይጣፍጥም፡፡እና በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር የምበላው፡፡አሰሪዬ ደግሞ ራስሽን ልታጠፊ ነው እያለች ትጨቀጭቀኝ ነበር፡፡ከዛ ሲሰለቸኝ ሶስት ቀን መኝታ ቤቴን ቆልፌ ተቀመጥኩ፡፡ከዛ በሩን ሰብረው ገብተው አወጡኝ፡፡ትኬት ቆርጠው ወደ ሃገሬ ሲልኩኝ የስድስት ወር ደሞዜን አልሰጡኝም ነበር፡፡…..” አያልቅም፡፡ትዝታዋ ሁሉ በመከፋት እና በመገፋት የተሞላ ነው፡፡

“ምን ልስራ?” ትለኛለች፡፡ሁሌ ስራ መስራት፤እናቷን ማገዝ ህይወቷን መቀየር ትፈልጋለች፡፡“አንተ ስራ ፈልግልኝ ስለህ እሺ እያልክ ረሳኸኝ አይደል?” ስወጣ ስገባ አንዳች ተስፋ ይዤ እመጣ ይመስል፡፡ትምህርቷን ዘጠነኛ ክፍል ነው ያቋረጠችው፡፡“ድሮም ትምህርት አይገባኝም ነበር፡፡” በራሷ ላይ አስተያየት ስትሰጥ ጨካኝ ናት፡፡የራሷን ስራ ለመጀመር ገንዘብ የላትም፡፡በተረፈ የሞከረችው ሁሉ ወደ መከፋት እየገፋት ዘላቂ ስራ መስራት አልቻለችም፡፡አንድ ሰሞን የሰፈሩን ስራ አጦች እየዞሩ በሚመዘግቡት የቀበሌ ሰዎች ተስፋ አድርጋ ነበር፡፡“ካደራጀናችሁ በኋላ ገንዘብ ተበድራችሁ ስራ ትጀምራላችሁ ብለውናል፡፡” ብላኝ ነበር፡፡ ይህንንው እያወሩ ሶስቴ መዘገቧት፡፡ከምዝገባው በኋላ የውሃ ሽታ ሆኑ፡፡አሁን በመደራጀቱም ሆነ በብድሩ ተስፋ ቆርጣ ከሰፈሩ በሚገኝ ፀጉር ቤት እና ፊልም ማከራያ ትሰራለች፡፡የምታውቀው ሰው በመንገድ ካለፈ “ና ፊልም ተከራይ!” ማለቷ አይቀርም፡፡ልመና አይደለም፡፡ውስጡ ልመናን ያዘለ የእንተዋወቃለን ትዕዛዝ እንጂ፡፡ “ዛሬስ ፊልም አትከራይም?” ………..

ፀጉር ቤቱ አካባቢ ስልክ እንጨት ተደግፈው፤ጫት እየቃሙ ሲጋራ የሚያቦኑት ይሳለቁባል፡፡ይለክፏታል፡፡ተሳልቆውን፤ለከፋውን ወይም ስድቡን እንደ አመጣጡ ሳይሆን እንደ ስሜቷ ታስተናግደዋለች፡፡የከፋት ቀን አያድርስ ነው፡፡