Friday, February 14, 2014

እውነት ከመንበርህ የለህማ! ሙሉጌታ ተስፋዬ


ምነዋ መንግሰተ ሰማይ! የምህረትሽ ቀን ራቀ?
ምነው ትንግርትሽ ረቀቀ ?
ምነው ኪዳንሽ ታጠፈ … ወዝሽ ወዘናሽ ነጠፈ?
እንደ ዳጉሳ ድፍድፍ … ላቦትሽ ተንጠፈጠፈ
አሳርሽ ጠሎ አሰፈፈ
ምነው እርሾው ተማጠጠ …. ጎታው ጎተራው ታጠጠ
ረሀብ ላንቃው ፈጠጠ….ያዳም ልጅ አፅሙ ገጠጠ
ምነው ጭር አለ ቀየው! ሀሩር ነዲዱ በረታ
ኮርማው ጥማዱ ተረታ
ምነው ነበልባሉ አየለ … ማሳው ተንቀለቀለ
ነቀለ ሞፈር ሰቀለ ተግድራ ደቀለ
ምነው ምድር ጨነገፈች ዝላ ተርገፈገፈች?
ካስማ እንደተደገፈች ምነው ተሳታብብ ረገፈች?
ምነው የናት ጡት ደረቀ ... አራስ ልጅ ተስረቀረቀ
ምነው አንጀቱ ታለበ … በውኑ ተበለበ
ኮሶ ስንብቱን ለለበ
ምነው ወላድ ተንሰለሰለ … ልሳነ ቃሉ ሰለለ

በቁሙ ከስሞ ከሰለ
አቤት የርግማን ቁርሾ
በንጣይ እርሾ መነሾ!
ምነው ላይፀድቅ በቀለ!
የሰው ልጅ ዋጋ ቀለለ
ትቢያ አፈር ተቀላቀለ
ሆድና ጀርባው ተጣብቆ አንጀቱ በራብ ተሰብቆ
እንደፈረሰ ክራር ቅኝት ሰርቅ እንዳነቀው ድብኝት
ወለሰ! ስልቱ ስለቱ
ሰው
ያ ሰው ጠንካራው ብረቱ
የጥንት የጥዋት የመሰረቱ
ውሳኔው ተርመጥምጦ
ተፈጥርቆ ተዳምጦ
ተሞዥርጎ ተሸምጥጦ
ምነው ጓሽቶ ሆመጠጠ
እንደበሬ ጨው ሆረጠ
ባፍላው ተዝለፍልፎ አረጠ፡፡
እንደ መወክል አጎዛ በችንካር ተገድግዶ
ይግባኝ እንዳይል ታግዶ
እንደ ወይራ ፍልጥ ተማግዶ
ምነው ኩክ ብሎ ሳይነቃ … ምነው ሳይጠረቃ መከከ
በስሎ ሳይሰላ ደከከ
ተፈጥሮ ፊቱን ጨፍግጎ
እንደግራዋስር መርግጎ
ሁዳዱን እያነደደ
አቤት ባዩን እያሳደደ
እንደ ግራ ግመሬ … በነፍር ጥፍሩ እየለቀመ
የረጨነውን እየቃመ
ጉልማችንን ሲያመክነው
ወረታችንን ሲያባክነው
እኮ ማንን ልንኮንን ነው?
የመቅሰፍት ደመና ሰሮ … ሽቅብ ጠቅሶ ሲያርመሰምስ
እንደወረግ ተደርምሶ እያንቃቃ እኛን ሲያምስ
ወገብ ከፍሎ ደረት ገምሶ አቅም ሲከላን አቅምሶ
እኮ እስከመቸ እግዚኦትነ
እኮ እስከመቸ ኪራራይሶ?
የቀንጨለማ ሲወረን እህል ሸማኔው ደውሮ ለጆቢራ ሲወረውረን
አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ቀሪ ወሬ ነጋሪ የሚያሳጣን
እኮ ምን በድለን ምን አጥፍተን ምን በወጣን?
የምን ቅጥት ነው ይሄ ቀጥፎ እንደተያዘ ጩልፋት
አርሰው አደፍርሰው በበሉ የምን የራብ ቱርፋት
ከንቱ ውእቱ ልፋት፡፡
እኮ እንደ ኖህ ዘመን ንፍር ውሃ ዘር ሳይተኩ ታክቶ መጥፋት!
ምነው ዲበኩሉ ቤዛ አለም
ጎህ ቀዶ በቀን መጨለም?
በጠኔ ርዶ መስለምለም
እኮ ያንጀትን ባንጀት መፋለም?
ምነው? አዛውንቱ በየጉድባው
ጋሜው ድምድሙ ኮበሌው … በየጥጉ በየደረባው
ወድቆ ደርቆ ሲነፈራ
ምነው ተፈጥሮስ ጡር አትፈራ?
ምን ይሉታል ይሄን ብይን አንቀፅ ገልፆ ሳያጣቅስ
ምን ይሉታል ይሄነን ፍርድ
እንዲህ ያለ ጉድ አለ እንዴ?
እግዜር ወንዱ እግዜር መንዴ!
ደረቅ ጡት እየጠባን ቁረንጮ ስንገተግት
ከመንግስተ ሰማይ የምህረት ግት
ምነው የማርያም ልጅ የስርየት ቀንህ ራቀ
ምነው ታምርህ ረቀቀ
በየጥሻው ተወትፈን እንደተምች ስንረፈረፍ
ቅኔ በበቀቀን ሲዘረፍ
አቀርቅረን ስናንቋርር
ቅሪታችንን ስናንቃርር
እንደ ቀላጤ አከንባሎ ቁልቁል ባፍጢም ተተክለን
በእርኩስ አመዳይ ተበክለን
እንዲህ የትም ስንቀር እያየህ ዝም ካልክማ
እውነት … እውነት ከመንበርህ የለህማ!
እንደ ሰባራ ቅል ደቀን
ድበን በራብ ተደቅድቀን
እርሻው ማረሻው ሲከዳ … ሰማይ መሬቱ ሲያብል
እያየህ ዝም ካልከኝ …. እኔስ እንደሌላው የለህም ብል
ምንተዳየ ብትፈርድብኝ መቸም አሽተህ አትቅመኝ እንደውልብኝ
ናዳ እንደሚጥል ጫላዳ ድርቅ ሲሳለቅብን
እየነዳ እያነደደ የገሞራ ድኝ ሲለቅብን
እያየህ ዝም ካልክማ …
እውነት አውነት ከመንበርህ የለህማ!
ጀንበር ትንታጓ ሰብ አለሙን ስትፈጀው
አብ ወልድህ ካልባጀን
ድርሳን ትንቢትህ ካልዋጀን
አንተስ ምንህ መለኮት እኔስ ለምን ያንተ ባሪያ
ሆዴን ሁዳዴን ላምልክ እንጅ ትንሳኤ እንደሌለው እሪያ
ያንተን ጉድማ አየሁት
ያንተን ጉድልማ ለየሁት
ማረኝ ሲሉት የሚመር የማይታደግ አላልክም
ወትሮም የተማረ ቄስ እንጅ የሰው ልጅ መላክ አይልክም
ለካ ሲያጋልጥ ይቆምጣል … ወራት ሲጥል ይከፋል
እንደ አመለ ጉድጓድ እህል ሞት በክቶ ይከረፋል
ለካስ ሰው መሆን እዳ ነው
ለካስ ሰውነት ባዳ ነው
እህል ውሃ ቢያደነድነው
ሲያጣ ሲነጣ በድን ነው፡፡
የኛስ ይሁን እንዳሻው ለእጥፍ ፈተና ከፈጠርከን
ለፍታችሁ ተፍታችሁ ኑ ካልከን
ለቀብር አፈር ከወጠንከን
ግን ፡- ግን ብላቴኖች ምን በደሉ
የማንን አደራ በልተው የማነን አማና አጎደሉ
እንብርታቸው ያላረረ
አጥንታቸው ያልከረረ
ሰማይ በቀል እንደቋጠረ
እጣቸውን እየመጠረ
መንገዳቸውን በእሾህ እያጠረ
እንደ ደራሽ ውሃ አግተልትሎ
በራብ አኮርማጅ ተልትሎ
ከእናት እቅፍ በግፍ ነጥቆ
ሲሰልፍብን ባጭር ታጥቆ
እያየህ ዝም ካልክማ
እውነት እውነት ከመንበርህ የለህማ!
እንደ ታዛ ስር ሰንሰል አሰልስሎ እያበሰበሰ
እንደ ሙሬ እየጠረገ እያጋበሰ
እንደ ሙሬ እየጠረገ … እያጋበሰ
የዘጸዓት ትንቢቶ ደርሶ ሰብ ዓለም ከል ከለበሰ
በማን ሊዳኝ ነው ቅጣቱ የሰው ዘር አንዲት ቅንጣቱ
ያባወራ ባላውራጣቱ
እንደ በልግ አውድማ ነዶ … ምድር ለቅልቆ ከምሮ
ነፍስ ከእስትንፋስ ነጥሎ … ሲኦል እቶን ውስጥ ሞጅሮ
በነበልባል መንሽ እየዘራ በረሀብ አራገበው
ሰው እርጥቡን አንገበገበው
ነፍስ ይማር እርካቡ ረገበ
ቀብርም አስከሬን ጠገበ
ፀሀፊም ድርሳን ዘገበ፡፡
ጥንብ አንሳን ግብር ጠርቶ በራሪ ጋር ይወዳጅበት
ስለት እንደዋጀበት እያጋፈረ ይባጅበት
ወትሮም የሞት ምሬትን ያልቀመሰ የራብ እሳት አይዋጅብበት
እንዲህ አይንን ጡር እያስከፈለ
እንደ በቆሎ እሸት እየጠበሰ እየፈለፈለ
ባይበላውም ያባለው!
መቸም ተጠቀም አላለው
አይ ወልዴ አባ ግድ የለው!
በየጥሻው ተወትፈን እንደተምች ስንረፈረፍ
ቅኔ በበቀቀን ሲዘረፍ
አቀርቅረን ስናንቋርር
ቅሪታችንን ስናንቃርር
እንደቀላጤ አከንባሎ ቁልቁሉ ባፍጢም ተተክለን
በእርኩስ አመዳይ ተበክልን
እንዲህ የትም ስንቀር እያየህ ዝም ካልክማ
እውነት እውነት ከመንበርህ የለህማ!

No comments:

Post a Comment