Thursday, February 27, 2014

የአድዋው አርበኛ-ካውንት አባይ-ኒኮላይ ስቴፓኖቪችበንጉሰ ነገስት አፄ ምኒሊክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር ራስ አሉላ እንግዳን፤ራስ መኮንን፤መንገሻ ዮሃንስ፤የወሎው ራስ ሚካኤልን፤ተክለ ሃይማኖት፤ ንግስት ጣይቱን እና ሩሲያዊውን ኒኮላይ ስቴፓኖቪችን በፊት አውራሪነት ይዟል፡፡ከእነዚህ መካከል አንዱ በዜግነቱም ሆነ በመልኩ እንግዳ ነው፡፡ከሌሎቹ የጦር አበጋዞች ጋር ግን አንድ ነገር ያመሳስለዋል፡፡ለኢትዮጵያ የነበረው ጥልቅ ፍቅር!
Nikolay Stepanovich Leontiev

ኒኮላይ ስቴፓኖቪች ሊኦንቴቭ (Nikolay Stepanovich Leontiev) አገር አሳሽ፤የጦር ባለሙያ፤አማካሪ፤ፀሃፊ እና የጂኦግራፊ ባለሙያ ነበር፡፡ እ.አ.አ ከ1862-1910 በህይወት ኖሯል፡፡በሩሲያ የጦር አካዳሚ ተምሮ አገሩን አገልግሏል፡፡ኒኮላይ ኢትዮጵያ የምትባለውን የሩቅ ሃገር የማየት ህልም ነበረውና አገሪቱን የተመለከቱ መረጃዎችን ይሰበስብ ነበር፡፡ያሰበው ተሳካለት እና ከሩሲያ የሳይንስ አካዳሚ እና ከሩሲያ ጂኦግራፊካል ሶሳይቲ ባለሙያዎች ጋር ለዘመናት ወደ ተመኛት ኢትዮጵያ የመምጣት እድል አገኘ፡፡ዋንኛ ተልዕኮው ግን ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን መፍጠር ነበር፡፡

ኒኮላይ ስቴፓኖቪች ወደ ኢትዮጵያ 11 ሰዎች አቅፎ ለሚጓዘው ልዑክ መሪ ነበር፡፡በኢትዮጵያም ከንጉሰ ነገስቱ አፄ ምኒሊክ ጋር ተገናኝቶ ተወያይቷል፡፡ንጉሰ ነገስቱ ከሩሲያ ጋር ወዳጅነት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ልዑክ አዘጋጅተው ከኒኮላይ ጋር ወደ ሩሲያ የላኩት ከመጀመሪያ ውይይታቸው በኋላ ነበር፡፡ኢትዮጵያውያኑ ልዑካን በሩሲያ የጠበቃቸው አቀባበል እጅጉን ደማቅ እንደ ነበር ስለ ኒኮላይ የተፃፉ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት የሚገልፁ አበባዎች፤የእንኳን ደህና መጣችሁ ደብዳቤዎች እና በርካታ ስጦታዎች በገፀ-በረከትነት ቀርበውላቸዋል፡፡
         ኒኮላይ ኢትዮጵያ በነበረበት ወቅት አፄ ምኒሊክ ተመልሶ እንዲመጣ ያቀረቡለትን ግብዣ በመቀበል እ.ኤ.አ. በ1895 ከበርካታ የጦር መሳሪያዎች ጋር የኢትዮጵያን አፈር ረገጠ፡፡(በወቅቱ ካመጣቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል 30,000 rifles, 5,000,000 cartridges, 5000 sabres, and a few cannons ይጠቀሳሉ፡፡)


Leonid Artamonov
የሩሲያ ፀሃፊያን ኢትዮጵያ በአድዋ ለተቀዳጀችው ድል ኒኮላይ ስቴፓኖቪች እና ሊዮኒድ አርቶሞኖቭን (Leonid Artamonov)  ጨምሮ በአውደ ውጊያው በአማካሪነት የተሳተፉ 15 ያህል የጦር አማካሪዎች ሚና ላቅ ያለ እንደ ነበር ይጠቅሳሉ፡፡

ኒኮላይ በንጉሰ ነገስቱ ትዕዛዝ መሰረት ዛሬ ቱርካና ተብሎ ወደ ሚጠራው የቀድሞው ሩዶልፍ ሃይቅ አንድ የኢትዮጵያ አሳሽ ጦር እየመራ መጓዙ በህይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሯል፡፡አፄ ምኒሊክ በጦር ሰራዊታቸው ውስጥ ካውንት (count) የሚለውን ማዕረግ መጠቀም የጀመሩት ኒኮላይ ስቴፓኖቪችን ከተዋወቁ በኋላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እርሱንም ካውንት አባይ (Count Abai) የሚል ማዕረግ ሰጥተውት ነበር፡፡

ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የአፄ ምኒሊክ ዘመናዊ ጦር ማደራጀት የጀመረውም ኒኮላይ ስቴፓኖቪች ሊኦንቴቭ ነበር፡፡ ኒኮላይ በዘመናዊነት ያሰለጠነውን ጦር ለንጉሰ ነገስቱ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 1899 አሳይቷል፡፡የኒኮላይ ጦር ከሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች (እንደ ሩሲያውያኑ አባባል ከሴኔጋል) ጭምር ወታደሮችን ሳይመለምል አልቀረም፡፡ስልጠናው የተሰጠውም በሩሲያ እና ፈረንሳይ ወታደራዊ መኮንኖች ነበር፡፡
ኒኮላይ ከኢትዮጵያ ወደ ሩሲያ የተመለሰው ቁስለኛ በመሆኑ ነበር፡፡ይሁንና ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ከልቡ አልጠፋችም፡፡በኒኮላይ ስቴፓኖቪች የኢትዮጵያ ቆይታ ላይ የፃፉ ሩሲያዊ ፀሃፍት አገር አሳሽ ወይስ ሰላይ ሲሉ እውነተኛ ተልዕኮውን ለማጠየቅ ይሞክራሉ፡፡በሁሉም ፅሁፎች ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ነገር ቢኖር ግን ሰውየው ለኢትዮጵያ የነበረው ጥልቅ ፍቅር እና ሃገሪቱን ለማገዝ ያደርግ የነበረው ጥረት ነው፡፡

P.S. በኒኮላይ ስቴፓኖቪች ሊኦንቴቭ የህይወት ታሪክ እና የኢትዮጵያ ቆይታ ላይ ኢትዮጵያዊ ፀሃፍት ያሉት ነገር መኖሩን አላየሁም፡፡ነገር ግን ለማረጋገጥ በሙከራ ላይ ነኝ፡፡

ምንጭ
http://www.proza.ru/