Monday, February 24, 2014

በመከራ መካከል-ስደተኛው ትውልድ

ስደተኛዋ የ18 አመት ወጣት ቤት ፍለጋ በምትንከራተትበት ወቅት ነበር አስገድደው ከደፈሯት ሰባት ሰዎች እጅ የወደቀችው፡፡በወቅቱ የሶስት ወር ነፍሰ ጡር ነበረች፡፡ጥቃቱን የፈፀሙት ሰዎች በቡድን የፈፀሙትን ድርጊት በቪዲዮ ቀርፀው በኩራት በማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ ሲያሰራጩ የተሰማቸው ሃፍረት አልነበረም፡፡እናም በዚሁ ቪዲዮ ምክንያት ያልተገባ ድርጊት በመፈፀም በሚል ለእስር ተዳረገች፡፡አስገድደው የደፈሯት ሶስት ወንዶች በ100 ጅራፍ ሲቀጡ ቪዲዮውን በማህበራዊ ድረ-ገፆች ያሰራጩት ሁለቱ ደግሞ የ40 ጅራፍ ቅጣት እንደ ተጣለባቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ቀሪዎቹ የቀረበባቸው ማስረጃ በቂ ባለመሆኑ በነፃ ተሰናብተዋል፡፡
ወጣቷ ስደተኛ ፈፅማዋለች በተባለው ወንጀል የአንድ ወር እስራት እና 5,000 የሱዳን ፓውንድ መቀጮ ተጥሎባታል፡፡የወጣቷ ክስ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ከጋብቻ ውጪ ወሲባዊ ግንኙነት በመፈፀም ወንጀል የቀረበባት ክስ ተቀባይነት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ በድንጋይ ተወግራ የምትገደልበት አሰቃቂ ሁነት ሊፈፀም ይችል ነበር፡፡ሆኖም ተበዳይ ፍርድ ቤቱን በትዳ ውስጥ የነበረች መሆኗን ማሳመን በመቻሏ ተርፋለች፡፡በቁጥጥር ስር ከዋለችበት ጊዜ ጀምሮ በእስር ላይ የምትገኘው ወጣት አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት እንዳልቻለች ስትራቴጂክ አሊያንስ ፎር ዉመን ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ የተሰኘ የግብረሰናይ ድርጅት በድረ-ገፁ አስፍሯል፡፡
አሁን በእርግዝና ዘጠነኛ ወር ላይ የምትገኘው ወጣት በህገ-ወጥ መንገድ በሃገሪቱ ተገኝታለች የሚል ክስ ይጠብቃታል፡፡እናም ወደ ሃገሯ ልትጋዝ ትችላለች፡፡

ስደተኛ ትውልድ

ማህበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፤ተደጋጋሚ ድርቅና ረሃብ፤ስራ አጥነት፤የኑሮ ውድነት እና መሰል በርካታ ችግሮች ወጣት ኢትዮጵያውያንን ለስደተኝነት እየዳረገ መሆኑን በጉዳዩ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በተሰደዱባቸው ሃገራት ህጋዊም ይሁኑ ህገ-ወጥ በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ይፈፀሙባቸዋል፡፡በስቃይ እና እንግልት ብዛት ራሷን ያጠፋችው አለም ደቻሳ፤በቀድሞ የሊቢያ መሪ ቤተሰቦች ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት የደረሰባት ሸዋዬ ሞላ እና ከሳዑዲ አረቢያ በስቃይና እንግልት ወደ ሃገራቸው የተጋዙት ከ151 000 በላይ ስደተኞች የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አካል ናቸው፡፡


ዘመናዊ ባርነት

አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ትዕግስት ትምህርቷን ስትጨርስ በሆቴል አስተናጋጅነት መስራት ጀምራ ነበር፡፡ወርሃዊ ደሞዟ እጅጉን አነስተኛ የነበረ ቢሆንም ፈፅሞ ወደ አረብ ሃገራት የመሰደድ ሃሳብ አልነበራትም፡፡ከዚህ አልፎ ጓደኞቿ ተወልደው ባደጉባት ሃገራቸው ጥረው ግረው ህይወታቸውን ለመቀየር እንዲሞክሩ ተከራክራለች፡፡ሆኖም በተሰማራችበት የሆቴል አስተናጋጅነት የስራ ዘርፍ የተረፋት ለከፋ እና መሰረታዊ ፍላጎቷን እንኳ ማሟላት የማያስችል አነስተኛ የወር ደሞዝ ነበር፡፡እናም ወደ የመን ሰንዓ ተጓዘች፡፡ጉዞውን ያመቻቸላት ደላላ ደሞዟ 100 ዶላር እንደሆነ ቢነግራትም ይከፈላት የነበረው ግምሹን ብቻ ሆነ፡፡የተቀጠረችበትን ቤተሰብ ምግብ ማዘጋጀት፤ልብስ ማጠብ እና ሙሉ ግቢውን ማፅዳት በአንድ ትዕግስት ትከሻ ላይ ወደቀ፡፡የስራው ብዛት የሚፈጥርባት ከፍተኛ ድካም በአግባቡ እንዳትመገብ ያግዳት ጀመር፡፡ሰውነቷ እጅጉን ተጎዳ፡፡ከዚህ አልፎ ተደጋጋሚ ህመም ያጋጥማት ጀመር፡፡ይህንን ሁኔታ አሰሪዎቿ በትዕግስት ለመመልከት አልቻሉም፡፡ተባረረች፡፡ሁለተኛ ከተቀጠረችበት ቤት አሰሪዎቿ አልወደዷትም፡፡ሶስተኛው ቤት አባቷ  መሆን የሚችለው አባወራ አይኑን ጣለባት፡፡ ነገር ከመበላሸቱ በፊት የአሰሪዋ ልጆች ለሁለት ወራት ያገለገለችበትን ክፍያ እንኳ ሳይፈፅሙ እንድትባረር አደረጉ፡፡በመጨረሻ በድብቅ በህገ ወጥነት ለመስራ ወሰነች፡፡
እንደ ትዕግስት፤አለም ደቻሳ እና ሸዋዬ ሞላ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅሞባቸዋል፡፡አሁንም እየተፈፀመባቸው ይገኛል፡፡ሰብዓዊ ክብራቸውን፤መብት እና ደህንነታቸውን የሚጥስ የስራ ብዛት እና ክፍያ፤ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃት በአሰሪዎች እንደሚፈፀም በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡በኢትዮጵያውያኑ ላይ የሚፈፀመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆምም ሆነ ስደተኛ ኢትዮጵያውን የሚደርስባቸውን ፈተና አስቀድሞ ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎች እጅጉን አናሳ ናቸው፡፡መንግስት አልፎ አልፎ  ለሚፈጠሩ ክስተቶች ደካማ ምላሽ ለመስጠት ከመሞከር ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደርገው ጥረት እስካሁን አልታየም፡፡
በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ዜጎችም ለአሳዛኝ አጋጣሚዎች  አነስተኛ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ሙከራቸው የተበታተበ እና ጊዜያዊ ሆኗል፡፡

እስከዚያው…


ወደ ሳዑዲያ አረቢያ ይደረግ የነበረው ህጋዊ ስደት በጊዜያዊነት ታግዷል፡፡ኩዌትም ከኢትዮጵያ የቤት ሰራተኞች መቅጠር ማቆሟ ተሰምቷል፡፡ይህን የሰማችው ባለትዳር እና የሶስት ልጆች እናት ጀሚላ(ስሟ የተቀየረ) የሁለቱ ሃገሮች በር እስኪከፈት ወደ ሱዳን ማማተር ይዛለች፡፡ጀሚላ ከባለቤቷ መለየት ባትሻም ከልጆቿ አጠገብ መለየት ባትፈልግም በቤታቸው ያረበበው ድህነት አልወጣ ማለቱ አስጨንቋታል፡፡እናም ከሻይ ቤት ተቀጥሮ የሚሰራ ባለቤቷን ለማገዝ ብቸኛው አማራጭ ስደት ነው ብላ ደምድማለች፡፡