Wednesday, April 17, 2013

ከየመን የተመለሱ በርካታ ስደተኞች ወደቀዬአቸው መመለሻ አጥተው ተቸግረዋል

-    ሰሞኑን ከሦስት ሺሕ በላይ ስደተኞች ይመለሳሉ

ማክሰኞ ማለዳ ከየመን ዋና ከተማ ሰንዓ አዲስ አበባ የገቡ 318 ስደተኞች፣ ወደየመጡባቸው አካባቢዎች የሚመለሱበት ገንዘብ በማጣታቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ገለጹ፡፡ መንግሥት እንዲረዳቸው ተማጽነዋል፡፡
አብዛኞቹ ስደተኞች ከሁለት ወራት በላይ በየመን ሲቆዩ ምንም ዓይነት ሥራና ገቢ ባለማግኘታቸው፣ ለእንግልት ተዳርገው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በርካቶቹም በሰንዓ በኩል ሳዑዲ ዓረቢያ ለመግባት አቅደው የወጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ሲወጡም ለሚያጓጉዟቸው ሕገወጦች እስከ 8,000 ሺሕ ብር መክፈላቸውን ይናገራሉ፡፡

ከስደተኞቹ መካከል ሪፖርተር ያነጋገረውና ከወሎ አካባቢ የተሰደደው ኢድሪስ ሐሰን ሁሴን መሐመድ እንደሚገልጸው፣ በየመን በኩል ሳዑዲ ዓረቢያ የመሻገሩ ዕቅድ አልሰምር ሲላቸው ለየመን መንግሥት እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከየመን የተመለሱት ስደተኞች የዜግነት ማስረጃ ከኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መሥርያ ቤት ተሰጥቷቸው ከአውሮፕላን ማረፊያ ቢወጡም፣ ለመጓጓዣ የሚሆናቸው ምንም ነገር እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡

ኢድሪስ ከመሰሎቹ ጋር ሆኖ በነፍስ ወከፍ ወደ ትውልድ ሥፍራቸው የሚመለሱበት ሦስት መቶ ብር በማጣታቸው ስደት ከሄዱበት አገር ያልተናነሰ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ይናገራል፡፡ ከስደት የተመለሱት ዜጎች በአብዛኛው ከወሎ፣ ከሐረርና ከጅማ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸውንም ኢድሪስ ገልጿል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካይነት የየመን መከላከያና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ስደተኞቹን ለመመለስ በመስማማታቸው የመጡ ናቸው፡፡ ዛሬና ነገ የሚመጡትን ጨምሮ ከ3,000 በላይ ስደተኞች ወደአገር ቤት ለመመለስ ፈቃደኛ በመሆናቸው እንደሚመጡ እየተጠበቀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም አይኦኤም የተባለው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅትን ጨምሮ በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለስደተኞች ድጋፍ ይሰጡ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ከየመን የሚመለሱት ስደተኞችን የሚደግፍ አካል ባለመገኘቱ የተመላሾቹ ችግር የፀና መሆኑ ታውቋል፡፡

አብዛኞቹ ስደተኞች ከሳምንት በላይ በእግራቸውና በመኪና እየተጓዙ የጂቡቲ ድንበርን እንደሚሻገሩ ሲታወቅ፣ ከዚያ በኋላ ያለውን የባህር ጉዞ በአነስተኛ ጀልባ ተሳፍረው በከፍተኛ ስቃይና እንግልት የመን እንደሚደርሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በጉዟቸው ዕድል ቀንቷቸውና በባህር ላይ ከመሞት ተርፈው የመን የሚገቡ ስደተኞች ግን እንዳሰቡት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያም ሆነ ወደሌሎች የዓረብ አገሮች መግባት እየተሳናቸው ናቸው፡፡

በሕገወጥ መንገድ ከሚጓዙት ውስጥ ጥቂት የማይባይሉት እንደገና ሲሄዱ ተይዘው እንደሚመለሱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ሆኖ ማክሰኞ ዕለት አዲስ አበባ የገቡት ስደተኞች የሚመገቡትም ሆነ የሚጠለሉበት ከማጣታቸውም በላይ፣ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው የሚወስዳቸው አካል ፍለጋ ሲባዝኑ ታይተዋል፡፡ ብዙዎቹ ገጽታቸው ላይ ድካም፣ ተስፋ መቁረጥና ጉስቁልና ይታይባቸዋል፡፡ ከስደት ተመላሾቹ መካከል ዕድላቸውን ለመሞከር ወደ ቀይ መስቀል ማኅበር ያመሩም በርካቶች ናቸው፡፡   
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment