Thursday, March 1, 2012

ቴዲ አፍሮ የታደገው ነፍስ አገሩ ገባ


‹‹ስለቴዲ አፍሮ የምናገርበት አንደበት የለኝም››  አስመሮም ኃይለ ሥላሴ

የሰው ሕይወት አጥፍቷል በሚል በአሥር ቀናት ውስጥ በሞት እንዲቀጣ ወይም የነፍስ ዋጋ 700 ሺሕ ብር እንዲከፍል የፍርድ ውሳኔ ተላልፎበት፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ሙሉ ክፍያውን (700 ሺሕ ብር) ከፍሎ ያተረፈው ኢትዮጵያዊው አስመሮም ኃይለ ሥላሴ ገብረ ኢየሱስ፣ የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከእስር ተፈታ፡፡ የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

አስመሮም የቀድሞ የሶማሊያ ግዛት በነበረችው ፑንትላንድ ቦሳሶ ወደብ አካባቢ ከሦስት ዓመታት በፊት በሚኖርበት ቤት ውስጥ ከሌሊቱ 7፡30 ሰዓት ሲሆን በር ሰብረው አደጋ ሊያደርሱበት በሞከሩ ሶማሊያውያን ላይ በወሰደው የመከላከል ዕርምጃ፣ አንድ ሰው ሞቶ ሌላኛው በመቁሰሉ ለእስር መዳረጉንና በመጨረሻም በሞት እንዲቀጣ ወይም ገንዘብ እንዲከፍል ተወስኖበት ነበር፡፡ ለነፍስ ዋጋ ክፈል የተባለውን 700 ሺሕ ብር በአሥር ቀናት ውስጥ ካልከፈለም በዕለተ ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ.ም ግድያው ይፈጸምበት ነበር፡፡ ጥቅምት 14 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የምትኖረው እህቱ ልዋም ኃይለ ሥላሴ ወደ ሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መጥታ ባቀረበችው ጥቆማ መሠረት ሁኔታው በመዘገቡ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በጋዜጣው የወጣውን ዜና በማንበብ አስመሮምን ሊታደገው ችሏል፡፡ ሕይወቱ መትረፉንም በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በፑንትላንድ ግዛት ታስሮ ሦስት ዓመታት ከአንድ ወር የቆየው አስመሮም፣ ስደት የጀመረው በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በ1990 ዓ.ም መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ተወልዶ ያደገው አስመራ ከተማ ውስጥ መሆኑን የገለጸው አስመሮም፣ እናትና አባቱ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት ያለምንም ሀብትና ንብረት ስላባረራቸው እሱና ጓደኞቹ ወደ ምፅዋ መሰደዳቸውንና ከቤተሰቡ ጋር መለያየቱን ተናግሯል፡፡

ከምፅዋ 2000 ናቅፋ በመክፈል ወደ የመን፣ ከየመን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ገብቶ የተወሰነ ጊዜ እንደሠራ ተጠርዞ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የሚናገረው አስመሮም፣ ከቤተሰቦቹ ሲለያይ አድራሻ ባለመቀበሉና ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊ ዘመዶቹን ስለማያውቃቸው፣ አዲስ አበባ መጥቶ በያዛት ገንዘብ ከመዝናናት በስተቀር ምንም ማድረግ አለመቻሉን ገልጿል፡፡

ለአሥር ጊዜያት ስደትን ሞክሮ ከተወሰነ ጊዜ የሥራ ቆይታ በስተቀር ተረጋግቶ መሥራት አለመቻሉን፣ እዚያ ሆኖ ሲሠራ ለቤተሰቡ ገንዘብ የሚልክበት አድራሻ ስለሌለው ሌሎች ለቤተሰብ ሲልኩ ያዝን እንደነበር ገልጾ፣ በስምንተኛው የስደት ጉዞው ወንድሙን ጅዳ እስር ቤት ውስጥ እንዳገኘውና አብረው ተጠርዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ቤተሰቦቹን ማግኘቱን አውስቷል፡፡

ቤተሰቦቹን (አባቱን፣ እህትና ወንድሞቹን) መቀሌ ሄዶ ካገኘና አብሯቸው የተወሰነ ጊዜ ከተቀመጠ በኋላ ምንም የሚሠራው በማጣቱና አባቱ ሲቸገሩ (እናቱ በሕይወት የሉም) ማየት ያልቻለው አስመሮም፣ ተመልሶ ወደ ስደት መጓዙን ገልጿል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ቤተሰቡን ከረዳ በኋላም ተጠርዞ እንደገና መመለሱንና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ስደት ሲሄድ ከሐረር ወደ የመን የተጓዘች ፈሪሀ አብዲ የተባለችን ልጅ ማግኘቱንና በፍቅር አብረው መኖር መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

ከፈሪሀ ጋር በፑንትላንድ ግዛት ቦሳሶ ወደብ ላይ ሻይ ቤት መክፈታቸውንና ሦስት ልጆች መውለዳቸውን የገለጸው አስመሮም፣ ሁለቱን ልጆቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከው የመጨረሻዋን ልጅ ይዘው በጋራ እየሠሩ እያሉ ከሦስት ዓመት በፊት ያልጠበቁት ችግር እንደገጠማቸው ገልጿል፡፡

አምስት ሶማሊያውያን ከሌሊቱ 7፡30 ሰዓት ሲሆን የመኖሪያ ቤታቸውን ሰብረው በመግባት ሊያደርሱባቸው የነበረውን አደጋ ለመከላከል ባደረገው ትግል አንድ ሰው በመሞቱና አንዱ በመቁሰሉ ለእስር መዳረጉንም ተናግሯል፡፡ የአንድ ወር ሕፃን ይዘው ይኼ አደጋ በመፈጠሩ የልጆቹ እናትና እህቷ የደረሱበትን ሳያውቅ የታሰረው አስመሮም፣ በወቅቱ ለማምለጥ ቢሞክርም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጿል፡፡ ከ20 ቀናት ቆይታ በኋላ ፍርድ ቤት ቢቀርብም የተፈረደበት ሞት መሆኑን የገለጸው አስመሮም፣ የነበረውን ሁኔታ ያውቁ የነበሩ የቦሳሶ ወደብ ነዋሪዎች ፍርዱን መቃወማቸውንና የኢትዮጵያ ቆንስላዎችም ጣልቃ በመግባታቸው የሞት ፍርዱ ወዲያው ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ ገልጿል፡፡

ፀቡ እንደተፈጠረ ለጊዜው በመጥፋቱ 250 ኢትዮጵያውያን ታስረው እንደነበርና እሱ ተይዞ ሲቀርብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን ማወቁንም ተናግሯል፡፡ የገደለው ሶማሊያዊ ‹‹ዑስማን መሀመድ›› የሚባል ጎሣ ዝርያ አባል በመሆኑ ከፍተኛ ክብር እንዳላቸውና እነሱን መንካት ከፍተኛ ቅጣት የሚያስቀጣ መሆኑን፣ ፖሊሱም፣ ዳኛውም የአገሪቱም መንግሥትም የሚያደላው ለእነሱ መሆኑን አስመሮም ፍርድ ቤት ሲመላለስ ማወቁን ተናግሯል፡፡

በአካባቢ ነዋሪዎችና በኢትዮጵያም ቆንስላ ተፅዕኖ በድጋሚ ወህኒ ቤት ውስጥ ባለች አንድ ክፍል ውስጥ ዳኞች ተሰይመው ለፍርድ ቢቀርብም፣ እንደገና በሞት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት ገልጿል፡፡ በሶማሊያ ሞት የተፈረደበት የሚገደለው ከጠዋቱ 11 ሰዓት ላይ ሲሆን፣ ከሦስት ወራት በፊት አንድ ቀን እሱንም ከእስር ቤት አስወጥተውት ሊገድሉት ይመጣሉ፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ‹‹አስመሮም ልትገደል ነውና የምትናዘዘው ካለህ እዚህ ላይ ጻፍና ፈርም፤ ይኼው መኪናና ሽማግሌዎች ቀርበዋል፤ በቀብር ቦታም ሌሎች ሽማግሌዎች እየጠበቁ ነው ፍጠን፤›› እንዳለው ይናገራል፡፡

‹‹ትንሽ አሰብኩ፤ ተስፋ የለኝም፤ ቆም ብዬ ሳስብ ሶማሌ የገንዘብ ነገር እንደማይሆንለት ተገነዘብኩ፤ ከዚያም አዛዡን አንድ ነገር ተባበረኝ አልኩት፤ ከአንድ ሐበሻ ዘንድ ከ15 እስከ 20 ሺሕ ዶላር ስላለኝ ተቀበልና ለቤተሰቦቼ ላክልኝ አልኩት፡፡ እሽ ምን ልርዳህ አለኝ፡፡ ሞባይል ስጠኝ አልኩት፤ ቦሳሶ ወደሚኖርና የእኔን ጉዳይ ለሚከታተል ጓደኛዬ ደውዬ የሆነውን ሁሉ ነገርኩት፤›› የሚለው አስመሮም፣ ጓደኛው ተሯሩጦ በፑንትላንድ ለኢትዮጵያ ተወካዮች በመናገሩ፣ የአገሩ መንግሥት ግድያው እንዲቆም በማዘዙ መትረፉን አብራርቷል፡፡

የፈጣሪ ኃይል ስላለበት በሚስጥር ሊገድሉት የነበረውን ሴራ ሁሉ አልፎ እስሩ የፑንትላንድ ኃላፊዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ መቀየሩን፣ ኃላፊዎችና ሀብታሞች ከሚበሉበት ዋሚ ከሚባል ሆቴል  በቀን ለቁርስ፣ ለምሳና ለእራት የ30 ዶላር ምግብ እየታዘዘለት ሲመገብ ቆይቶ፣ መጨረሻ ላይ የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም መለቀቁንና ለአገሩ መብቃቱን በደስታ ገልጾልናል፡፡

‹‹ስለ ቴዲ አፍሮ የምናገርበት አንደበት የለኝም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያመስግንልኝ፤ እኔ ደሃና አቅም የሌለኝ ወንድሙን ስላዳነ፣ እግዚአብሔር ደግሞ ለእሱ የሚያደርግለትን ሁሉ አብዝቶ ያድርግለት፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካንን፣ በፑንትላንድ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ኮሎኔል አስመላሽ ወልደ ምህረትና ባልደረቦቻቸው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ላደረገልኝ ነገር በሙሉ እግዚአብሔር ያክብራችሁ፤›› በማለት አስመሮም ያለውን አክብሮት ገልጿል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/