Wednesday, September 28, 2011

በቤይሩት አውሮፕላን አደጋ ምርመራ የኢትዮጵያና የሊባኖስ ባለሥልጣናት ቅራኔ ከሯል


 ‹‹አውሮፕላኑ ከመውደቁ በፊት ቡርቱካናማ ፍንዳታ ተመልክተናል›› የራፊቅ ሃሪሪ ኤርፖርት የበረራ ተቆጣጣሪዎች
-    የሊባኖስ ባለሥልጣናት የተጠየቁዋቸውን መረጃዎች አሁንም አላቀረቡም
-     አሜሪካኖች የምርመራውን ሒደት ችላ ብለውታል

በጥር 2002 ዓ.ም. በሊባኖስ ዋና ከተማ በቤይሩት አቅራቢያ ድንገተኛ አደጋ በደረሰበት የኢትዮጵያ አየር አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ በሚካሄደው የአደጋ ምርመራ፣ በኢትዮጵያና በሊባኖስ ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየከረረ መጥቷል፡፡

በቅርቡ በቤይሩት ራፊቅ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የሊባኖስ የሥራና ትራንስፖርት ሚኒስትሩ ጋዚ  አሪዲ የምርመራው ሒደት እንደተጠናቀቀ በመግለጽ፣ የአደጋ ምርመራ ሪፖርቱ ለሚመለከታቸው ወገኖች እንደሚላክ የገለጹ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን  ባለሥልጣን የምርመራው ሒደት እንዳልተጠናቀቀ እየገለጹ ነው፡፡ በነሐሴ ወር ከመርማሪው ቡድን ጋር ቴክኒካዊ ስብሰባ ለማካሄድ ወደ ቤይሩት ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናት እየተከተሉት ባለው አካሄድ  አዝኖ እንደተመለሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጥር 2003 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የሊባኖስ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናትና ቦይንግ ኩባንያ ምርመራው በምን አኳኋን መቀጠል እንዳለበትና ማንኛውንም ለምርመራው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ የቦይንግና የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የአደጋ መርማሪ ቡድኑ አባላት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የጠየቁዋቸው መረጃዎች በሙሉ የተሰጡዋቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎችን፣ ቴክኒሽያኖችን፣ የበረራ ቁጥር 409 አብራሪዎች ጓደኞችን፣ ቤተሰቦችንና መምህራን በሙሉ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትምህርት ቤት የአሠለጣጠን ዘዴዎችንና በአጠቃላይ የአየር መንገዱን እንቅስቃሴ መርምረው ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ነሐሴ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. በቤይሩት ለሚካሄደው የቴክኒክ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአውሮፕላን አደጋ መከላከያና ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ሻምበል ግርማ ገብሬና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ክፍል ኃላፊ ካፒቴን ደስታ ዘሩ ወደ ቤይሩት አቅንተው ነበር፡፡

ካፒቴን ደስታ ዘሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቡድኑ ወደ ቤይሩት ከመጓዙ በፊት አዲስ አበባ ላይ በጥር 2003 ዓ.ም. በተፈረመው የመረጃ ልውውጥ ስምምነት መሠረት፣ የኢትዮጵያ ልዑክ በተደጋጋሚ የጠየቃቸው መረጃዎች እንዲዘጋጁለት ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት የበረራ ቁጥር 409 ተሳፋሪዎች ፕሮፋይል፣ በራፊቅ ሃሪሪ አውሮፕላን ማረፊያ በደኅነነት ካሜራዎች የተቀረፁ ፊልሞች፣ በመንገደኞች ሻንጣ መፈተሺያ የተነሱ ፊልሞች፣ በበረራ መቆጣጠሪያ ማማ ውስጥ በሚገኝ መቅረፀ ድምፅ የተቀዱ በአብራሪዎችና በበረራ ቶቆጣጣሪዎች መካከል የተደረጉ ንግግሮችና የአስከሬን ምርመራ ውጤቶች እንዲሰጧቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፣ የሊባኖስ ባለሥልጣናት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ነሐሴ 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ወደ ቤይሩት የተጓዘው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ መሰብሰቢያው ክፍል ሲገባ ያገኘው የምርመራ ቡድኑን ኃላፊ ሊባኖሳዊውን ካፒቴን አዚዝን ብቻ እንደሆነ ካፒቴን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተቀሩት የመርማሪ ቡድኑ አባላት ለምን በስፍራው አልተገኙም  ብለን ላቀረብነው ጥያቄ የተሰጠን ምላሽ በቂ መረጃ ስላለን ነው ብለው ቀርተዋል የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡



የኢትዮጵያ ልዑክ እንዲቀርቡለት የጠየቃቸው መረጃዎች አንዳቸውም ባለመቅረባቸውና በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ ስብሰባውን መቀጠል እንደማይቻል ገልጾ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡ የሊባኖስ ትራንስፖርት ሚኒስትር ጋዚ አሪዲ እውነታውን ወደጎን በማለት የኢትዮጵያ ልዑክ ምንም ሳያሳውቃቸው ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ አድርገው መግለጻቸው እንዳሳዘናቸው ካፒቴን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ሚስተር አሪዲ ምርመራው የሚያተኩረው በነበረው የአየር ፀባይ፣ ቴክኒክ ወይም የደኅንነት ጉዳይ ላይ ሳይሆን በፓይለቱ ስህተት ላይ ብቻ እንደሆነ መግለጻቸው፣ እጅግ በጣም የሚያሳዝንና የሚያስተዛዝብ እንደሆነ ካፒቴን ደስታ ተናግረዋል፡፡

የሪፖርተር የዜና ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ በደረሰበት ወቅት ተረኛ የበረራ ተቆጣጣሪ የነበሩ ሁለት መኮንኖች ከአውሮፕላን ማረፊያው አራት ማይል ርቀት ላይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ወደ ባህር ከመውደቁ በፊት በአየር ላይ መፈንዳቱንና ድቡልቡል ቡርቱካናማ እሳት ተመልክተዋል፡፡ ሁለቱ ከ20 ዓመት በላይ ያገለገሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች አደጋውን እንደተመለከቱም የአደጋ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

መኰንኖቹ ወዲያውኑ ያሰፈሩት ዕለታዊ ሪፖርትም ‹‹አውሮፕላኑ ሲፈነዳና ወደ ቡርቱካናማ ድቡልቡል እሳትነት ሲለወጥ ተመልክተናል፡፡ ከዚያም ተበታትኖ ቁልቁል ወደ ባህር ወርዷል፤›› ይላል፡፡ ዕለታዊ ሪፖርቱ  የበረራ ተቆጣጣሪዎቹን ፎቶግራፍ፣ ስምና ፊርማ የያዘ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ መኰንኖች ከኢትዮጵያ ልዑክ ጋር እንዳይገናኙ መደረጉ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም አደጋው በደረሰበት ወቅት ወደ ቤይሩት ራፊቅ ሃሪሪ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ተቃርበው የነበሩ የኢትሃድና የኦሎምፒክ  አየር መንገዶች ንብረት የሆኑ አውሮፕላኖች ካፒቴኖች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመውደቁ በፊት የተከሰተውን ፍንዳታ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ በምድር ላይ ሆነው አደጋውን የተመለከቱ የዓይን እማኞችም ደብዛቸው እንዲጠፋ እንደተደረገ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

የቦይንግና የአሜሪካ መንግሥት ተወካዮች የአደጋውን ምርመራ ሒደት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችላ እንዳሉት የገለጹት ምንጮች፣ አሁን እየተደረገ ያለው የአደጋውን ትክክለኛ መንስዔ ለማወቅ ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት ጥቅምን የማስከበር ጉዳይ ሆኗል ብለዋል፡፡ ‹‹የሊባኖስ ባለሥልጣናት ፍንዳታ የሚለውን ቃል መስማት አይፈልጉም፡፡ ሂዝቦላህ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ የእኛን አባላት ለማጥፋት የተሰነዘረ ጥቃት ነው ይላል፡፡ አሜሪካኖችም ለመሸፈን የሚፈልጉት ጉዳይ አለ፡፡ በአጠቃላይ በአደጋው ምርመራ ሒደት ፖለቲካ ገብቶ እየበጠበጠ ይገኛል፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡

የሊባኖስ ባለሥልጣናት የምርመራው ሒደት ተጠናቋል ሲሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው መረጃዎች ተሟልተው አልተሰበሰቡም እያሉ ነው፡፡ በዚህም የሁለቱ ወገኖች ባለሥልጣናት ልዩነት እየሰፋ፣ ቅራኔውም እየከረረረ ይገኛል፡፡ የሊባኖስ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የመጨረሻ ረቂቅ ሪፖርቱን ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን፣ ለአሜሪካው ፌዴራል ኢቨዬሽን አድሚኒስትሬሽንና ለቦይንግ ኩባንያ መላኩ የሚታወስ ሲሆን፣ ሪፖርቱን ተመልክተው በ60 ቀናት ውስጥ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋን የምርመራ ሒደት ችላ እንዳሉት እንደማስረጃ የሚቀርበው፣ በነሐሴ ወር በተካሄደው የቴክኒክ ስብሰባ ላይ አንዳቸውም አለመገኘታቸው ነው፡፡ ‹‹አውሮፕላኑ አሜሪካ ሠራሽ እንደመሆኑ ጉዳዩ ቦይንግን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ መንግሥትን ይመለከተዋል፡፡ እስከ መጨረሻውም በምርመራው ሒደት ሊሳተፍ ይገባ ነበር፡፡ አሁን እንዳየነው ከሆነ ግን አሜሪካኖቹ ከምርመራው ሒደት ራሳቸውን እያገለሉ ነው፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ሰዒድ ሃሪሪ ከሚመራው የሊባኖስ መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት እንዳለው አክለው ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ሚስጥራዊ ሰነዶችን በማውጣት የሚታወቀው ዊኪሊክስ የተባለው ድረ ገጽ ይፋ ባደረገው ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋን በተመለከተ በሊባኖስ የአሜሪካ አምባሳደር ሚሼል ሲሰን ለመንግሥታቸው በላኩት ሚስጥራዊ መልዕክት የዓይን እማኞች አውሮፕላኑ በአየር ላይ ጋይቶ ወደ ድቡልቡል እሳትነት ሲቀየር መመልከታቸውን እንደተናገሩ አስነብቧል፡፡ ሚስጥራዊው ሪፖርቱ የሊባኖስ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት የተምታቱና የሐሰት መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸውን አጋልጧል፡፡

የአደጋ ምርመራ ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት የሊባኖስ ሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክተር ጄኔራል  ሃምዲ ቻውክ፣ ከዚህ በፊት በአደጋ ምርመራ ምንም ዓይነት ልምድ እንደሌላቸው ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ የሊባኖስ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሚስተር አሪዲ አደጋው  በደረሰ ማግስት፣ አደጋው የደረሰው በፓይለቶቹ ስህተት እንደሆነ መናገራቸው አግባብ እንዳልሆነ የቦይንግና የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ ተወካዮች መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡

የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሚስተር ጃዋድ ካሊፋ፣ ‹‹በአደጋው ሰለባ ከሆኑ ግለሰቦች አስከሬን ለመረዳት እንደተቻለው አውሮፕላኑ አየር ላይ ፈንድቷል፤›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን መናገራቸውን አምባሳደር ሲሰን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ ሚስተር ጆንስ የተባለ የቦይንግ ከፍተኛ ኤክስፐርት የምርመራ ሪፖርቱ መደምደሚያ የአብራሪዎች ስህተት በሚል እንደሆነ እንደገለጸላቸው አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡ ኤክሰፐርቱ ይህን የተናገረው አደጋው ከደረሰ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ‹‹አንድ የአውሮፕላን አደጋ በደረሰ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ገና መረጃዎች ባለመሰባሰባቸው የሚስተር ጆንስ ቀደም ብሎ የተሰጠ አስተያየት በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን፣ የአደጋውን መንስዔ የአብራሪዎቹ ስህተት ነው ብሎ ለመደምደም የተጠነሰሰ ሴራ እንደነበር የሚጠቁም ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የነበረው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ በደረሰው የመከስከስ አደጋ የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ጨምሮ 90 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ 

No comments:

Post a Comment