Wednesday, September 21, 2011

የገንዘብ ሚኒስትሩ በቦሌ መንገድ ግንባታ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሊያሳልፉ ነው


የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ፣ ከቦሌ ድልድይ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ በሚደርሰው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በአነስተኛ ወለድ በተገኘው 60 ሚሊዮን ዶላር ይገነባል ተብሎ የታቀደው 4.5 ኪሎ ሜትር መንገድ ከአራት ዓመት በፊት ይገነባል ቢባልም፣ በእስካሁኑ ሒደት የተለያዩ መሰናክሎች ገጥመውት ሳይካሄድ ቆይቷል፡፡

ከነዚህ መሰናክሎች መካከል ተጠቃሽ የሚሆኑት የጨረታው ውጤት መሰረዝና በግንባታ ዋጋ ውድነት ምክንያት በድጋሚ እንዲጤን መወሰኑ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ መንገዱ የሚገነባው በብድር እንደመሆኑ መጠን ከአራት ወራት በፊት ለብድር ውሳኔ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ለአንድ ኪሎ ሜትር 12.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዋጋው ውድነት ስላልተዋጠላቸው፣ በድጋሚ የፕሮጀክቱ ዋጋ እንዲጤን በማዘዛቸው ፕሮጀክቱ በተወሰነለት ጊዜ ሳይካሄድ ቆይቷል፡፡
የፕሮጀክቱን ዋጋ በሚመለከት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር እንዲነጋገር ምክር ቤቱ መወሰኑን ተከትሎ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ከባለሥልጣኑ ጋር ዋጋው በምን ምክንያት ሊወደድ እንደቻለ ማብራርያ ሲቀበል ቆይቷል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ካቀረበው የተለየ ሐሳብ ለሚኒስቴሩ ባያቀርብም፣ ይህንን በዝርዝር የተመለከቱት አቶ ሱፊያን በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱን ማስጀመር የሚያስችል ውሳኔ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አፍሪካ ጐዳና በመባል ለሚታወቀው መተላለፊያ አዲስ የሚገነባው መንገድ 40 ሜትር ስፋትና ሦስት የመተላለፊያ ድልድዮች ይኖሩታል፡፡ መተላለፊያዎቹ የሚገነቡት ሩዋንዳ ኤምባሲ መታጠፊያ፣ ወሎ ሰፈርና ኦሊምፒያ አካባቢዎች ላይ ነው፡፡ ዲዛይኑን ኢንጂነር ዘውዴ እስክንድር ናቸው የሠሩት፡፡

ባለሥልጣኑ ከአራት ዓመታት በፊት ይህንን መንገድ ለመሥራት ያወጣውን ጨረታ ያሸነፈው እንይ ኮንስትራክሽን ሲሆን፣ በወቅቱ ከተማውን የሚያስተዳድረው የባለአደራ አስተዳደር ፕሮጀክቱን ለእንይ ኮንስትራክሽን እንዲሰጥ ወስኖ ነበር፡፡ ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ከተማዋን የተረከበው በአቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው አስተዳደር እንይ ኮንስትራክሽን ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ለማካሄድ የአቅም ውስንነት አለበት በሚል ነጥቆታል፡፡ ግንባታውንም የቻይናው ሲአርቢሲ እንዲያከናውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የአቶ ሱፊያንን ውሳኔ ካገኘ ባለሥልጣኑ በ2004 ዓ.ም. ከሚያስገነባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ እንደሚሆን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com