Sunday, September 18, 2011

የሆስቴሷ ሁለት ዓይኖች በቀድሞ ባለቤቷ በስለት ተወግተው ጠፉ


ሪፖርተር ጋዜጣ)
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የበረራ አስተናጋጅ (ሆስቴስ) የሆነችውን የወ/ሮ አበራሽ ኃይላይን ዓይኖቿን በስለት ወግቶ በማጥፋት የተጠረጠረውና ባለቤቷ የነበረ ግለሰብ፣ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ሌሊት እጁን ለፖሊስ መስጠቱን ቤተሰቦቿ አስታወቁ፡፡
ቤተሰቦቿ እንዳስታወቁት፣ ወ/ሮ አበራሽ ተከራይታ በምትኖርበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ፣ ፍስሐ ታደሰ የተባለው ተጠርጣሪ፣ ሁለቱንም ዓይኖቿን በስለት ወግቶ ካጠፋ በኋላ እጁን ለፖሊስ በመስጠቱ ፖሊስ ደርሶ ወደ ሆስፒታል ወስዷታል፡፡

በቤቷ ውስጥ ራሷን ስታና ብዙ ደም ፈሷት የተገኘችውን ተጐጂ ፖሊስ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ቢወስዳትም፣ ጉዳቱ ከሆስፒታሉ አቅም በላይ በመሆኑ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በሪፈር መሄዷን አጐቷ አቶ አስመላሽ ሞላ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መስከረም 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የሄደችው ወ/ሮ አበራሽ፣ አንድ ዓይኗ ሙሉ በሙሉ በመፍሰሱ ተጠርጐ ከመውጣቱ ውጭ ማትረፍ አለመቻሉን አቶ አስመላሽ አስታውቀዋል፡፡

ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ያነጋገራቸውና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያ እንዳረጋገጡት፣ የወ/ሮ አበራሽ ዓይኖች በከፍተኛ ሁኔታ በስለት ተወግተው ወደ ውጭ የወጡ መሆኑን ጠቁመው፣ አንደኛው መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ተጠርጐ መውጣቱንና ሁለተኛውም ተስፋ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው ዓይኗ ሙሉ በሙሉ ተጐልጉሎ ባለመውጣቱና ባለበት ሆኖ የፈሰሰ በመሆኑ፣ ምናልባት በዘመናዊ መሣርያና የሐኪም ዕርዳታ የሚተርፍ ከሆነ በሚል መስከረም 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ወደ ባንኮክ መብረሯን አቶ አስመላሽ ገልጸዋል፡፡



መስከረም 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በሪፈር ወደ ቤተዛታ ጠቅላላ ሆስፒታል የተዛወረችው ወ/ሮ አበራሽ፣ እስከ ምሽት ድረስ በአይሲዩ ውስጥ የዋለች ሲሆን፣ ጊዜያዊ ክትትል ሲያደርጉላት የነበሩ የሆስፒታሉ ዶክተር አንድ ዓይኗ ጉዳቱ ከፍተኛ ቢሆንም የመትረፍ ዕድል ሊኖረው እንደሚችል ተስፋ መስጠታቸውን፣ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ያገኘናቸው በርካታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጆችና ቤተሰቦቿ ገልጸዋል፡፡

በተጠርጣሪው አቶ ፍስሐ ታደሰና በዋና የበረራ አስተናጋጇ ወ/ሮ አበራሽ መካከል ስለነበረው ግንኙነት እንዲያስረዱን የጠየቅናቸው አጐቷ አቶ አስመላሽ እንደገለጹት፣ ድርጊቱ እስከፈተጸመ ድረስ ሁለቱም በፍቅር ኖረዋል፡፡ ሕጋዊ ጋብቻ ፈጽመው ከሰባት ዓመታት በላይ አብረው በፍቅርና በመተሳሰብ ቢኖሩም፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን ልጅ አልወለዱም፡፡ ሁለቱ በመነጋገርና በመስማማት ከአራት ወራት በፊት ትዳራቸውን በሰላም በፍርድ ቤት አፍርሰዋል፡፡ ላለፉት ወራትም በተለያዩ ቤቶች ቢኖሩም እሷም በእሱ ቤት፣ እሱም በሷ ቤት በመሄድና በመተሳሰብ በፍቅር ነበሩ፡፡

መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. እሷ በረራ ስለነበረባት ሁለቱም በእሳቸው ቤት መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ተገኝተው ግብዣ እንዳደረጉላቸው የገለጹት አቶ አስመላሽ፣ በሰላም ተሰነባብተው ከሄዱ በኋላ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሁለቱንም ዓይኗን በመኖርያ ቤቷ ውስጥ በስለት ጨቅጭቆ ማጥፋቱ መራር ሐዘን እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የእሷን ዓይን ብቻ ሳይሆን ያጠፋው የመላ ቤተሰቧን ዓይን ነው፤›› ያሉት አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ይኼንን ድርጊት ያየ፣ የሰማና የሚያውቃት፣ መንግሥትም፣ የአገሪቱ ሕዝብና የዓለም ሕዝብ ይፍረደን፤›› ሲሉ እያለቀሱ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ ባህል ታይቶ የማይታወቅ በሴቶች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጸመ የሚታየው ጭካኔ የተሞላበትና ነውረኛ ድርጊትን፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊያስብበት እንደሚገባና ወንጀሉን በሚፈጽሙት ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አቶ አስመላሽ አሳስበዋል፡፡

ወ/ሮ አበራሽ ኃይላይ በትግራይ ክፍለ አገር ውቅሮ ከተማ ከተወለደች በኋላ፣ በሕፃንነቷ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ እንዳደገች የገለጹት አጐቷ፣ ከ11 ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ እያለች በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት መቀጠሯን ጠቁመዋል፡፡

አሜሪካ አገርም ለሁለት ዓመታት ኖራ ተመልሳ በበረራ አስተናጋጅነት እየሠራች እንደምትገኝና ቤተሰቦቿንም የምትረዳውና የምታስተዳድረው እሷ መሆኗንም አጐቷ ተናግረዋል፡፡

ዋና የበረራ አስተናጋጇን ወ/ሮ አበራሽ ኃይላይን ዓይን አጥፋቷል በሚል የተጠረጠረውን አቶ ፍስሐ ታደሰን በሚመለከት ጉዳዩን እየተከታተለ ያለውን፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር አሥራት ገመዳ መግለጫ እንዲሰጡን በቢሮአቸው ተገኝተን ብንጠይቃቸውም፤ ‹‹ገና በምርመራ ላይ ነን፤ ጉዳዩ አልተጠናቀቀም፤ ምን ያደርግላችኋል?›› በማለት ሊነግሩን አልቻሉም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጳጉሜን 4 ቀን 2003 ዓ.ም. አንድ ተጠርጣሪ ከቡና ቤት ወደ ቤቱ የወሰዳትን ሴተኛ አዳሪ በስለት በመውጋት ጉዳት እንዳደረሰባት ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ስሟ ቢገለጽ በሕይወቷ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በመናገር እንዳይገለጽባት የጠየቀችውና ያነጋገርናት ተጐጂ፣ አቶ ከድር ሻፊ የተባለ ግለሰብ ቦሌ አካባቢ ከሚገኘው ፒያኖ ባር ጳጉሜን 3 ቀን ለ4 አጥቢያ 2003 ዓ.ም. ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 በሚገኘው መኖርያ ቤቱ ይዟት እንደሄደ ተናግራለች፡፡

መኖርያ ቤቱ እንደደረሱ ያለኮንዶም ግንኙነት እንዲያደርጉ ሲጠይቃት ባለመስማማቷ፣ ጭንቅላቷን በጠርሙስ መትቶ በስለት ግራ እጇንና ቀኝ እግሯን ሲቆርጣት፣ ‹‹ከመሞት ይሻላል›› በማለት ያለኮንዶም ግንኙነት ማድረጓን ገልጻለች፡፡

አንድ ሺሕ ብርና ወርቅ እንደወሰደባት የገለጸችው ተጐጂዋ፣ ለሰዓታት ደሟ ሲፈስ ቆይቶ፣ ተጠርጣሪው እንቅልፍ ሲወስደው እርቃኗን በመስኮት ዘላ በመውጣት የድረሱልኝ ጥሪ በማሰማቷ፣ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ደርሰውና የሚለበስ ልብስ ሰጥተው ፖሊስ በመጥራት ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስረድታለች፡፡

በእጇና በእግሯ ላይ በደረሰባት ጉዳት ሕክምና ለማግኘት በአካባቢው ወደሚገኘው ጤና ጣቢያ ቢወስዷትም፣ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ወደ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ተወስዳ ሕክምና ከተደረገላትና አንድ ቀን ከቆየች በኋላ ወደ ቤቷ መመለሷን ገልጻለች፡፡

የአንድ ልጅ እናት መሆኗንና የምትሠራው ሥራ በማጣቷ ልጇን ለማሳደግ ስትል በቡና ቤት ሥራ ላይ መሰማራቷን የገለጸችው ተጐጂዋ፣ መንግሥት ጉዳት ባደረሰባት ተጠርጣሪ ላይ ተገቢ የሆነ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቃለች፡፡

ተጠርጣሪው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀበት ታውቋል፡፡

ፖሊስ ስለጉዳዩ ማብራርያ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም፣ ‹‹ምርምራ ስላልጨረስኩ መረጃ መስጠት አልችልም፤›› በማለቱ አልተሳካልንም፡

No comments:

Post a Comment