Wednesday, July 13, 2011

Ethiojazz



የመጀመርያው የጃዝ እና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅልቅል (Fusion) በሙላቱ አስታጥቄ ተቀናብሮ አርባ ዓመታትን ቢያስቆጥርም አሁን የደረሰበትን ደረጃና ለውጥ ላይ ለመድረስ የቻለው ግን በዚህ አስር ዓመት ውስጥ ነው ፡፡  ለለውጡ አስተዋጽኦ አድርገዋል ከሚባሉ ሰዎችም የጃዝ አባት ተብሎ የሚጠራው ሙላቱ አስታጥቄ አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ የመጀመርያው ኤፍ ኤም 97.1 በተከፈተበት ሰሞንም ወደማታው “ይህ የአፍሪካ ጃዝ መንደር ድምፅ ነበር፡፡ የሚል ጐርነን ያለ ድምፅ ይሰማ ነበር፡፡ ያም ድምፅ የሙላቱ አስታጥቄ ነው ይሄ ፕሮግራም እንደሚታወሰው ስለ ጃዝ ሙዚቃ ምንነት ለአድማጮች በጥልቅ ያስረዳ ነበር፡፡

ከዚያም ኮፊ ሐውስን ጨምሮ የጃዝንና የጃዝና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅልቅል የሚባለውን የሚያጫውቱ ክለቦች እንዲሁም የሚጫወቱ ባንዶች መምጣት ጀመሩ፡፡

በዚህ አስር ዓመት ውስጥ ከተማ ውስጥ ያለው የጃዝ ሁኔታ በሚታይበት ሰዓት ብዙ ባንዶች ለመፈጠር ችለዋል፡፡ ለመጥቀስም ያህል መለከት፣ ጃዝማሪስ፣ አዲስ አኩስቲክስ፣አርባን ቫይብስ ይጠቀሳሉ፡፡

በጥንታዊት ኢትዮጵያ መለከት በጦርነት ጊዜ፣ በበዓላትና አዳዲስ ነገሮችን ለማወጅ የሚጠቀሙበት መሣርያ ነው፡፡

በቦሌ ሮክ ዓርብ የሚጫወተው መለከት ባንድም ይሄ የሙዚቃ መሣርያ ስም የባንዱን ሁኔታ እንደሚገልጸው ይናገራሉ፡፡ እንደ ሙዚቃ መሣርያው መለከት የኢትዮጵያን የደቡብ ሙዚቃ ለማሳወቅ የተመሰረተው ባንድ ሲሆን ከዓመት በፊት ደግሞ ግጥምን ከጃዝ ጋር አዋሕዶ እየሠራ ነው፡፡  ባንዱ መጀመርያ ሲመሠረት ሦስት አባላት የነበሩት ሲሆን አሁን ግን ስድስት ደርሰዋል፡፡ እነሱም ግሩም ግዛው (ሊድ ጊታር)፣ መብራቱ ሸዋ (ቤዝ ጊታር)፣ ዮናስ ይማም (ድራም)፣ አብይ ወልደማርያም (ኪ-ቦርድ) እና ዮናስ ጐርፌ (ፐርከሽን) ይጫወታሉ፡፡

መጀመርያ ባንዱ ሙዚቃ ሲጀምር ስታንዳርድ ጃዝ የሚባለውን ይጫወቱ ነበር፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያን የዱሮ ሙዚቃና የደቡብ ሙዚቃ እንዲሁም የራሳቸው ቅንብር ተጨመረበት፡፡

በተለያዩ በዓላት ጊዜ ይሁን በዕለት ተዕለት ኑሮዋቸው ውስጥ የሚዘፈኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን እያመጡ ከጃዝ ጋር አዋሕዶው አዲስ ድምፅ ፈጥሮ በመጫወትም ይታወቃሉ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ሙዚቃ በደንብ አልታወቀም ብለው የባንዱ አባላት የሚያምኑ ሲሆን፣ ያንንም ለመለወጥ የተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ሙዚቃ መሣርያዎችንና ዜማዎችን ከጃዝ ጋር ለማስተዋወቅ ሞክረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌላ አዲስ ፕሮጀክት የጀመሩት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር  በከተማው ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሲያዩ ግጥምንና ሙዚቃን አንድ ላይ የሚጫወት ምንም ባንድ እንደሌለ ስለተረዱ ግጥምና ሙዚቃን አንድ ላይ በማምጣት አዲስ ነገር ለማስተዋወቅ ወሰኑ፡፡

መጀመርያ ሲጀምሩት ተቀባይነት ስለማግኘቱ ጉዳይ ጥርጣሬ የነበረባቸው ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን የሰውን መውደድ ሲያዩ ያ ጥርጣሬአቸው ሙሉ በሙሉ ተወግዶላቸዋል፡፡ 

የመጀመርያዎቹ ፕሮግራሞች ላይ ከገጣሚ ቸርነት ወልደ ገብርኤል ጋር በመጣመር ሠርተዋል፡፡

አብይ ወልደማርያም እንደሚናገረው፣ ይሄ የሁለቱ ጥምረት የሚፈጥረው ሙዚቃ አዲስና ለየት ያለ ሙዚቃ ነው፡፡

ባንዱ ከዋናው ፕሮግራም በፊት ከገጣሚዎቹ ጋር ልምምድ የሚያደርግ ሲሆን፣ ለግጥሙ የሚሆን ሙዚቃም ያቀናብራል፡፡ እሱ እንደሚናገረውም፣ “ግጥሙን እንድንለምደውና ግጥሙን በሙዚቃ ስንት ቦታ መከፋፈል እንዳለብን እናጠናለን፡፡ የት ቦታ ማቀዝቀዝ እንዳለብን፣ መሀል ላይ ያለውን ክፍተት በሙሉ እንዴት ከሙዚቃው ጋር አብሮ መሔድ እንዳለበት በአጠቃላይ ከግጥሙ ጋር አብረን እንዴት መሔድ እንዳለብን እናጠናለን፡፡”

ሙዚቃው የግጥሙን መንፈስ ማንፀባረቅ ስላለበት የግጥሙን ይዘት ተከትለው አንዳንዴ የራሳቸውን ሙዚቃ እያቀናበሩ ሌላ ጊዜ ደግሞ የቆዩ ሙዚቃዎችን በማሻሻል ከግጥሙ ጋር በሚሔድ መልኩ ይቀናበራል፡፡ መጀመርያ ላይ ሲጀምሩት አዲስ ነገር ስለሆነ ላይወደድ ይችላል ብለው ፈርተው የነበረ ቢሆንም፣ ከዓመት በኋላ ግን የተመልካቹ ቁጥር መጨመር እንዳስደሰታቸው አልበደቁም፡፡

“በጣም ከጠበቅኩት በላይ ነው፤ በከተማችን ውስጥ ግጥም የሚወድ ሰው ብዙ ነው፡፡ የጃዝም እንዲሁ፡፡ ሁለቱንም አንድ ላይ ስናመጣው ሰው ሊቀበለው ችሏል፡፡” በማለት አብይ ይገልጻል፡፡ ባንዱ በየሳምንቱ አንድ ቀን ዓርብ ጃዝ ይጫወታል፡፡ ግጥሙ የየሳምንቱ ፕሮግራም ባይሆንም በየመሀሉ አንድ ወይም ሁለት ግጥሞች ጣል ያደርጋሉ፡፡ በሁለት ሳምንት አንዴ ደግሞ በዛ ያሉ ግጥሞች የፕሮግራሙ አካል ናቸው፡፡

በየሦስት ወሩ ደግሞ ለግጥሙ ለየት ያለ ዝግጅት ያለ ሲሆን፣ ከተማ ውስጥ አሉ የሚባሉ ገጣሚዎች እንደነ አበባው፣ ደምሰው ዝግጅታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ዝግጅቶች በሚያቀርቡበት ጊዜም ግጥሙን ከሙዚቃ ጋር በመቀላቀል ይጫወታሉ፡፡  

http://www.ethiopianreporter.com/life-art-culture.html

No comments:

Post a Comment