ታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ተቋረጠ
መነሻው የሳያት ደምሴ የአትላንታ ኮንሰርት ነው፡፡
የሰራንው ነገር ይቅርታ የሚያስጠይቅ አይደለም-አዘጋጆቹ
(አዲስ አድማስ) በሸገር ኤፍአም 102.1 በሳምንት አምስት ቀናት የሚተላለፈው ታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ተቋረጠ፡፡የፕሮግራሙ መቋረጥ ሰበብ ሳያት ደምሴ በአሜሪካ አትላንታ ባቀረበችው ኮንሰርት ላይ ያጋጠማትን ሁኔታ የሚዘግበው ዜና ነው ተብሏል፡፡ሳያት በአትላንታው ኮንሰርት ከአዲሱ አልበሟ የተጫወተችው ዘፈን በቴፕ ሆኖ እሷ ማይም እያደረገች መዝፈኗን የተረዳው ተመልካች ተቃውሞውን በመግለፅ ጩኸት እና ሁካታ ማሰማቱን በስፍራው ከነበረው የታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ሰይፍ ፋንታሁን በደረሳቸው መረጃ መሰረት የፕሮግራሙ አዘጋጆች ባለፈው ማክሰኞ ዘግበዋል፡፡ይህንኑ ዘገባ ተከትሎም የሳያት ደምሴ ቤተሰቦች ዜናው የሳያትን ወገን ያላካተተና የአንድ ወገን እይታ ብቻ መሰረት ያደረገ መሆኑን በመግለፅ አዘጋጆቹ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቋቸው የሬዲዮ ጣቢያውን እንደጠየቁ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ይገልፃሉ፡፡ዘገባው በትክክል የተሰራና ሚዛናዊ እንደሆነ የሚናገሩት አዘጋጆቹ ይቅርታ ልንጠይቅበት የሚያስችለን ምንም ጉዳይ የለም ብለዋል፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጅ ተወልደ በየነ(ተቦርነ) ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው ዜናው ትክክለኛ እና በመረጃ የተደገፈ ሆኖ ሳለ ይቅርታ እንድንጠይቅበት መደረጉ አግባብነት እንደሌለው በተደጋጋሚ ብንናገርም ከእኛ ፍላጎት እና እውቅና ውጪ በሬዲዮ ጣቢያው ስም በአበበ ባልቻ ይቅርታ እንዲነበብ ተደርጓል ብሏል፡፡ይቅርታው በቀን ሁለት ጊዜ በተከታታይ ለአምስት ቀናት እንዲተላለፍና በየቀኑ ከይቅርታው በኋላ የሳያት ደምሴ ዘፈን እዲለቀቅ መደረጉን መቃወማቸውን የገለፀው ተወልደ(ተቦርነ) ይቅርታው ህጋዊ ስርአትን ያልተከተለና አግባብነት የሌለው በመሆኑ እንቃወመዋለን ሲል ተናግሯል፡፡በዕለቱ በዘገባው ሌሎች አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ዘፋኞች የሳያት የተለየ ሆኖ ይቅርታ ሊያስጠይቅ የሚችልበት ምክንያት አለመኖሩን ተናግሯል፡፡የሸገር ኤፍአም 102.1 ሬዲዮፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ አለሙን ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው ጣቢያው የስራ ውሉን የፈፀመው ከታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ሰይፉ ፋንታሁን ጋር መሆኑን ጠቁመው ስለጉዳዩ ሃላፊነት ያለበት እና የፕሮግራሙን መቋረጥ አስመልክተው የሚያነጋግሩት እሱኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ጣቢያው በሳያት ደምሴ ላይ ተሰራ በተባለው ዘገባ ድምፃዊቷ ይቅርታ መጠየቅ አለባት ብሎ በማመኑ በይፋ ይቅርታ መጠየቁን የተናገሩት አቶ ተፈሪ ሁኔታው የሰይፉ ፋንታሁንን ቅጥር ሰራተኞች ቅር አሰኝቶ ፕሮግራሙን እስከ ማቋረጥ ሊያደርሳቸው ይችላል የሚል እምነት አልነበረኝም ብለዋል፡፡ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው እና በመጪው ማክሰኞ አዲስ አበባ ከሚገባው የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ሰይፉ ፋንታሁን ጋር በመነጋገር በቅርቡ ለጉዳዩ እልባት እንደሚሠጡት ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ተው ባክህ
ReplyDelete