Tuesday, August 21, 2012

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ Haile Mariam Desalegne named acting Prime Minister


የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈተ ሕይወት አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በሙሉ ሥልጣን አገሪቱን እንደሚመሩ አስታወቀ፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን በሒልተን ሆቴል ዛሬ ማለዳ በሰጡት መግለጫ፣ አቶ ኃይለ ማርያም በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አገሪቱን ይመራሉ ብለው፣ በሚቀጥለው መስከረም መጨረሻ የሚሰበሰበው ፓርላማ የሚቀጥለውን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚያስፈጽም ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ ምክር ቤት መቋቋሙንም አቶ በረከት አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ትናንት ከምሽቱ 5፡40 ላይ ማረፋቸውን የገለጸ ሲሆን፣ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ስለ ሕመማቸውና አማሟታቸው ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አመራር የወጡት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጸው መንግሥት፣ የአቶ ኃይለ ማርያምን ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አረጋግጧል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እስኪፈጸም ድረስ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታውጇል፡፡ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማም ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ አቶ በረከት አስታውቀዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment