ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. በገበያ ላይ እንዳይውልና እንዳይሠራጭ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታገደው፣ እስካሁንም ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ሕትመቱ የተቋረጠው የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ታሰረ፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን እንዲታሰር ትዕዛዝ የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ ዋና አዘጋጁ በፍትሕ ጋዜጣ ላይ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም.፣ የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም.፣ ሐምሌ 22 ቀን 2003 ዓ.ም. እና መጋቢት 7 ቀን 2004 ዓ.ም. የተዘገቡ መጣጥፎችን ተከትሎ የፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ በመሠረተበት ሦስት ክሶች ዋስትና በመከልከሉ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ክሱን ለማየት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ለነሐሴ 9 ቀን 2003 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ ዳኛው ባለመገኘታቸው በጽሕፈት ቤት ሠራተኞች አማካይነት ለዛሬ ተላልፎ ነበር፡፡ ዛሬ በቀጠሮው መሠረት ፍርድ ቤት ተሰይሞ ክሱን ለችሎቱና ለተከሳሹ ካሰማ በኋላ፣ በክሱ ላይ ዋና አዘጋጁ አስተያየቱን እንዲሰጥ ሲጠየቅ፣ በጠበቃው አማካይነት የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለት ጠይቆ ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ ግን ባቀረበው መቃወሚያ ተከሳሹ የተመሠረተበት ክስ ከፍተኛ የሆነ ተጠያቂነትን የሚያስከትልበት መሆኑን በመጥቀስ፣ ከአገር ሊወጣ እንደሚችልና ሊቀርብ እንደማይችል በመናገር ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም አስተያየት ካደመጠ በኋላ የጋዜጠኛ ተመስገንን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ በማረሚያ ቤት ቆይቶ ነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. ለውሳኔ ቀጥሮታል፡፡ በጋዜጣው አሳታሚ ድርጅት ላይ ስለቀረበው ክስ ፍርድ ቤቱ ያለው ነገር የለም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment