“ኢትዮ-ምኅዳር” ለሚባለው ሣምንታዊ ጋዜጣ ከአማራ ክልል ሲዘግብ የቆየው ሙሉቀን ተስፋሁን በቤንሻንጉል-ጉምዝ ፖሊስ መያዙን የጋዜጣው ምንጮች አስታወቁ።
ስለጋዜጠኛው እሥራት ከአካባቢው ፖሊስ መልስ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሣካም።
ሙሉቀን ከተያዘበት ዕለት ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት እንዳልቀረበም የቅርብ ዘመዶቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት “የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት
የመቅረብ መብት አላቸው” ሲል በአንቀፅ 19 ንዑስ አንቀፅ 3፤ “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሣቡን
የመግለፅ ነፃነት አለው፤ ይህ ነፃነት በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሁፍ
ወይም በሕትመት፣ በሥነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንሃውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሣብ
የመሰብሰብ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል” ሲል በአንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 2 ያረጋግጣል፡፡ እንዲሁም
በአንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 3 እና ንዑስ አንቀፅ 3/ለ የሚከተለው ሠፍሯል “3. … የፕሬስ ነፃነት የሚከተሉትን
ሕጎች ያጠቃልላል…፤ …ለ/ የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን”
ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋሁን ዓርብ ግንቦት 16/2005 ዓ.ም ጀምሮ በቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል ዶቢ በምትባል የገጠር
መንደር ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ መቆየቱንና እስከዛሬም ማክሰኞ ግንቦት 20/2005 ዓ.ም ፍርድ ቤት አለመቅረቡን ቅርበት
ያላቸውና ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጮች ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡
በዶቢ ቀበሌ እሥር ቤት ውስጥ ሣለ ሙሉቀንን ባለቤቱና ወንድሙ ሄደው የጎበኙት ሲሆን ማክሰኞ፣ ግንቦት 20/2005
ዓ.ም ጠዋት ግልገል በለስ በተባለ ሥፍራ ወደሚገኘው የዞኑ እሥር ቤት መወሰዱን ምንጩ ጠቁመዋል፡፡
ሙሉቀን ለላከው “ኢትዮ-ምኅዳር” ጋዜጣ መረጃ በመሰብሰብ ላይ እያለ ፖሊሶቹ ጋዜጠኛ ለመሆኑ ማስረጃ እንዲያቀርብ
ጠይቀውት ማሣየቱንና “በፖለቲካ ነው የምንፈልግህ” ብለው እንደወሰዱት፤ በአካባቢው የነበሩት ሰዎች “ለምን
ትወስዱታላችሁ?” ብለው ሲጠይቁም “እናንተንም እናስራችኋለን” ብለው ያስፈራሯቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
http://amharic.voanews.com
No comments:
Post a Comment