Wednesday, May 22, 2013

በኑሮ መንገድ ላይ፥ ዮናታን እና ሜሮን




ሁሉም ሰው አሸናፊ መሆን ፤በህይወቱ ውስጥ ከሚፈልገው አላማ መድረስ ይችላል? አይቻልም፡፡አንድ ሰው በህይወቱ ካሰበበት ለመድረስ ህልም እና ፍላጎቱን ለማሳካት በርካታ ውጣውረዶችን ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡የስኬታማነት/ውጤታማነት አንዱ ቁልፍ ደግሞ ቁርጠኝነት (Determination) ነው፡፡  ቁርጠኝነት ስኬት አይደለም፡፡የስኬታማነት ሂደት እንጂ፡፡

በእሸቴ በቀለ

ቁርጠኝነት ላይ ለዳጉ አዲስ  ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም የሰራሁትን እና  በሸገር 102.1 የተላለፈውን ፕሮግራም እዚህ ማዳመጥ ይችላሉ፡፡
 


የሜሮን  ‘’ፍለጋ’’
አባቷ በነበረባቸው የፍርድ ቤት ጉዳይ እጅጉን ሲማረሩ ታስታውሳለች፡፡ይህን ችግር መፍታት የሚያስችላትን የጥብቅና ሙያ ማለም የቻለችው የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ቤተሰቦቿ ጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪ ሆና ስትመደብ ‘’ተይው’’ ብለዋት ነበር፡፡እርሷም የማታውቀውን ዩኒቨርሲቲ ርቀት አስባ ፍርሃት ፍርሃት ሳይላት አልቀረም፡፡ወስና የዩኒቨርሲቲውን የህግ ተማሪዎች ተቀላቀለች፡፡ግን ህይወት ቀላል አልሆነችም፡፡የትምህርት አሰጣጡ አዲስ ነበር፤ሙቀቱ ከባድ ነው፤ምግቡ አልተመቻትም ፡፡በዚያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብ ለራቀችው ራሄል አጥር አልባው ዩኒቨርሲቲ ያስፈራል፡፡ዩኒቨርሲቲው ውስጥም ሆነ ውጪ ለከፋ ገጥሟታል፡፡የመጀመሪው አመት በእንዲህ አይነት በርካታ መሰናክሎች የተሞላ ነበር፡፡ቢሆንም አልተሸነፈችም፡፡እንዲያውም አካባቢዋን ወደ ሚስደስታት እና አላማዋን ለማሳካት ወደሚያግዛት አለም መቀየር ጀመረች፡፡የሴቶች ክበብ አቋቋመች፡፡በትምህርታቸው ደካማ የነበሩ ተማሪዎችን እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያሻቸውን ማገዝ ጀመረች፡፡ስትመረቅ ውጤቷ ጥሩ ነበር፡፡ሜሮን ከኮሌጅ ህይወት በኋላ በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢንዱስትሪ ግንኙነት ኦፊሰርነት ለ3 ወር ሰርታለች፡፡ቢሆንም ቢሮክራሲው እና የተማረችው ሳይጣጣምላት ቀርቶ ጥላ ወጣች፡፡ቀጣይ ማረፊያዋ ቪኤስኦ የተሰኘ የግብረ ሰናይ ድርጅት ነበር-በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፡፡ሜሮን ከአላማዋ ለመድረስ ባደረገችው ጥረት የገጠሟት ችግሮች ነበሩ፡፡ቤተሰቦቿ ቋሚ ደሞዝ ከሚከፈላት ተቋም ለቃ ስትወጣ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስትጀምር ደስተኛ አልነበሩም፡፡ነገር ግን ማሳመን ችላለች፡፡

አሁን የሜሮን አለም ሰፍቷል፡፡ቀድሞ ባለመችው እና በተማረችው የህግ ሙያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ለመሆን ትመኛለች፡፡ፍለጋዋን ቀጥላለች፡፡ሜሮን ካሰበችበት ለመድረስ አሁንም ጠንክራ መስራት ይኖርባታል፡፡ቁርጠኝነት ለስኬታማነት መንገድ ይሁን እንጂ በራሱ ደስታ አለው፡፡በአንዳች ጉዳይ ላይ ስኬታማ ለመሆን በምናደርገው ጥረት የህይወት ክህሎታችን ይዳብራል፤ስብዕናችን ይበለፅጋል፡፡በራሳችን ህይወት ውስጥ ለምንወስናቸው ውሳኔዎች ሃላፊነት መውሰድ ከስህተት መማር እና ከውድቀት መነሳት እንችላለን፡፡ከፀፀት እንገላገላለን፡፡
በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ቆራጥ መሆን ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ሲጀመር አባት እና እናት ቤተሰብ እና ማህበረሰብ በልጅነታችን ፍላጎታችንን ይወስናሉ፡፡የመምረጥ ነፃነታችንን ተነጥቀናል፡፡እንደ ቀላል ‘’ልጄ ሲያድግ ዶክተር…ኢንጂነር….ፓይለት…ሳይንቲስት ይሆናል’’ ብለው የእነሱን ፍላጎት በልጆች ልቦና ይቀርፃሉ፡፡ያ ልጅ የተመረጠለትን ወይም የተፈለገለትን መሆን ባይፈልግ እንኳ ‘’አሻፈረኝ’’ የማለት መብት  የራሱን ፍላጎት የማወቅ እና የመምረጥ  ነፃነት እንዳለው የሚያውቅበት እድል የለውም፡፡በዶክተርነት፤አንጂነርነት፤ፓይለትነት፤ ሳይንቲስትነት እየተቀጠቀጠ ያድጋል፡፡ትምህርት ቤት እና ጓደኝነትም የራን ፍለጋ እድልን አያበረታቱም፡፡
አንድ ልጅ ቤተሰብ የመረጠለትን ወይም እድለኛ ከሆነ በራሱ ምርጫ መሆን የሚፈልገውን ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርበታል? በአግባቡ መማር;ማጥናት;…ይህ የተማሪ ሃላፊነት ነው፡፡ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት የቁርጠኝነት አንዱ መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡የተለያዩ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ቆራጥ ለመሆን በህይወት ውስጥ ሊደረጉ ይገባቸዋል የሚሏቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች ይዘረዝራሉ፡፡ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
·         በራስ መተማመን
·         በህይወት ውስጥ ማሳካት የምንፈልገውን ግብ ለይቶ ማወቅ
·         ጊዜን በአግባቡ መጠቀም
·         በመረጥንው ግብ ላይ መፅናት
·         ግባችንን ለማሳካት የሚረዱንን መንገዶች መርጦ መለየት
·         በሂደት ውስጥ ለሚገጥሙ ችግሮች እጅ አለመስጠት፤ለችግሮቹ መፍትሄ መፍጠር እችላለሁ ብሎ ማመን
·         ግልፅ እና የሰዎችን አስተያየት ለመቀበል ዝግጆ መሆን ቢሆንም ከሰዎች የሚመጡ የተጋነኑ ማበረታቻዎች እና ምስጋናዎች ወይም ትችቶች እና ነቀፌታዎችን በእርጋታ መመርመር
የጀመርንውን ለመጨረስ ከምንወደው ከሚያስደስተን እና ስኬታማ ከምንሆንበት ለመድረስ ጥንካሬ ያስፈልጋል፡፡መንገዱ ግን ሁልጊዜም ቢሆን አልጋ ባልጋ አይደለም፡፡

የዮናታን ዓለም
ጫት በጣም ተወደደ፡፡ዮናታን በቀን 80 ብር ለጫት መክፈሉ እጅጉን ያንገበግበዋል፡፡ቀደም ሲል ሩብ ጫት በ3 ብር ይገዛ እንደነበር ያስታውሳል፡፡አሁን በህይወቱ እጅጉን ከሚያሳስቡት ጉዳዮች አንዱ የጫት መወደድ ነው፡፡ጫት፤ሲጋራ እና መጠጥ የዮናታን እና ጓደኞቹ የአለም መለኪያ ናቸው፡፡ጠዋት ጫት ማታ መጠጥ፡፡መሽቶ ሲነጋ የሚቀየር ነገር የለም፡፡ዮናታን አምባሳደር አካባቢ መኪና በማጠብ ይተዳደራል፡፡ ‘’ደስተኛ ነኝ ‘’ሲል ይናገራል፡፡ዮናታን ህልሙ ሌላ ነበር፡፡መካኒክ መሆን የሚመኝ ኢንጂነሪንግ መማር የሚፈልግ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ከቤት ተባረረ፡፡ ‘’አንዳንድ ነገሮች አጠፋለሁ፡፡ከቤት ይዤ እወጣና እሸጣለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ ከአባቴ ጋር ተጣልቼ ወጣሁ በዚያ የተነሳ ትምህርቴ ተቋረጠ፡፡’’ ሲል ያስታውሳል፡፡
የዮናታን ህይወት ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም፡፡ዶክተር፤ኢንጂነር፤ሰዓሊ፤የሚዚቃ ባለሙያ…መሆንን እየተመኙ ካሰቡበት ያልደረሱ በርካታ ወጣቶች አሉ፡፡ህልማቸውን፤ፍላጎታቸውን የህይወት ግባቸውን ማሳካት ያቃታቸው ኢትዮጵያውያን፡፡ መውደቅ መሸነፍ፤እጅ መስጠት እንደ ሃገር ተጠናውቶናል፡፡አስተማሪ አባት ኢንጂነሪንግ፤የህክምና ባለሙያነት፤ተመራማሪነት ወይም ከፍ ያለ የተሻለ ሙያን ለልጁ ይመኛል፡፡ቤተሰብ የግል ፍላጎቱን በልጁ ልቦና ይቀርፃል፡፡የልጁ ፍላጎት፤ተሰጥኦ፤ችሎታ አይጠየቅም፡፡ልጁም በህፃንነት ልቦናው የተቀረፀ ቤተሰባዊ ግብን ያነበንባል፡፡ጥቂቶች የቤተሰባቸውን ተልዕኮ አሳክተው ዚያ ሙያ ባለቤቶች ይሆናሉ፡፡እጅግ በጣም ጥቂቶች የተጫነባቸውን አሻፈረኝ ብለው የሚፈልጉትን ለመሆን ይታትራሉ፡፡በርካቶች የተሰጣቸውንም ሆነ የሚፈልጉትን መሆን ሳይችሉ በመብከንከን ውስጥ ህይወታቸውን ያሳልፋሉ፡፡

No comments:

Post a Comment