Monday, March 24, 2014

የግብፅ ኩባንያ በኢትዮጵያ ትልቁን የወርቅ ክምችት አገኘአስኮም ማይንኒግ የተባለው የግብፅ ኩባንያ በኢትዮጵያ ታሪክ እስከዛሬ ከተገኘው የላቀ የወርቅ ክምችት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አገኘ፡፡

የተገኘው የፅንስ ወርቅ ክምችት በኢትዮጵያ የወርቅ ፍለጋ ታሪክ ከተገኙ የወርቅ ክምችቶች በሙሉ ይበልጣል ተብሏል፡፡

በቅርቡ ከተደረሰባቸው የወርቅ ክምችቶች መካከል በቱሉ ካፒ ወለጋ ኒዮታ ሚኒራልስ የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ፣ በመተከል ሳካሮ በሚድሮክ ጐልድ በኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች በናሽናል ማይኒንግ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ስትራቴክስ በተባለው የእንግሊዙ ኩባንያ፣ በትግራይ ክልል በኢዛና ማይንኒግ የተገኙት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የግብፅ ኩባንያ አስኮም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያገኘው የወርቅ ክምችት በእነዚህ ኩባንያዎች ከተገኙት ክምችቶች ሁሉ እንደሚበልጥ ተገልጿል፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስኮም ያገኘው የወርቅ ክምችት እስከዛሬ ከተገኙ ክምችቶች ሁሉ የላቀ ነው፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ለማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች ስላገኙት ግኝት ከሁለት ሳምንት በፊት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ኩባንያው ባካሄደው የወርቅ ፍለጋ ሥራና ባገኘው ውጤት የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች መደሰታቸውን አቶ ቶሎሳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እስከዛሬ ስናወራ የነበረው ስለ 30 እና 40 ቶን የወርቅ ግኝት ነበር፡፡ አስኮም ያገኘው ከዚያ በእጅጉ የሚበልጥ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የግብፁ ያገኘው የወርቅ ክምችት መጠን በትክክል ምን ያህል እንደሆነ በአኃዝ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ የአስኮም ኃላፊዎች ከሁለት ሳምንት በኋላ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡


አስኮም ማይኒንግ በቀጣይነት የአዋጭነት ጥናት የሚያካሂድ መሆኑን፣ የአዋጭነት ጥናቱን ከሠራ በኋላ ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ደረጃ የወርቅ ማምረት ፈቃድ እንደሚሰጠው አቶ ቶሎሳ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማምረት እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

በሚድሮክ ኢትዮጵያ ሥር ከሚተዳደሩት በርካታ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ናሽናል ማይኒንግ ኩባንያ በኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ባገኛቸው የወርቅ ክምችቶች ያካሄደውን የአዋጭነት ጥናት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያውና ሚኒስቴሩ የጥናቱን ውጤቶች በቅርቡ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኒዮታ ሚኒራልስ በቱሉ ካፒ ባገኘው የወርቅ ክምችት ላይ የአዋጭነት ጥናት አካሂዷል፡፡ ጥናቱ ከተሠራ በኋላ የወርቅ ዋጋ በማሽቆልቆሉ እንደገና ጥናቱን ለመከለስ ተገዷል፡፡ በዚህም ምክንያት ኩባንያው በአሁኑ ወቅት የተሻሻለ ጥናቱን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አቶ ቶሎሳ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከማዕድናት ኤክስፖርት በዓመት ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የምታገኝ ሲሆን፣ 90 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣው ወርቅ ነው፡፡ ወርቅ በአሁኑ ወቅት ከቡና ቀጥሎ ትልቁ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምርት ሆኗል፡፡ በየጊዜው ተጨማሪ የወርቅ ክምችቶች መገኘታቸውን የጠቆሙት ጂኦሎጂስቶች፣ ወርቅ የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com