Monday, March 17, 2014

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ለቀቁዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት ምሳሌ ይሆናል የተባለውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩትን ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅንን ተክተው ሲሠሩ የቆዩት አቶ አንተነህ አሰፋ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡

ምንጮች እንደጠቆሙት አቶ አንተነህ ከኃላፊነት የለቀቁት አሜሪካ ሆነው ባመለከቱት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ሲሆን፣ የምርት ገበያው ቦርድ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡

በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ ሊቀመንበርነት የሚመራው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቦርድ የሥራ መልቀቂያውን ተቀብሎ ውሳኔ የሰጠው፣ ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. መሆኑን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

አቶ አንተነህ ሥራቸውን ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ ያደረሳቸው የጤና ችግር መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በልብ ሕመም ምክንያት በአገር ውስጥ በሕክምና ላይ እንደነበሩና አነስተኛ ቀዶ ጥገና ተደርጐላቸው እንደነበር ታውቋል፡፡


በዚህ ምክንያት ለከፍተኛ ሕክምና አሜሪካ የሄዱት አቶ አንተነህ፣ ሕክምናውን እዚያው በቅርብ እንዲከታተሉ በመወሰኑ ሥራቸውን ለመልቀቅ እንደተገደዱ እየተነገረ ነው፡፡ ወደ አሜሪካም ሲጓዙ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው እንደሆነም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በሥራ ገበታቸው ላይ ሳይገኙ ከሁለት ወራት በላይ የቆዩት አቶ አንተነህ፣ ይመለሳሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ጊዜ የሥራ መልቀቂያ መላካቸው ያልተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡

አቶ አንተነህ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሙሉ የምርት ገበያውን ኃላፊነት ተረክበው መምራት ከመጀመራቸው ቀደም ብሎ፣ ከነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. እስከ መስከረም 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ዕጩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተብለው ከዶ/ር እሌኒ ጋር በጋራ ሲሠሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መስከረም 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ደግሞ ዶ/ር እሌኒ ኃላፊነቱን ተረክበው ምርት ገበያውን ሲመሩ ነበር፡፡

የ40 ዓመቱ ጐልማሳ አቶ አንተነህ ወደ ምርት ገበያው ከመምጣታቸው በፊት፣ የአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በሥራ ዓለም ከ15 ዓመታት በላይ ልምድ አላቸው፡፡

ዶ/ር እሌኒ ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁ ካስታወቁ በኋላ እርሳቸውን ሊተኩ ይችላሉ ተብለው ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል የተሻለ ውጤት በማምጣት አቶ አንተነህ መመደባቸው ይታወሳል፡፡ ዶ/ር እሌኒም ‹‹በትክክል የሚተካኝ አቶ አንተነህ ነው፤›› በማለት ብቃት ያላቸውና  ለቦታውም የሚመጥኑ መሆናቸውን መስክረውላቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

አቶ አንተነህ ለሕክምና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው አሜሪካ ሲሄዱ እስኪመለሱ ድረስ የምርት ገበያው የኮምፕሊያንስ ኦፊሰር አቶ ሽመልስ ሀብተ ወልድ በውክልና እየመሩ ነበሩ፡፡

አሁንም አቶ አንተነህን ወክለው እየሠሩ ያሉት አቶ ሽመልስ፣ የአቶ አንተነህን ከኃላፊነት መልቀቅ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምንም ዓይነት አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡
http://ethiopianreporter.com