Sunday, June 10, 2012

በኃይሌ ገብረ ሥላሴ ላይ የተመሠረተው ክስ እንዲቋረጥ ተደረገ“ክሱ የተመሠረተው ያላግባብ ስለሆነ መከሰስ አልነበረበትም” የየካ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ላይ መሥርቶት የነበረውን “በሕገወጥ መንገድ መብትን የማስከበር ወንጀል” ክስ፣ “የማጣራው ነገር ስላለኝ ክሴን አቋርጫለሁ” በማለት ግንቦት 29 ቀን 2004 ዓ.ም አቋረጠ፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክሱን መሥርቶ የነበረው ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አካባቢ በሚገኘው የአትሌት ኃይሌ ሕንፃ ላይ ተከራይ በነበሩት “አዲስ የመኪና ሻጭና አከራይ” ባለቤት የአቶ አዲስ ደገፋን ቢሮ፣ በሕገወጥ መንገድ ቁልፉን በመቀየርና በቢሮው ውስጥ የነበረውን ንብረት በመጋዘን ውስጥ በማስቀመጡ ነበር፡፡

ኃይል ለፖሊስ በሰጠው ቃል ድርጊቱን በማመኑ ክሱ ሊመሠረት ቢችልም፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ከመመሥረቱ በፊት ወይም ተጐጂው ለፖሊስ ሲያመለክቱ ቤቱን የተከራዩበትን ውል አያይዘው ማቅረብ ሲገባቸው፣ ሳያያይዙ በማቅረባቸው ባልተሟላ ማስረጃ ክሱን መመሥረቱን የየካ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ፀጋ ተናግረዋል፡፡ አትሌት ኃይሌ ክሱ ከመቋረጡ ቀደም ብሎ ግንቦት 28 ቀን 2004 ዓ.ም ጉዳዩን እየመረመረው ለሚገኘው ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት መቃወሚያ አቅርቧል፡፡ኃይሌ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያሰናዳበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 436 (ሐ) ተፈጸመ ከተባለው የወንጀል ድርጊት ጋር የማይገናኝና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፣ የግል ተበዳይ የተባሉት አቶ አዲስ ደገፋ በፈረሙት የኪራይ ውል ግዴታ እንደገቡና በወቅቱ ኪራይ ካልከፈሉ ዕቃቸው በእዳ እንደሚያዝና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በመጥቀስ ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ መቃወሚያው ሳይነበብ “የሚቀረኝ ምርመራ አለ” በማለት ቀድሞ ክሱ በመቋረጡ መቃወሚያው ሳይሰማ ቀርቷል፡፡

ክሱ እንደ ተቋረጠ ኃይሌን አነጋግረነው፣ “ክሱ እንደሚቋረጥ ቀድመን እናውቀው ነበር፤ ማንኛውንም ዓይነት ሥራ የምንሠራው ሕጉን ጠብቀን ነው፡፡ በግብታዊነት አንሠራም፤ ሩጫ እንኳን የሚሮጠው በመስመር ነው፤ ማንም በማንም ላይ መሮጥ አይችልም እንኳን ሕግን ያህል ነገር፤›› በማለት የደረሰበት ስም ማጥፋት ከባድ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ውድድር የሚያደርግበት ጊዜ ላይ በመሆኑ ብዙ ነገር እንደ ደረሰበት ገልጾ፣ “ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፤” ያለው ኃይሌ፣ ለክሱ ዋና ምክንያት የሆነው እሱ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ የሰጠው ቃልና ከሳሽ ነጥሎ ያቀረበው ያልተሟላ ሰነድ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ሙሉ ሰነድ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ ይኼ ሁሉ ችግር በእሱ ላይ እንደማይደርስ የገለጸው ኃይሌ፣ ከሳሹ የፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቶባቸው 92 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ሲወሰንባቸው፣ ባለመክፈላቸው ክፍያውን ታስረው እንዲፈጽሙ በፍርድ ቤት የተላለፈው ትዕዛዝ ግን እንዳልተዘገበ ገልጿል፡፡

ባልተሟላ ሰነድ ክስ ስለተመሠረተበት እስከ ፍትሕ ሚኒስቴር ድረስ አቤቱታ ማቅረቡን የገለጸው ኃይሌ፣ ዓቃቤ ሕጉም ክሱን ያቋረጠው ያልተሟላ ሰነድ ስለያዘ መሆኑን አስረድቷል፡፡

“በኃይሌ ላይ ክስ የተመሠረተው አላግባብ ነው፤ መከሰስ አልነበረበትም፤” ያሉት የየካ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ፀጋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ  “ኃይሌ በር ማሸጉንና ግለሰቡ ተከራይ መሆናቸውን ባመነበት ሁኔታ በክሱ ላይ መሠረታዊ ስህተት አለ ብዬ አላምንም፤” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የአከራይ ተከራይ ውል ከክሱ ጋር ባለመያያዙና ተከራይ በውሉ ላይ መፈረም አለመፈረሙ ስላልተጣራ፣ ክሱ እንዲቋረጥ ያዘዙት እሳቸው መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ “የኪራይ ውሉን የሕግ ሰው ያዘጋጀው አይመስልም፤ ትላልቅ የንግድ ሥራዎችንና ድርጅቶችን ከሚያንቀሳቅስ ሰው እንደዚህ ዓይነት ውል አይጠበቅም፡፡ ውሉ መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፤” ብለዋል፡፡

አትሌት ኃይሌና በደል ተፈጽሞብኛል የሚሉት አቶ አዲስ ደገፉ፣ ከትናንት በስቲያ ረፋዱ ላይ በየካ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ተገናኝተው፣ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ አደራድረው አስማምተዋቸዋል፡፡

ሁለቱ ግለሰቦች ከስምምነት ላይ የደረሱት አትሌት ኃይሌ አቶ አዲስን “በወቅቱ የቤት ኪራይ አልከፈሉኝም” በማለት የፍትሐ ብሔር ክስ መሥርቶ ያስወሰነባቸውን 92 ሺሕ ብር በመተው ነው፡፡ ከ92 ሺሕ ብሩ ላይ ለመንግሥት የሚከፈለውን 30 በመቶ የታክስ ክፍያ ግን አቶ አዲስ እንዲከፍሉ ተብሏል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ አቶ አዲስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ግንቦት 28 ቀን 2004 ዓ.ም ያቀረቡት ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበር አቶ አዲስ ገልጸዋል፡፡ ስለተስማሙ ይግባኙንም መተዋቸውን አስረድተዋል፡፡

ሁለቱም ወገኖች ካሁን በኋላ መካሰሱን መተዋቸውን ሲገልጹ፣ አትሌት ኃይሌም በመጋዘን ቆልፎበት የነበረውን የአቶ አዲስን ንብረት ለማስረከብ ተስማምቷል፡፡

አትሌት ኃይሌና አቶ አዲስን ለክስ ያበቃቸው ጉዳይ ሁለቱ ወገኖች ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የተፈረመ የኪራይ ውል ህዳር 22 ቀን 2002 ዓ.ም. በ6,900 ብር (15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ጨምሮ) ተዋውለው እንደነበር ሰነዱ ይገልጻል፡፡ ከዓመት በኋላ መስከረም 7 ቀን 2003 ዓ.ም. በተጻፈ “ውል ማቋረጥ” የሚል ደብዳቤ በኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የፋይናንስ መምርያ ሥራ አስኪያጅ በአቶ ምንተስኖት ታደሰ ተፈርሞ ለአቶ አዲስ ይደርሳል፡፡

ደብዳቤው “ቢሮውን ለድርጅታችን ሥራ ስለምንፈልገው እ.ኤ.አ ከህዳር 1 ቀን 2010 ጀምሮ ውላችን የተቋረጠ መሆኑን አውቃችሁ ቅድመ ዝግጅት አድርጉ፤” የሚል ነው፡፡ አቶ አዲስ እንደማይለቁ በደብዳቤ ሲገልጹ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2003 ዓ.ም. ሁለተኛው ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡ የደብዳቤው ይዘትም፤ “… ያለንን ግንኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለድርጅታችን ሥራ የሚውል ተመሳሳይ (እሳቸው ከተከራዩት ክፍል ጋር) ቤት ተፈልጐ በተገኘው የኪራይ ዋጋ እንዲከራዩና የዋጋ ልዩነት ካለው አቶ አዲስ እንዲከፍሉ ብሎ የሚያትት ነው፡፡ በመሆኑም ተመሳሳይ የተባለውን ቤት ድርጅቱ በ50 ሺሕ ብር ማግኘቱንና አቶ አዲስም በውላቸው መሠረት እ.ኤ.አ ከታህሳስ 1 ቀን 2010 ጀምሮ 50 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ ውዝግቡ መጀመሩን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 430 (ሐ) በመተላለፍ በፍርድ ቤት ክርክር ያለውን ጉዳይ ውሳኔ ሳያገኝ በሕገወጥ መንገድ መብትን ለማስከበር በመሞከሩ በተመለከተ የወንጀል ክስ በዕለቱ ባለመቅረቡ፣ ታስሮ እንዲቀርብ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የየካ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ማዘዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
www.ethiopianreporter.com