Saturday, June 2, 2012

በፍርድ ቤት የተረቱት ግለሰብ ከሳሻቸውን በሽጉጥ ገደሉ


ከሰባት ዓመታት በላይ በወሰደው የፍርድ ቤት ክርክር ገንዘብ ማጭበርበራቸው ተረጋግጦ ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰብ ከሳሻቸውን በሽጉጥ ገደሉ፡፡ የሟች ቤተሰቦች ተደጋጋሚ ዛቻ ሲደርስባቸው እንደነበር ለፖሊስ ቢያመለክቱም ፖሊስ ዕርምጃ አለመውሰዱን ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ብርሃኑ ቦጋለ በፍርድ ቤት ክርክር የረታቸውን አቶ ኑርሁሴን አህመድን የገደሉት ባለፈው ሐሙስ አዳማ ከተማ ወደሚገኘው ዳሸን ባንክ ለፍርድ አፈጻጸም በሄዱበት ወቅት ነው፡፡ ምንጮቻችን እንደገለጹት፣ ተጠርጣሪው ግለሰብ አቶ ኑርሁሴንን ዳሸን ባንክ በር ላይ በሽጉጥ ሆዱን ተኩሰው ከመቱ በኋላ መኪና ውስጥ ገብተው ሊያመልጡ ሲሉ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር ሊያዙ ችለዋል፡፡ በሽጉጥ የተመቱት አቶ ኑርሁሴንም በሁለትና በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ሟች አቶ ኑርሁሴንና አቶ ብርሃኑ ከሰባት ዓመት በፊት አብረው ይሠሩ ነበር፡፡ የጥራጥሬ ላኪ ድርጅት ባለቤት የነበሩት አቶ ኑርሁሴን በአቶ ብርሃኑ መጋዘን ጥራጥሬ እየገዙ ያከማቻሉ፡፡ ለአቶ ብርሃኑም ገንዘብ እየሰጡ እህል እንዲገዙላቸው ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሲሠሩ በነበረበት ወቅት አቶ ብርሃኑ በመጋዘኑ ውስጥ የነበረውን እህል ለባንክ ቤት መያዣነት አቅርበው ብድር መውሰዳቸውን እነ አቶ ኑርሁሴን ሰሙ፡፡
መረጃው እንደደረሳቸው ወዲያውኑ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱና በመጋዘኑ የተከማቸው 11 ሺሕ ገደማ ኩንታል ቦሎቄ እንዲታገድ አደረጉ፡፡ ጥሬ ገንዘብን በሚመለከትም ለጊዜው የሰነድ ማረጋገጫን መሠረት በማድረግ ሦስት ሚሊዮን 400 ሺሕ ብር ለአቶ ብርሃኑ ሰጥተናል በሚል ክስ መሠረቱ፡፡

የአቶ ኑርሁሴን እህት ወ/ሮ ነፊሳ አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወንድማቸው የመሠረተውን ክስ ተከትሎ በመጋዘን ውስጥ የሚገኝ 11 ሺሕ ኩንታል ቦሎቄ ተቆጥሮ እህሉ እንዳይንቀሳቀስ ውሳኔ ቢተላለፍም፣ ተከሳሽ የፍርድ ቤትን ውሳኔ ወደ ጐን በመተው እህሉን እያወጡ ይሸጡ ነበር፡፡ ተከሳሽ አቶ ብርሃኑ በፍርድ ቤት የታገደውን እህል በመኪና አስጭነው ሲወስዱ ከአንድም ሁለት ጊዜ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ ነፊሳ፣ ‹‹የፍርድ ቤት እግድ አለበት›› በማለት ጉዳዩን ወደ አዳማ ፖሊስ ጣቢያ ቢያመለክቱም፣ ፖሊስ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት እህሉ ወደ መጋዘን ተመልሶ እንዲገባ ከማድረግ ይልቅ ለተሸጠለት ድርጅት ሲራገፍ ዝም ማለቱን ይናገራሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፣ ወንድማቸው የታገደው የመጋዘኑ እህል እንዳይወሰድ ለመከላከል በየቀኑ ለሁለት ፖሊሶች ሁለት ሁለት መቶ ብር እየከፈሉ ቢያስጠብቁም፣ እህሉ በተከሳሽ አቶ ብርሃኑ ከመወሰድ አልዳነም፡፡ በመጨረሻ በመጋዘኑ የቀረው 50 ኩንታል ቦሎቄ ብቻ ነበር ይላሉ፡፡

ጥሬ ገንዘብን በሚመለከት ሟች አቶ ኑርሁሴን የመሠረቱት ክስ ግን ረጅም ጊዜ ቢወስድም የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ለማግኘት ችሏል፡፡ ተጠርጣሪው አቶ ብርሃኑ ከከሳሽ አቶ ኑርሁሴን የተቀበሉትን ሦስት ሚሊዮን 400 ሺሕ ብር ከነወለዱ (ስድስት ሚሊዮን ብር ገደማ) እንዲከፍሉ ተወሰነባቸው፡፡ ተከሳሽ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢሉም ተመሳሳይ ውሳኔ ነው የተላለፈባቸው፡፡

ከሰባት ዓመታት መንገላታት በኋላ የተጭበረበሩት ገንዘብ እንዲመለስላቸው የተወሰነላቸው አቶ ኑርሁሴንም ሐሙስ ዕለት ፍርዱን ለማስፈጸም ዳሸን ባንክ ገብተው በሚወጡበት ጊዜ በተጠርጣሪው በተተኮሰ ጥይት ሆዳቸው ላይ ተመትተው ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

የሟች እህት ወ/ሮ ነፊሳ አህመድ እንደሚሉት፣ ተጠርጣሪው ግለሰብ ላለፉት ሰባት ዓመታት በቤተሰባቸው ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን በደል ለተመለከተ ሰው በአገሪቱ ውስጥ ሕግ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ተጠርጣሪው አቶ ብርሃኑ በየጊዜው ይፈጽሙት የነበረውን ዛቻና ሕገወጥ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ለአዳማ ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የክልሉ ባለሥልጣናት ጭምር ቢያመለክቱም፣ ግለሰቡ ያለምንም ከልካይ የፈለጉትን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቆሙት ወ/ሮ ነፊሳ፣ ተጠርጣሪው ግለሰብ መጋዘን ውስጥ በመግባት በሠራተኞች ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት ዕርምጃ ቢወሰድባቸውና ፖሊስ ጉዳዩን እየሸፋፈነ ከማስቀረት ይልቅ ወደ ፍርድ ቤት ቢመራው ኖሮ፣ ወንድማቸው እንደማይገደሉ በቁጭት ይናገራሉ፡፡

‹‹አገሪቱ ሕገወጥ ሰዎች እንደፈለጉ እያደረጉ የሚኖሩባት ነች፡፡ ሕግን መሠረት አድርገን በመንቀሳቀሳችን ለጥቃትና ለበደል ተዳርገናል፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት በእኛ ላይ የተፈጸመውን በደል ለተመለከተ ሰው በአገሪቱ ሕግ አለ ብሎ ለመናገር አይደፍርም፤›› በማለት ወ/ሮ ነፊሳ እንባ እየተናነቃቸው ምሬታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሟች አቶ ኑርሁሴን የሦስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ አቶ ኑርሁሴንን በመግደል የተጠረጠሩት አቶ ብርሃኑ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተረጋግጧል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com