Wednesday, November 16, 2011

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት 24 ተጠርጣሪዎች ክስ ሳይሰማ ቀረ


ከኤርትራ መንግሥት፣ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ የግንቦት 7 ድርጅት አመራርና አባል በመሆን፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚል 17 ገጽ ክስ የቀረበባቸውና በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 24 ተከሳሾች ክስ በትናንትናው ዕለት ሳይሰማ ቀረ፡፡ ክሱ ያልተሰማው ሀብትና ንብረት እንደሌላቸው ቃለ መሀላ በመፈጸም መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው የጠየቁት ተከሳሾች፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሽዋስ ይሁንዓለም፣ ምትኩ ዳምጤና አንዱዓለም አያሌው፣ ተከላካይ ጠበቃቸው መጥቶ እንዳላነጋገራቸው በመግለጻቸውና ተከሳሽ ክንፈ ሚካኤል ደበበ ጠበቃ ለማቆም ጊዜ ይሰጠኝ በማለቱ ነው፡፡

በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን በመከታተል ላይ ካሉት ስምንት ተከሳሾች መካከል፣ ክንፈ ሚካኤል ደበበን ‹‹አቅምህ ካልቻለ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምልህ ስትጠየቅ አልፈልግም ብለሀል፡፡ በራስህ አላቆምክም፤ ለምን?›› የሚል ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሲያቀርብለት፣ ‹‹ለሁለት ወራት ታስሬ ስቆይ አንድም ቀን ቤተሰቦቼን አግኝቼአቸው አላውቅም፡፡ ቤተሰቦቼን ያገኘኋቸው ማረሚያ ቤት ከተዛወርኩ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ [ኅዳር 2 ቀን 2004 ..] ነው፡፡ ጊዜው አጭር በመሆኑ ተመካክሬ ጠበቃ ለማቆም አልቻልኩም፡፡ የሰባት ቀን ጊዜ ቢሰጠኝ በግሌ ማቆም እችላለሁ፡፡ መንግሥት ራሱ ከሶኝ፣ ራሱ ጠበቃ አቁሞ ይከራከርልኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አልፈልግምም፤›› ብሏል፡፡

ዓቃቤ ሕግም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶና ሁሉም ተሟልቶ ክሱ እንዲሰማ እንዲታዘዝለት በማመልከቱ፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ለምን ጠበቆች እንዳልመደበ ቀርቦ እንዲያስረዳና ለቀጣይ ቀጠሮ እንዲመድብ፣ አቶ ክንፈ ሚካኤልም ጠበቃውን ይዞ እንዲቀርብ አሳስቦ፣ ክሱን ለመስማት ለኅዳር 13 ቀን 2004 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 30 ቀን 2004 .ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት፣ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ባቀረበው ክስ ውስጥ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሽዋስ ይሁንዓለም፣ ክንፈ ሚካኤል ደበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አያሌው በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እየተከታተሉ መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

አንዳርጋቸው ጽጌ፣ / ብርሃኑ ነጋ፣ ውቤ ሮቤ፣ ኤፍሬም ማዴቦ፣ መስፍን አማን፣ ዘለሌ ፀጋ፣ ፋሲል የኔዓለም፣ አበበ በለው፣ አበበ ገላው፣ ነአምን ዘለቀ፣ ኤልያስ ሞላ፣ ደሳለኝ አራጌ፣ ኮሎኔል አለበል አማረ፣ ኦባንግ ሜቶ፣ መስፍን ነጋሽና አብይ ተክለ ማርያም በሌሉበት የተከሰሱ መሆኑም ተዘግቧል፡፡

No comments:

Post a Comment