Wednesday, November 23, 2011

የሆስተሷ የቀድሞ ባለቤት ተከላካይ ምስክሮች መሰማት ጀመሩ ‹‹የእህቷ ፍቅረኛ ነበርኩ፤ ኤችአይቪ/ኤድስ በደሜ ውስጥ አለ›› ተጠርጣሪና ተከሳሽ ፍስሐ ታደሰ


የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችውን የቀድሞ ባለቤቱን ሁለት ዓይኖች አጥፍቷል በሚል ተጠርጥሮ ክስ ከተመሠረተበት በኋላ በተሰጠ ብይን፣ ‹‹ተከላከል›› የተባለው አቶ ፍስሐ ታደሰ፣ ተከላካይ ምስክሮቹን በትናንትናው ዕለት ማሰማት ጀመረ፡፡ ተከሳሹ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ካቀረባቸው የሰዎች ምስክሮች መካከል ሁለቱን እንደማይፈልጋቸው በጠበቆቹ አማካይነት ለፍርድ ቤቱ ካስታወቀ በኋላ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያልቀረቡ ሁለት ምስክሮች እንዳሉትና ከቀረቡት መካከል አንዱ የሚመሰክርበት ጭብጥ ከእነሱ ጋር ስለሚመሳሰል በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ተቃውሞ ተከሳሹ ተከላካይ ምስክሮቹን አንድ ላይ አቅርቦ ካላሰማ፣ በዕለቱ የምስክርነት ቃላቸውን የሚያሰሙት ላልቀረቡት ሊያስጠኑ ስለሚችሉ የጠበቃው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ሁሉም የሚሰሙበት ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ወገኖች ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ካልቀረቡት የተከላካይ ምስክሮች ጋር ተመሳሳይ ምስክርነት የሚሰጡት ምስክሮች በቀጣይ ቀጠሮ ቀርበው ከቀሪዎቹ ጋር መመስከር እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ጠበቆች ጭብጥ እንዲያስይዙና ተከሳሹ የተከሳሽነት ቃሉን እንዲሰጥ ፈቀደ፡፡

ተጠርጣሪና ተከሳሽ ፍስሐ ታደሰ ባቀረበው የተከሳሽነት ቃል እንደገለጸው፣ አበራሽና እሱ የሚተዋወቁት 1993 . ጀምሮ ነው፡፡ በወቅቱ የታላቅ እህቷ ፍቅረኛ ነበር፡፡ ታላቅ እህቷ በእሱ ስልክ ለአበራሽ ትደውልላታለች፡፡ በአጋጣሚ የእሱን ስልክ ያገኘችው አበራሽ መደወል ጀመረች፡፡ የእህቷ ፍቅረኛ መሆኑን ታውቃለች፡፡ ከመደዋወል አልፎ መገናኘትና መጨዋወት ጀመሩ፡፡ ግንኙነታቸው መስመሩን የለቀቀ እንዳይሆን በመፍራት ለመሸሽ ቢሞክርም፣ ሳይቻል ቀርቶ በድብቅ የፍቅር ግንኙነት ጀመሩ፡፡
ለእህቷም እንደምትወደውና ልታገባው እንደምትፈልግ ነግራት ግንኙነታቸውን በግልጽ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ከእህቷ በላይ የምትጨነቅለትና የምታስብለት በመሆኗ ልቡን በሙሉ ከፍቶ በውስጡ እንድትገባ ማድረጉን የገለጸው ተከሳሹ፣ የፍቅር ግንኙነት ከጀመሩ ከስድስት ወራት በኋላ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ቢጀምሩም፣ ቀደም ብሎ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ግንኙነት ያደርግ እንደነበር ስለሚያውቅ፣ በነፃነት ግንኙነት ለማድረግ ሁለቱም የኤችአይቪ/ኤድስ ምርመራ ለማድረግ መስማማታቸውን ተናግሯል፡፡

እሱ ቀድሞ ወደ ቤተዛታ በመሄድ ባደረገው ምርመራ ቫይረሱ እንዳለበት ሲነገረው፣ ለጊዜው እንደደነገጠና እንደተረበሸ የተናገረው ተከሳሹ፣ የቅርብ የሚለውን ጓደኛውን አማክሮት፣ ውጤቱን ለአበራሽ ማሳወቅ እንዳለበት ተነጋግረው እንደነገራት አስታውቋል፡፡ አበራሽም ራሷን እንድታውቅ መመርመር እንዳለባት ተማምነው ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል ሄዳ መመርመሯን የተናገረው ተጠርጣሪው፣ ውጤቷን እሱ እንዲቀበል ካደረገች በኋላ ውጤቱን የሚነግራት ማታ ተገናኝተው እራት ከበሉ በኋላ መሆኑን አስጠንቅቃው ወደ ሥራዋ ብትሄድም፣ ውጤቱን ሲመለከት ነጌቲቭ (ነፃ) በመሆኑ አላስችል ብሎት ቃሏን ሳይጠብቅ በስልክ እንደነገራት አብራርቷል፡፡ ውጤቱን ከነገራት በኋላ ምሽት ላይ ተገናኝተው እራት በልተውና መጠጥ ጠጥተው ፕላዛ ሆቴል አብረው ማደራቸውን የገለጸው ተከሳሹ፣ አብረው ቢተኙም የውጤቱ ጉዳይ የሁለቱንም ስሜት ከማቀዝቀዙም በላይ ከአልጋ ወርዶ ለብቻው ወለል ላይ ማደሩንም ተናግሯል፡፡

እንዳፅናናችውና እንደማትለየው ብትነግረውም ከእንግዲህ የእሱን ያልሆነን ገላ አቅፎ ማደር እንደሌለበት ነግሯት፣ ለሰባት ቀናት ያህል እንደጠፋባት ነገር ግን ከዕለታት አንድ ቀን ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ በማያውቀው ስልክ ሲደወል መጠጥ እየጠጣ ስለነበር ሲያነሳው፣ እሷ መሆኗንና ሳታገኘው ማደር እንደማትችል ነግራው መገናኘታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ለምን እንደጠፋ ስትጠይቀው ስላልተመቸው መሆኑን ቢገልጽላትም ልታምነው ባለመቻሏ፣ እውነቱን እንድታውቀው በማለት ሁልጊዜም እንደሚወዳትና እንደሚያፈቅራት፣ ነገር ግን በመካከላቸው በተፈጠረው ክስተት ራሱን ወዳድ መሆን እንደሌለበትና እርሷም ሌላ ሕይወት መጀመር እንዳለባት እንደነገራት ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

‹‹ፊሽ እኔ ያልተማርኩ መሐይም ወይም ሕፃን ልጅ አይደለሁም፤ ባይገርምህ አሰልችና ረጅም ዕድሜ ከመኖር አጭርና አስደሳች ጊዜ ከምወደው ሰው ጋር መኖር ምርጫዬ ነው፤›› እንዳለችው የተናገረው ተከሳሹ፣ በስሜትና እሱን ለመርዳት በማሰብ ወደፊት ሊፀፅታት የሚችል ውሳኔ መወሰን እንደሌለባት ቢነግራትም፣ ምንም የማይሽረው ፍቅር እንዳለባት በመግለጽ መለያየት እንደማትችል በመግለጿ አብረው መቀጠላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ግንኙነታቸውን እንደ አዲስ በመቀጠሉ መኪናውን ሸጦ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት እንዳስቀጠራት የገለጸው ተከሳሹ፣ እሱም የውጭ ንግዱ ስለተሳካለት መኪና ገዝቶ ስጦታ እንደሰጣትና ናዝሬት ድረስ ሄደው የቃል ኪዳን ቀለበት አድርጋለት አብረው መኖር መጀመራቸውን አብራርቷል፡፡

የእሷን ሕይወት ለመጠበቅ ከማሰብ አንጻር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲያደርጉ ኮንዶም እንደሚጠቀሙ፣ ለአራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ጋብቻቸውን በሕጋዊ መንገድ ማድረግ እንዳለባቸው ስትጠይቀው ገንዘብ እንደሌለው ቢነግራትም፣ ሙሉ ወጭውን ሚዜ ጭምር በመቻል የቀለበት ሥነ ሥርዓታቸውን መፈጸማቸውን ተናግሯል፡፡ ልጅ ስላልወለዱ አንድ ነገር ብሆን ብሎ ሁለት አክሲዮን እንደገዛላት፣ የተጀመረ ፎቅ በእሷና በእሱ ስም እንደገዛ የተናገረው ተከሳሹ፣ እሷን በማግባቱ ቀድሞ የወለዳቸው ልጆቹ የጎዳና ተዳዳሪ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት አብረው ሲኖሩ የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚም ቢሆን በፍቅር፣ በመተሳሰብና ያለምንም ግጭት መኖራቸውንና 2003 . አሜሪካ ለሽርሽር ሄደው እንደነበር የተናገረው ተከሳሹ፣ 2003 . ሚያዝያ ወር ገዳም ለፀሎት ሄዶ ባለበት ወቅት ስልክ ደውላለት ሲመጣ ቀለበቷን አውልቃ ‹‹እኔና አንተ አብረን ልንኖር አንችልም›› በማለት እንደወረወረችለት ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ቢለምናትና፣ ቢያስለምናት መፋታትን በመምረጧ ተስማምተው ፍርድ ቤት ሄደው በሰላም ፍች መፈጸማቸውን የገለጸው አቶ ፍስሐ፣ ከተለያዩ በኋላ በጣም በመታሙና በመጎዳቱ ወደ አዕምሮ ሐኪም መሄዱን፣ ታሞ ሆስፒታል መተኛቱንና በመቆየት እየተሻለው ሲመጣ፣ ተመሳሳይ ሕመም ያለባትን ሴት አግኝቶ ለማግባት በዝግጅት ላይ እያለ፣ አበራሽ ደውላለት እንደምትፈልገው ከገለጸችለት በኋላ ተገናኝተው ያለበትን ሁኔታ ቢነግራትም፣ መለየት እንደማትችል ነግራው እንደገና መገናኘት መጀመራቸውን አስረድቷል፡፡ ሁለተኛ ከተገናኙ በኋላ ሁለቱም ቅዱስ ገብርኤል ከፍተኛ ሆስፒታል ሄደው ሲመረመሩ ውጤቱ የመጀመሪያው በመሆኑ፣ ‹‹ተይኝ›› ብሎ ከተመሳሳዩ ጋር የነበረውን ግንኙነት መቀጠል ቢፈልግም፣ እምቢ ስላለችው መገናኘትና መጫወት፣ መብላት፣ አብረው መዝናናት ሲጀምሩ፣ አብረው በሚሆኑበት ጊዜ እሷም ሆነች እሱ ስልክ ቢደወልላቸው እንደማያነሱ ቃል የተግባቡ ቢሆንም፣ መስከረም 1 ቀን 2004 . እሱ ቤት እያሉ የማያውቀው ሰው ደውሎላት በማነጋገሯ ጭቅጭቅ መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡ 



ፍርድ ቤቱ በመሀል ገብቶ ከእሱ ጋር የማይገናኝ፣ ለመከላከል የማይጠቅም ስለሆነ ሊያስቆመው መሆኑን በመግለጽ ችግሩ ወደተፈጸመበት ዕለትና ጉዳይ እንዲገባ አዘዘ፡፡ መስከረም 2 ቀን 2004 . አጎቷ ቤት ምግብ በልተው እሷ ቤት ወይን መጠጣታቸውንና መጫወት ሲጀምሩ፣ አየር መንገድ መልቀቂያ ማስገባቷንና ወደ አሜሪካ እንደምትሄድ ስትነግረው፣ እሱም ዶላር እንደሚልክላት በመነጋገር ላይ እያሉ፣ የእርሳስ ሽጉጥ በማውጣት ‹‹ተነስ ውጣ እምቢ ካልክ አንበረክክሃለሁ›› ስትለው ‹‹ኤቢ ከምርሽ ነው›› በማለት ዘወር ብሎ ሲታገሉ ተይይዘው መውደቃቸውንና ከዚያ በኋላ የሆነውን እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡ የሆነው ሁሉ ከሆነ በኋላ ፍራሽ ላይ አስተኝቷት እያለቀሰ በሩን ሳይቆልፍ ገርበብ በማድረግ ‹‹ፖሊስና ሐኪም ይዤ ልምጣ›› በማለት ወደ ፖሊስ ሄዶ የሆነውን ሁሉ በመንገር ይዞ መጥቶ፣ ጓደኛው ገንዘብ ከቤት እንዲያመጣ በማድረግ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል መሄዳቸውን በመግለጽ የተከሳሽነት ቃሉን አጠቃሏል፡፡

አንደኛ የመከላከያ ምስክር በሰጠው የምስክርነት ቃል እንደገለጸው፣ አበራሽን 13 ዓመታት፣ አቶ ፍስሐን ለአሥር ዓመታት ያውቃቸዋል፡፡ ጓደኛቸው ነው፡፡ በጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውም ላይ ተገኝቷል፡፡ አቶ ፍስሐ አዛኝ፣ ሰዎችን የሚረዳ፣ ጋብቻቸውም ለሁሉም ሰው አርዓያ ነበር፤ ይዋደዳሉ፤ ይከባበራሉ፡፡ ሽማግሌያቸው በመሆኑ በመጨረሻው ሊለያዩ በነበረበት ጊዜ ሦስት ጊዜ ሽምግልና መቀመጡንና በእሱ (ፍስሐ) ጥያቄ ሁለቱም የነበራቸውን መሣሪያ እሱ ዘንድ እንዲቀመጥ ተደርጎ ከፍች በኋላ ሽማግሌዎች ባሉበት ማስረከቡን መስክሯል፡፡ ከፍች በኋላ አቶ ፍስሐ መታመሙንና ሆስፒታል መግባቱን እንደሚያውቅና አበራሽ ቤት ከተከራየች በኋላ እንደድሮው ይገናኙ እንደነበር ገልጾ፣ መስከረም 1 ቀን 2004 . ልጁንና ባለቤቱን ይዞ አበራሽ ባለችበት እሱ ቤት ቆንጆ ዓውደ ዓመት ማሳለፋቸውን ተናግሯል፡፡

መስከረም 2 ቀን 2004 . ዘወትር እንደሚያደርገው (በተለይ ከተፋቱ በኋላ) ወደ ፍስሐ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲደውል አላነሳ ስላለው፣ ለፍስሐ ዘበኛ ሲደውል እንዳልገባ እንደነገረው መስክሯል፡፡ ባለመሰልቸት ወደ ፍስሐ የደወለው ምስክሩ፣ መጨረሻ ላይ ፍስሐ አንስቶ የት እንደሆነ ሲጠይቀው ‹‹ከኤቢ ጋር ተጣልተን እሷ ቤት በፖሊስ ታስሬአለሁ›› ሲለው ወደ ዘበኛው በመደወልና አብረው በመሆን ወደ እሷ ቤት መሄዳቸውን አስረድቷል፡፡

ፖሊሶች ወደ ውስጥ እንዳይገባ ከልክለውት የሆነውን ሁሉ ውጭ ሆኖ ከተከታተለ በኋላ፣ በፖሊስ መኪና ይዘዋት ወደ ኮሪያ ሆስፒታል መሄዳቸውን፣ ፍስሐ ለዘበኛው ቁልፍ ሰጥቶት ገንዘብ እንዳመጣ፣ የሕክምና ወጪውን እንደሸፈነና ለአጎቷ ስልክ ደውሎ እንዳሳወቀ መስክሯል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ፍስሐ የት እንደሚኖርና ሌሎችንም መስቀለኛ ጥያቄዎች አንስቶለት መከላከያ ምስክሩ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የተከሳሹ ሁለተኛ ምስክርም ለአምስት ዓመታት በዘበኝነት ለአቶ ፍስሐ ካገለገለ በኋላ፣ አሁን የእሱ ሾፌር መሆኑንና አብሮ እንደሚኖር ከተናገረ በኋላ በሰጠው የምስክርነት ቃሉ፣ ሁለቱ ይዋደዱ እንደነበር፣ ተጣልተው እንደማያውቁና በመጨረሻም መስከረም 2 ቀን 2004 . የተፈጠረውን ችግር ከፍስሐ ጓደኛ (1 ምስክር) በኩል ሰምቶ አብሮ መሄዱንና ገንዘብ ወስዶ ለሕክምና መክፈሉን መስክሯል፡፡

ሦስተኛው የመከላከያ ምስክር የፖሊስ አባል ሲሆን፣ በዕለቱ ተወርዋሪ ተረኛ ሆኖ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ በሬዲዮ መገናኛ ወደ ገርጂ እንዲሄድ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ገርጂ ሲደርስ፣ የአካባቢው ፖሊስ መድረሱንና የሆነውን ሁሉ መመልከቱን ተናግሯል፡፡ በሰጠው ምስክርነት አበራሽ ኮንፈርት ለብሳ ተኝታ እንደነበር፣ ፖሊሱ ሲነካት ‹‹ፊሽ ነህ›› ስትለው ፖሊስ መሆኑን ሲነግራት፣ ‹‹ፊሽን እንዳትነኩት ጥፋቱ የእኔ ነው›› እንዳለችውና፣ በቤቱ ውስጥ ጎራዴ መገኘቱን፣ የእናቷ ማስታወሻ መሆኑን ተከሳሹ እንደገለጸላቸው፣ በትንሽ ጠረጴዛ ላይ መጠጥ እንደነበርና ብርጭቆዎች ወድቀው ማየቱንና ሲጠጡ እንደነበር ፍስሐ እንደነገራቸው መስክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዕለቱን የመከላከያ ምስክሮች ቃል ከሰማ በኋላ ቀሪዎቹን ምስክሮች ለመስማት ለሕዳር 19 ቀን 2004 . ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment