Wednesday, October 19, 2011

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት የስዊድን ጋዜጠኞች ክስ ሳይሰማ ቀረ

•  የአሜሪካ፣ የጀርመንና የፊንላንድ አምባሳደሮችና በርካታ ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል

 በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ሁለት ወራት በኋላ ጳጉሜን 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ክስ እንደተመሰረተባቸው የፍትሕ ሚኒስቴር ካስታወቀ በኋላ፣ ክሳቸው በትናንትናው ዕለት እንደሚሰማ ቢገለጽም ሳይሰማ ቀርቷል፡፡ በትናንትናው ዕለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ችሎት ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ሲከፈት፣ የአሜሪካ፣ የፊንላንድ፣ የስዊድን፣ የጀርመንና የሌሎችም አገሮች አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአገር ውስጥ፣ የውጭ አገር ጋዜጠኞችና ለተያዩ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት የተመመው ሕዝብ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የፍርድ ቤቱን ግቢ ልዩ ድባብ ሰጥቶት ነበር፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር ስለሽብር ተጠርጣሪዎቹ መከሰስ እንጂ ክሳቸው የሚታይበትን ችሎት ባለመግለጹ፣ ትናንትና በተለይ ዲፕሎማቶቹና ጋዜጠኞች ችሎቱ ሳይጀመር ቀድመው ለመታደም በፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ሲሯሯጡ ለተመለከታቸውና ስለዕለቱ ሁኔታ መረጃ የሌለው ሰው ‹‹ምን ተፈጠረ›› ሳይል አይቀርም፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሚቀርቡበት ችሎት ከታወቀ በኋላ ሁሉም ታዳሚ ወደ አንድ ቦታ ሲሰባሰብ፣ ክሱ ይታይበታል የተባለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ወደ አንደኛ ወንጀል ችሎት የሚታይበት ችሎት ተቀየረ፡፡

የችሎቱ መቀየር እንደተሰማ ሁሉም ታዳሚ ግር ብሎ ወደ ተቀየረው ችሎት ከሄደ በኋላ፣ ጥብቅ ፍተሻ በማድረግ በቅድሚያ ዲፕሎማቶቹ ቀጥሎ ጋዜጠኞች ወደ ችሎቱ እንዲገቡ ተደረጉ፡፡

Martin Schibbye
ከጠዋቱ 3፡10 ሰዓት ሲሆን ችሎቱ ተሰየመ፡፡ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ሁለቱ ማለትም አብዲ ወሊ መሀመድ እስማኤልና ከሊፍ ዓሊ ዳሂር የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆኑ፣ ጋዜጠኛ መርቲን ካርል ሽብዬና የፎቶ ጋዜጠኛው ጁሃን ካርል ፐርሰን እንግሊዝኛ ተናጋሪ ስለሆኑ፣ ለፍርድ ቤቱ የሚያስተረጉሙ እንደሚመጡ ፍርድ ቤቱ ለታዳሚው ገለጸ፡፡

ቦታውን ቀይሮ በሌላ ችሎት የተሰየመው የዕለቱ ችሎት ሥራውን ከመጀመሩ በፊት፣ ከአራቱ የሽብር ተጠርጣሪና ተከሳሾች ጋር ችሎት የቀረቡ ሌሎች ባለጉዳዮች በፖሊስ ተጠብቀው በውጭ እንዲጠበቁ ከተደረገ በኋላ፣ እነሱ ባለቀቁት ቦታ ላይ መቀመጫ ጠቧቸው ባንድ ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ጋዜጠኞችንና ዘግይተው የመጡ የውጭ ዜጐች እንዲቀመጡ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ ለሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች የቆሙትን ጠበቃ አበበ ባልቻና ጠበቃ ስለሺ ቀፀላ መቅረባቸውን ካረጋገጠ በኋላ፣ ሁለቱ የሶማሌ ተወላጆች ጠበቃ እንዳላቸውና እንደሌላቸው ጠይቋቸው ‹‹የለንም›› በማለታቸው፣ ‹‹ጠበቃ የምናቆምበት ምንም ሀብትም ሆነ ንብረት የለንም›› ብለው እንዲምሉ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ሱማሌዎቹ ምንም ሀብትም ሆነ ንብረት እንደሌላቸው በመሀላ ካረጋገጡ በኋላ፣ መንግሥት ከተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ክሱ እንደደረሳቸውና እንዳልደረሳቸው ካረጋገጠ በኋላ፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ከመስማቱ በፊት የጋዜጠኞቹ ጠበቆች በክሱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገለጹ፡፡

የክስ ቻርጁ ቢደርሳቸውም በክሱ ላይ የተጠቀሰ የቪዲዮ ማስረጃ እንዳልደረሳቸው ጠበቆቹ ሲገልጹ፣ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ‹‹ፍርድ ቤቱ ወደፊት  አስቀርቦ የሚያየው ይሆናል፡፡ ለጠበቆች እንድንሰጥ የምንገደድበት የሕግ አግባብ የለም፤›› በማለት ተቃውሞአቸው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

ተከሳሾቹ የተንቀሳቀሱባቸውን ቦታዎች የሚያሳየው ማስረጃ የሚገኘው ይዘውት በነበረው ላፕቶፕ ውስጥ እንደነበር የገለጹት ጠበቆቹ፣ ወደፊት ‹‹ተከላከሉ›› ቢባሉ ለማስረጃነት ስለሚጠቅማቸው ፍርድ ቤቱ እንዲያዝላቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መጨረሻ ላይ በዕለቱ የነበረው ቀጠሮ የተጠርጣሪ ተከሳሾችን ክስ ለመስማት እንደነበር አስታውሶ፣ ተጠርጣሪዎቹ የተከሰሱበት አንቀጽ ከባድ በመሆኑና በተለይ ሁለቱ ተከሳሾች በአቅም ምክንያት ጠበቃ ማቆም ባለመቻላቸው፣ መንግሥት ሊያቆምላቸው ስለሚገባ ክሱን በሚቀጥለው ቀጠሮ ለመስማት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በመሆኑም ለሁለቱ ሱማሌዎች ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ዛሬ አነጋግሯቸውና ተመካክረው በነገው ዕለት እንዲቀርቡ በማዘዝ ክሱ ሳይሰማ ለነገ ቀጠሮ በመያዝ ችሎቱ አብቅቷል፡፡ 


http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment