“ድርጊቱን አልፈጸምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” ተጠርጣሪ የወንድወሰን ይልማ
በታምሩ ጽጌ
ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 20/20 ልዩ ሥፍራው ካርቱም ሬስቶራንት ኦሎምፒያ አካባቢ የልጆቹን እናት ከ10 በላይ ጥይቶች ተኩሶ ግፍ በተሞላበትና በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ የወንድወሰን ይልማ፣ በከባድ የሰው መግደል ወንጀልና የሰው መግደል ሙከራ ወንጀል ክስ ተመሠረተበት፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ኅዳር 25 ቀን የተጻፈ የክስ ማመልከቻ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን የተመለከተው ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡
ተጠርጣሪው ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰሌዳ ቁጥሩ 2-75991 የሆነ መኪና እያሽከረከረ ባምቢስ አካባቢ ሲደርስ፣ ሟችና የሁለት ልጆቹ እናትን ወይዘሮ ፍሬሕይወት ታደሰን የሰሌዳ ቁጥሩ 2-76225 እያሽከረከረች ይመለከታታል፡፡
በመከታተል ኦሎምፒያ ካርቱም ሬስቶራንት አካባቢ ሲደርስባት፣ ይዞት በነበረው የውግ ቁጥሩ 0740722 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከአሥር በላይ ጥይቶች ተኩሷል፡፡ በተኮሳቸው ጥይቶች ሟችን ደረቷን፣ ጭንቅላቷን፣ ግንባሯን፣ ሆዷን፣ ጀርባዋን፣ ሁለቱንም ታፋዎቿን፣ እጆቿንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿን በመምታት ጨካኝና ነውረኛነቱን በሚያሳይ ሁኔታ እንደገደላት የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪው ይዞት በነበረው መሣርያ ሟች ታሽከረክረው የነበረው የሰሌዳ ቁጥር 2-76225 መኪና በመምታት የ33,600 ብር የንብረት ጉዳት በማድረሱም ተከሷል፡፡
ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ቀርቦ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም፣ ወንጀለኛም አይደለሁም፤” ብሎ ክዶ በመከራከሩ፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም. አቅርቦ እንዲያስመሰክር ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
http://ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment