- የአቶ ጁነዲን ባለቤት ክስ ከሌሎቹ እንደማይለይ ተገለጸ
በታምሩ ጽጌ
የእምነት ነፃነትን በመቃረን ከራሳቸው አክራሪ አስተሳሰብና አስተምህሮት ውጪ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ እምነት መኖር የለበትም በሚል ሃይማኖታዊ መንግሥት ለማቋቋም ፖለቲካዊ ግብ በማስቀመጥ፣ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው 29 ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ፣ የሕግ መሠረት የሌለው ነው በማለት ውድቅ እንዲደረግ ዓቃቤ ሕግ ጠየቀ፡፡ የፌዴራሉ ዓቃቤ ሕግ ኅዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው አማካይነት ላቀረቡት የመጀመሪያ መቃወሚያ የክስ መልስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት አቅርበዋል፡፡
ዓቃቤ ሕጉ ባቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾች ላቀረበው መቃወሚያ ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት፣ ጠበቆች የሚያቀርቡት አቤቱታ እንዳላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ጠበቆቹ ባቀረቡት አቤቱታ ተጠርጣሪ ደንበኞቻቸው በሕግ ከለላ ሥር እያሉና ተጠርጥርው በተከሰሱበት ክስ ጥፋተኛ ተብለው በፍርድ ቤት እስካልተወሰነባቸው ድረስ ነፃ ሆነው የመታሰብ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚያሳጣ ዘገባ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና በዛሚ ኮሙዩኒኬሽን ኤፍኤም ሬዲዮ እየተላለፈ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡ በዕለቱ በነበረው ችሎት ውስጥ የተጠቀሱት ሚዲያዎች ዘጋቢዎች ካሉም እንዲያስወጣላቸው ጠየቁ፡፡ በወንጀል ክስ እንደሚመሠርቱም አስታወቁ፡፡
ዳኞች ከተመካከሩ በኋላ በሰጡት ትዕዛዝ፣ ‹‹ክሱ ሲጀመር ችሎቱ ዝግ ነው አልተባለም፤ ማንም የመከታተል መብት አለው፡፡ ዘጋቢዎችም ሲዘግቡ ኃላፊነት እንዳለባቸው አውቀው መሥራት አለባቸው፡፡ ከዚያ ውጭ ከሠሩ በሕግ የሚጠየቁበት አሠራር አለ፡፡ አሁን ግን ከፊሉ ይውጣ ከፊሉ ይከታተል ማለት አይቻልም፤›› በማለት ዓቃቤ ሕግ ለቀረበበት ተቃውሞው መልስ እንዲሰጥ አዘዘ፡፡
ዓቃቤ ሕግ ባቀረባቸው ክሶች ላይ ከተከሳሾች የቀረቡትን መቃወሚያዎች፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ክሱን የማየት ሥልጣን የለውም፤ በቀረበው ክስ ላይ የተጠቀሰው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ሕገ መንግሥቱንና ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የቃልኪዳን ሰነዶች የተቃረነ መሆኑንና በክሱ ውስጥ የተጠቀሱ ቃላት፣ ሐረጐችና ዓረፍተ ነገሮች ትርጉም ስለሚያስፈልጋቸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረብ አለባቸው፤›› በሚል ከፋፍሎ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡
ዓቃቤ ሕግ ከላይ በጠቃሳቸው መልኩ ከፋፍሎ ምላሽ እንደሚሰጥበት ቀድሞ ቢያሳውቅም፣ የመጀመርያ መልሱ የሆነው ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት ያቀረቡት የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ የወንጀለኛ ሕግ ቁጥር 130 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2ን የሚያሟላ ባለመሆኑ መቃወሚያቸው ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን ክስ የማየት ሥልጣን እንደሌለው ተከሳሾች ላቀረቡት መቃወሚያ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ ተቃዋሚዎቹ ፍርድ ቤቱ በምንና እንዴት ሥልጣን እንደሌለው ነጥለውና ገልጸው ባያቀርቡም፣ ፍርድ ቤቱ ግን በወንጀል ሕጉም ሆነ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ተጠርጣሪዎቹ የተከሰሱበትን ዓይነት የወንጀል ክስ የማየት ሥልጣን እንዳለው መደንገጉን አስታውቋል፡፡
ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ቃላት፣ ዓረፍተ ነገሮችና ሐረጐችን በሚመለከትም ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸውን ለይተው ባለማቅረባቸው ለፌዴራል ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሚላክበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡
ደንበኞቻቸው የተከሰሱትና ያለዋስትና በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ የተደረጉት ሕገ መንግሥቱን በመቃረን በታወጀው የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ መሆኑን ጠበቆች ለተቃወሙት ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ አዋጁ የወጣው የንፁኃንን ሕይወት የሚቀጥፈውንና ሌሎች ያልተጠበቁ ውድመቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መሆኑን በማስረዳት ላይ እያለ፣ ከተከሳሾች ጠበቆች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ጠበቆች ባቀረቡት ተቃውሞ፣ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ እየሰጠ ያለው ባቀረቡት ተቃውሞ ላይ ሳይሆን ስለ ሕጉ አወጣጥ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ጠበቆች የሚናገሩበት የሕግ ሥነ ሥርዓት ስለሌለ ተቃውሞአቸውን እንዲያቆሙ በመንገር፣ ዓቃቤ ሕግ ምላሹን ካቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ካቀረቡት ተቃውሞ ጋር በማስተያየት እንደሚመዝነው በመግለጽ ዓቃቤ ሕግ እንዲቀጥል አዟል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በመቀጠል ፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከሕገ መንግሥቱም ጋር ሆነ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር እንደማይቃረን በመጠቆም፣ በዓለም ላይ 17 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ የፀረ ሽብርተኝነት ስምምነቶች እንዳሉም ጠቁሟል፡፡ የትኞቹ ድርጊቶችም ሽብርተኛ ሊያሰኙ እንደሚችሉ ተለይተው መቀመጣቸውንና የእነሱም ክስ ከዚህ አኳያ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ቤታቸው እንደተበረበረና ስለመያዛቸው ለቀረበው መቃወሚያ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ ፖሊስ ወንጀል እንደሚፈጸም በቂ ጥርጣሬ ካለው መያዝ እንደሚችል፣ በወንጀል ሕጉ ጣሪያ ባይቀመጥለትም የ14 ቀናት የምርመራ ቀጠሮ መጠየቅ እንደሚችል አስረድተው፣ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ግን 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ ለአራት ወራት ብቻ እንደሚቆዩ ገደብ በማበጀቱና የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ፈቃድ ሳይሰጡ መበርበር ስለማይቻል፣ በተጠርጣሪዎቹም ላይ በሕጉ መሠረት መደረጉን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በኃይልና ያለ ግለሰቡ ፈቃድም የተወሰደ ምርመራ እንደሌለም ጠቁሟል፡፡
ክሱ ባንድ ላይ መቅረብ ሲገባው ተነጣጥሎ መቅረቡ ደንበኞቻቸውን እንደሚጐዳ የተጠርጣሪ ጠበቆች ላቀረቡት መቃወሚያ፣ ክሱ የቀረበው ለእያንዳንዱ ድርጊት ማን ምን እንደሠራና ምን የሥራ ኃላፊነት እንዳለው ጭምር ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ማቅረቡን አስረድቶ፣ ተቃውሞው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ቀኑ፣ ወሩና ድርጊቱ የተፈጸመበት ዕለት አለመጠቀሱን፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የፀደቀው በህቡዕ ተደራጅተዋል ከተባለበት ዕለት በፊት ስለሆነ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ለቀረበው ተቃውሞ፣ ዓቃቤ ሕግ ሁሉንም ዝርዝር በክሱ ውስጥ መጥቀሱን ገልጾ፣ ጊዜው የሚወሰደው እጃቸው ከተያዘበት ጀምሮ መሆኑ በሕግ መደንገጉንም አክሏል፡፡
ጅሀድ፣ አስተምህሮትና ሌሎች ሃይማኖታዊ ቋንቋዎች ናቸውና ክስ ሊመሠረትባቸው እንደማይገባ በተቃውሞ ስለቀረቡበት ሁኔታ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ ቃላቱ፣ ሐረጐቹ ወይም ዓረፍተ ነገሮቹ ዓቃቤ ሕግ የፈጠራቸው ሳይሆኑ ተከሳሾች ሽብር ለመፈጸም ሲነጋገሩባቸው የነበሩና በማስረጃም የሚረጋገጡ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
የአቶ ጁነዲን ሳዶን ባለቤት ክስ በሚመለከት ከሌሎቹ ተለይቶ ክሱ መታየት እንዳለበትና ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር ተቀላቅሎ መቅረብ እንደሌለበት የተነሳውን መቃወሚያ በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ ግለሰቧ የወንጀሉ ተካፋይ መሆናቸውን፣ የወንጀሉ ዓላማ አንድ ዓይነት መሆኑንና ‹‹ማን ነበር? የት ነበር?›› የሚለው በማስረጃ የሚጣራ በመሆኑ ክሱ ተነጣጥሎ መቅረብ እንደሌለበት አስረድቷል፡፡
የዓቃቤ ሕግ 23ኛ ተከሳሽ አብዱራዛቅ አክመል ሐሰን የተባለው ተጠርጣሪ የአዕምሮ፣ የነርቭና የአጥንት ሕመም ያለበት በመሆኑ በነፃ መሰናበት እንዳለበት ጠበቆች በጠየቁት መሠረት፣ ፍርድ ቤት ማስረጃ እንዲቀርብ ጠይቋል፡፡ ጠበቆች የምስክሮችን ዝርዝር በሚመለከት ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ የሰጠው ዓቃቤ ሕግ ለማባበል፣ ለማስፈራራት ወይም ጉዳት ለማድረስ ካልሆነ በስተቀር ስማቸው እንደማይጠቀስ ሕጉም ስለሚደግፍ፣ ጥያቄውን ተቃውሞ ጊዜው ሲደርስ በችሎት እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ግራና ቀኝ የቀረቡትን ተቃውሞና ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለኅዳር 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
http://ethiopianreporter.com
Hop onto the best convection microwave oven in India now. Get the best microwave oven in
ReplyDeleteIndia. best convection microwave oven