Sunday, December 2, 2012

ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ ምሁራን የግራዚያኒ ሐውልት እንዲፈርስ ጥያቄ አቀረቡ

በኢጣሊያ አፊሌ ከተማ የተገነባው የፋሺስት ጦር ወንጀለኛው ሩዶልፍ ግራዚያኒ ሐውልት


በሔኖክ ያሬድ

ባለፈው ወር በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው 18ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ምሁራን፣ በኢጣሊያ አፊሌ ከተማ የተገነባው የፋሺስት ጦር ወንጀለኛው ሩዶልፍ ግራዚያኒ ሐውልት እንዲፈርስ ወይም እንዲለወጥ የኢጣሊያ መንግሥትን ጠየቁ፡፡

ከመላው ዓለም ከ26 አገሮች የተውጣጡት 300 ምሁራን ከጥቅምት 19 ቀን እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ያካሄዱትን 18ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ሲያጠናቅቁ ያወጡትን መግለጫ፣ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጂኦርጂዮ ናፖሊታኖ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ሞንቲ በላኩት ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡

በጉባዔው የተሳተፉት ታዋቂው የታሪክ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ለሪፖርተር በኢሜይል የላኩት የደብዳቤው ቅጅ እንደሚያመለክተው፣ የኢጣሊያ ፋሺዝም በኢትዮጵያና ቀደም ብሎም በሊቢያ ላይ ላደረሰው ግፍ በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን እልቂት ተጠያቂው ግራዚያኒ ነው፡፡ ግራዚያኒ ለሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ከሕዝቧ ጋር አሊያም ኢትዮጵያን ብቻ›› አበረክትልሃለሁ ማለቱን ያስታወሰው ደብዳቤው፣ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በመርዝ ጋዝ ፈጅቷል፡፡

የግራዚያኒ ፍጅት
በተለይም ጎልቶ የሚታወቀው ‹‹የግራዚያኒ ፍጅት›› የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. የሰላማውያን ኢትዮጵያ ዘግናኝ እልቂት ትኩረቱን በተማሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ላይም ማነጣጠሩን፣ በግንቦት ወርም የመካከለኛው ዘመን ገዳም በሆነው ደብረ ሊባኖስ 300 መነኮሳትና ሌሎች 20 ኢትዮጵያውያንም መጨፍጨፉን አስታውሷል፡፡

ግራዚያኒ በሕይወት ቢኖር ኖሮ በአፍሪካ ለፈጸመው ግፍ ያለ ጥርጥር በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ችሎት እንዲቀርብ ይደረግ ነበር በማለት የገለጸው የምሁራኑ ደብዳቤ፣ በበርካቶች አፍሪካውያን ደም እጁ ለጨቀየው ግራዚያኒ ከሕዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ሐውልት እንዲተከልለት መደረጉ ሰለባዎችን መስደብ መኾኑን አጽንዖት ሰጥቶበታል፡፡

የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ከ53 ዓመታት በፊት እንዲጀመር ኢጣሊያውያን ምሁራን ያደረጉት ታላቅ አስተዋጽኦ የዘከሩት ጉባዔተኞቹ፣ ይህም በሁለቱም አገሮች ሕዝቦችና መንግሥታት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር ቢያስችልም፣ ይሁን እንጂ በጦር ወንጀለኛነትና ጨካኝነቱ ለተረጋገጠው ግራዚያኒ ሐውልት እንዲታነጽለት መደረጉ ግንኙነቱን እንዳያጨናግፈው ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የግራዚያኒ ፍጅት
በመሆኑም ይህን ተግባር በጥብቅ በመቃወም አቋማቸውን ከገለጹ ኢጣሊያውያንና ኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸውን አንድነት በመግለጽ፣ የግራዚያኒ አሳፋሪ ሐውልት ወይ ይፍረስ አሊያም በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩት የግራዚያኒ ሰለባዎች መታሰቢያ በሚሆን መልኩ እንዲስተካከል ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የኢጣሊያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጦር ወንጀለኛነት ለተፈረጁ አንዳች ዓይነት መታሰቢያና ክብር እንዳይሰጣቸው የሚያደርግ ሕግ እንዲደነግግም ተማጽነዋል፡፡ ለኢጣሊያ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር የተላከው ደብዳቤ ግልባጭም ለፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በኢትዮጵያ ለኢጣሊያ አምባሳደር ሬንዞ ሮሶ እና ለኢጣሊያ የአፍሪካ ጥናቶች ማኅበር መላኩን ለማወቅ ተችሏል፡፡


የግራዚያኒ ፍጅት
ግራዚያኒ ከ76 ዓመት በፊት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በአዲስ አበባ 30 ሺሕ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ ያካሔደው የኔፕልስ ልዕልት በመወለዷ ለደስታ መግለጫ ብሎ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ባዘጋጀው የስጦታ መድረክ ላይ፣ አርበኞቹ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በቦምብ ጉዳት ካደረሱበት በኋላ ነው፡፡

በታሪክ እንደተመዘገበው ፋሺስቶቹም የበቀል አጸፋውን በቤተ መንግሥቱ ከተገኘው ሕዝብ በተጨማሪ ከተማውን ዳር እስከዳር በማመስ ነዋሪውን በቤት ውስጥ እያስገቡ ከውጭ ቆልፈው ቤንዚን እያርከፈከፉ ሲያቃጥሉ፣ በአካፋ፣ በዶማና በመጥረቢያ እየቆራረጡ ፍጅቱን ፈጽመዋል፡፡ ገፈቱን በቀመሱት አርበኛው ደራሲ ተመስገን ገብሬ አገላለጽ፣ ‹‹ዓለም በድንገት ተለውጣ፣ አዲስ አበባም ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያውያንን የሚያርዱበት ቄራ ሆና ነበር፡፡››

ሩዶልፍ ግራዚያኒ የቤኔቶ ሙሶሎኒ ፋሺስታዊ መንግሥት ከወደቀ በኋላ በጦር ወንጀለኝነት ተከሶ የ19 ዓመታት ፍርድ ቢተላለፍበትም፣ ከሁለት ዓመት እስር በኋላ ተለቆ በ1955 ዓ.ም. መሞቱ ይታወቃል፡፡

የተለያዩ የዜና ዘገባዎች ባለፈው ነሐሴ እንደዘገቡት፣ የግራዚያኒ መታሰቢያ ሐውልትና ሙዚየም 127 ሺሕ ዩሮ እንደፈጀና በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይም የከተማው ከንቲባ ኤርኰል ቪሪን ጨምሮ 100 የሚሆኑ ‹‹የቀድሞ ፋሺስቶች የነፃነት ሕዝብ›› (በኢጣልያንኛ IL Poplo della Liberta) የቀኝ ክንፍ ፓርቲ አባላት መገኘታቸው ይታወሳል፡፡
http://ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment