Sunday, December 18, 2011

ሁለት የአየር ኃይል አውሮፕላኖች ተጋጭተው አንድ ፓይለት ሞተ


በልምምድ ላይ የነበሩ ሁለት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጦር አውሮፕላኖች ተጋጭተው ተከሰከሱ፡፡ በአደጋው አንድ ፓይለት ሲሞት ሌላ አብራሪና ሁለት ሠልጣኞች ከፍተኛ አደጋ ደርሶባቸው በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡

ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኤስኤፍ 260 የተሰኙት ለፓይለት ማሠልጠኛነት የሚያገለግሉት ሁለቱ አውሮፕላኖች ድሬዳዋ አካባቢ ተጋጭተው የተከሰከሱት ባለፈው ሳምንት ነው፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በጦር አውሮፕላኖቹ ላይ አደጋ የደረሰው አርፎ የመነሳት ልምምድ በሚያደርጉበት ወቅት ሲሆን፣ ሟች ሻምበል ማዕረግ ሕይወት የነበረበት አውሮፕላን አርፎ ሲነሳ በማረፍ ላይ የነበረው የሁለተኛው አውሮፕላን ክንፍ በቀጥታ የፓይለቱን ክፍል መስታወት ሰብሮ በመግባት የሟች አናት ላይ በማረፉ ለሞት ዳርጎታል፡፡ የሌላኛው አውሮፕላን የፓይለት አሠልጣኝና ሁለት ሠልጣኞች ደግሞ በደረሰባቸው አደጋ ኮማ ውስጥ ናቸው፡፡

ሟች ሻምበል ማዕረግ የነበረበት አውሮፕላን ሁለቱ አውሮፕላኖች ከተጋጩ በኋላ ወዲያውኑ ሲከሰከስ ሁለተኛው አውሮፕላን ግን እንደምንም ብሎ ሊያርፍ ችሏል፡፡ ገጪው አውሮፕላን ሲያርፍ ክንፉ ተቀዶ ነዳጅ እያፈሰሰ ነበር፡፡ ሻምበል ማዕረግ ሲያለማምደው የነበረው ሠልጣኝ የሚወስደው ሥልጠና የአውሮፕላን አብራሪ አሠልጣኝ ለመሆን የሚያስችለው ነበር፡፡

የሩሲያ ሥሪት የሆነው 27 አውሮፕላን አብራሪ የነበረው የሟች ሻምበል ማዕረግ አስከሬን ቤተሰቦቹ ወደሚኖሩበት ደሴ ከተማ የተላከ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኤስኤፍ 260 የተባሉት ሁለት የጦር አውሮፕላኖች የተገዙት በደርግ ጊዜ የግንቦት 8 መፈንቅለ መንግሥት ቀስቃሽና የአየር ኃይሉ አዛዥ በነበሩት በሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ ነበር፡፡ በወቅቱ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ 10 የጦር አውሮፕላኖችን ከጣሊያን የገዙ ሲሆን፣ አውሮፕላኖቹ 30 ዓመት የቆይታ ታሪካቸው አንድ ጊዜ ብቻ አደጋ ሲደርስባቸው ከፍተኛ የደህንነት ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment