Saturday, December 17, 2011

የአቶ በረከት ስምኦን መጽሐፍ ማክሰኞ ይመረቃል ምርጫ 97- በሰላም ተጀምሮ በብጥብጥ የተቋጨ


ምርጫ 2002- በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተቋጨ፣ ብለውታል


ምርጫ 2002- በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተቋጨ፣ ብለውታል

‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› የተሰኘው የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት የአቶ በረከት ስምኦን  መጽሐፍ የፊታችን ማክሰኞ  በሸራተን ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ ይመረቃል፡፡የሁለት ምርጫዎች ወግየሚለው የአቶ በረከት ፖለቲካዊ መጽሐፍናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ”  የሚል ንኡስ ርእስ የተሰጠው ሲሆን በመጽሐፉ ክፍል አንድ ውስጥ፤ ምርጫ 97፣ሟሟሻ ወግ፣ሦስተኛው አገራዊ ምርጫና የቅድመ ምርጫ ሂደቱ፣ ቆጠራና ያልተገመተ የምርጫ ውጤት፣ድህረ ምርጫ፤የዜሮ ድምር ፖለቲካ በተግባር የሚሉ ርእሶች ተካተውበታል፡፡

በክፍል ሁለት ደግሞ፤ሁሉን ታገኛለህ!?” ወይም ሁሉን ታጣላህ! ፣እንደገና ሌላ ቅድመ ምርጫ፤ምርጫ 2000…ትንሿ አስደንጋጭ ምልክት፣ሰላምና አመጽ በሌላ ዙር የምርጫ ፍልሚያ፣ ድምጽ መስጠት ቆጠራ እና ፈጽሞ ያልተገመተው ውጤት፣ መቋጫ ወግ የሚሉ በአጠቃላይ አጭር ምዕራፎች አሉት፡፡አቶ በረከት በመጽሐፋቸው መቅድም‹‹…..ሁለቱ ምርጫዎች በመሰረታዊ ባህሪያቸው ተመሳሳይ ቢሆኑም በብዙ ጉዳዮች ደግሞ በጣም ተነጻጻሪነት የታየባቸው ነበሩ፡፡አንደኛው በሰላም ተጀምሮ በብጥብጥ የተቋጨ ሲሆን ሌላው በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተቋጨ ነበር፡፡እንደገናም የመጀመሪያው ተቃዋሚዎች 12 ወደ170 ወንበሮች እመርታ ያሳዩበት ምርጫ ሲሆን የኋለኛው ደግሞ 170 ወደ አንድ ወንበር ያሽቆለቆሉበት ነበር፡፡ኢሕአዴግ 97 ምርጫ በአያሌው ተንገዳግዶ በምርጫ 2002 ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ልቆ ያሸነፈበት እንደሆነው ሁሉ››በማለት ስለሁለቱ ምርጫዎች በንፅፅር ጽፈዋል፡፡ስለ ትውልዱና ገድሉ በጠቀሱበት የመቅድሙ አንቀጽ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- ‹‹አባል የሆንኩበት የታጋ ትውልድ ከስድሳዎቹ አጋማሽ እስከአሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተዋናይ ነው፡፡የመጀመሪያዎቹና ከተማሪዎች ንቅናቄ ፈልቀው የትግልን ፈለግ ያስተማሩን መሪዎቻችን በብዙ መልካም አቋሞቻቸው መሞገስ ያለባቸውን ያህል በልምድና በአተያይ እጥረት ትግሉን ወደፊት ማራመድ ሲያቅታቸው በእኛ የትግል ትውልድ መተካታቸው አይቀሬ ሆነ፡፡ትግል የዱላ ቅብብሎሽ ነውና እኛም በፋንታችን ለቀጣዩ ትውልድ ሐላፊነቱን እስክናስረክብ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የሐላፊነት ደረጃዎች አገለገልን፡፡የተመደብንበት የአመራርነት ሐላፊነት የአገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚነኩ ብዙ ውሳኔዎች የተላለፉበት፤ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ተደጋግፈን የተረባረብንበት፣በሂደት ደግሞ የዛሬውን የኢትዮጵያ እውነታ የፈጠርንበት ሆነ፡፡

ኢሕአዴግን በጋራ መርተን እዚህ ያደረስነው የአመራር አባላት ሁሉ የድርሻችንን አስተዋፅኦ ባበረከትንበት በዚህ ሂደት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡በታሪክ መልክ ቢቀርቡ ተደምጠው የማይሰለቹ ብዙ፣እጅግ በጣም ብዙ የጀግንነት የሕዝብና የአገር ፍቅር፣የሰማዕትነትና እንዲያም ሲል የፍቅር ገድሎች ተፈፅመዋል፡፡ደርግን ለመጣል በለጋ ዕድሜያችን በተቀላቀልነው የትግል ድርጅት ውስጥ ተሰልፈን ያልተዋጋንበት የአገራችን ክልል እና እየወደቅን እየተነሳን ያልፈጸምነው ገድል አልነበረም…”ስንት የገድል ጉዞ በታለፈበት ሂደት ከትግሉ የማለዳ ወቅቶች መነሳት ሲቻል ለምን በምርጫዎች ወግ መጀመር ተመረጠ የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል ያወሱት አቶ በረከት፤  የምርጫዎች ጉዳይ ከብዙዎች አእምሮ ውስጥ ያልጠፉ የቅርብ ትዝታዎች በመሆናቸው እና ሁለቱም ምርጫዎች የተለየ ገጽታ እና ባህሪ ስለነበራቸው ነው ሲሉ ይመልሳሉ፡፡የታሪክ መጽሐፍ የሚያዘጋጅ ሰው የመጀመሪያው ችግር ከየት መጀመር እንዳለበት በትክክል መወሰን ላይ ነውያሉት አቶ በረከት፤‹‹ይህ መጽሐፍ በሁለቱ ምርጫዎች ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ቢሆንም ለሕዝቡ እና ለሁሉም ተዋናዮች የምርጫ ገጸ ባህሪ መነሻ ሆኖ ያገለገለው የኢሕአዴግ የተሀድሶ ንቅናቄ ነበርና ከእሱ መጀመርን የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
                             
ተሀድሶው ደግሞ ከኢትዮ ኤርትራ ግጭት ለጥቆ የመጣ በመሆኑ እንደገና ከዚህ መጀመሩ ተገቢነት ነበረው፡፡››በማለት በመቅድማቸው አብራርተዋል፡፡መጽሐፉ ላይ የጠቀሷቸውን ግለሰቦች ስለገለጹበት አንተ እናአንቺእና አንቱታ አጠራር ምክንያት ሲገልጹም፤‹‹በመጽሐፉ ውስጥ አንዳንዶቹን አንተ ወይም አንቺ፣እርሱ ወይም እርሷ በማለት፤ሌሎቹን ደግሞ በአንቱታ የገለጽኩትም በሰማንያ ዓመተ ምህረት በአስራዎቹ አጋማሽ ዕድሜው ላሊበላ ያገኘሁትን አቶ ልደቱን ጨምሮ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በቅርብ የማውቃቸውን ሁሉ አፌን በፈታሁበት የቅርበት አጠራር፣ ማቅረቡ ተገቢ መስሎ ስለተሰማኝ ብቻ ነው፡፡›› የመጽሐፉ ምርቃት ጥሪ ካርድ  የመጽሐፉን ምስል የያዘ ሲሆን ከመጽሐፉ ጀርባ አቶ መለስ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት ተናገሩት በሚል ተቀንጭቦ የቀረበው ጹሑፍ እንዲህ ይላል፤ ‹‹የተሃድሶ እንቅስቃሴያችንን በከፍተኛ ፍጥነት ከሚወርድ እና በየደቂቃው ፍጥነት እየጨመረ ከሚጓዝ ናዳ አምልጦ ወደ ጠንካራ ከለላ ለመግባት ከሚሮጥ ሰው ጋራ ማመሳሰል ይቻላል፡፡ ይህ ሰው ከለላው ያለበትን አቅጣጫ አውቆ ወደዚያ የሚያመራ አቋራጭ መንገድ ይዞ ካልተጓዘ በስተቀር በናዳው እንደሚዳፈን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህም አኳያ ቀና አቅጣጫም ተይዞ ቢሆን ሰውየው ከናዳው ፍጥነት በላይ መሮጥ ካልቻለ ባለበትም ቢቀበር፣ ወደመጠለያው ለመግባት አንድ እርምጃ ሲቀረው ቢቀበር ለውጥ የለውም፡፡ ዞሮ ዞሮ በፍጥነት ችግር ምክንያት መሞቱ አልቀረም፡፡ በሌላ አነጋገር የፍጥነትም ጉዳይ ከአቅጣጫው ባላነሰ መንገድ የህልውና ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ፍጥነትም ሳይሆን አደጋው እየተጓዘበት ካለው ፍጥነት ጋር ተነጻጽሮ ከአደጋው ለማምለጥ የሚያስችል ብቃት ያለው ፍጥነት ወሳኝ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡እኛም ያለንበት ሁኔታ ቀና መንገድ ይዘን ከአደጋው ለማምለጥ ብቃት ያለው ፍጥነት ስለሌለን በእርግጠኝነት የምንሸነፍበት አደጋ ነው እየተከሰተ ያለው፡፡››በማለት የአደጋውን ክብደት እና አስፈሪነት በግልጽ አስረዳ፡፡ከናዳ ለማምለጥ የሚሮጠው ሰው አደጋው ሳይደርስበት ቀድሞ ለማለፍ በሚያስችለው ፍጥነት መሮጥ አለበት በማለት የቀረበው ምሳሌ አመራሩን ጊዜ የለንም በሚል ጥድፊያ ውስጥ እንዲገባ አደረገው፡፡የአርመናጌዲዮን አደጋ ፈጦ በወጣት …..ለተፋጠነ ለውጥ አመቺ የሆነ የፖሊሲ እና ስትራተጂ ማእቀፍ መዘጋጀቱ፣በተጨባጭ የተደቀነው የህልውና አደጋ እና ከአደጋው ለማምለጥ የተፈጠረው ከፍተኛ ወኔ እና ፍላጎት የኢትዮጵያ ህዳሴ መሰረቶች ሆኑ፡፡››ይላል፡፡፡ የፊታችን ማክሰኞ በሸራተን የሚከናወነውን የመጽሐፍ ምርቃት ያዘጋጀው ታሜሶል ኮሙኒኬሽን እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል

No comments:

Post a Comment