ባሳለፍነው ሳምንት ወታደሮችዋን ሶማሊያ ውስጥ አስገብታለች የሚሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዘገባዎችን ስታስተባብል የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሶማሊያ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ ኦፊሴላዊ ጥያቄ እንደቀረበላትና መስማማቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሪፖርተር አረጋገጠ፡፡ ባለፈው ዓርብ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተመራው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የመሪዎች ስብሰባ በሸራተን አዲስ ሲካሄድ፣ ሶማሊያ ውስጥ በአልሸባብ ላይ እየተከናወነ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍና ጽንፈኛውን ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ይፋዊ ጥያቄ ቀርቦላታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላም ሲባል በኢጋድ የቀረበላትን ጥያቄ ስትቀበል የቆየች ሲሆን፣ አሁንም የቀረበላትን ጥያቄ ተቀብላ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች በአካባቢው ከተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይልና በቅርቡ ሶማሊያ ከገባው የኬንያ ጦር ኃይል ጋር ተቀላቅለው አንድ የተጣመረ ኃይል እንዲፈጠርም ተወስኗል፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ መግባታቸውን ሲያስተባብል የነበረው መንግሥት፣ ኢጋድ ከወሰነ ግን ሊዘምት እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በመሩት የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ነበር ኢትዮጵያ በአልሸባብ ላይ ለሚካሄደው ዘመቻ ድጋፍ እንድትሰጥ በይፋ ጥያቄው የቀረበላት፡፡
አምባሳደር ዲና ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያን የሽግግር መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረትን የሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልና ኬንያን የምትረዳው በወታደራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በዲፕሎማሲያዊና በተለያዩ መንገዶች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ድጋፍ ሁሉን አቀፍ መሆኑን አመልክተው፣ የኢጋድ መሪዎች አልሸባብን ለመምታት በሚደረገው ጦርነት የኢትዮጵያ እገዛ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አምነውበታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳንና በሱዳን መካከል በምትገኘው አወዛጋቢዋ የአቢዬ ግዛት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሥር ያሰማራቻቸው የሰላም አስከባሪ ወታደሮቿ በድርጅቱ ከፍተኛ አድናቆት ያገኙ መሆኑን በማስታወስ፣ በአካባቢው ለሰላምና ለደኅንነት የምታደርገው አስተዋጽኦ በሶማሊያም እንዲቀጥል ነው ኢጋድ ጥሪውን ያቀረበው፡፡
የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶማሊያ የሚሰማራውን የተጣመረ ወታደራዊ ኃይል ለማንቀሳቀስ እየተነጋገሩበት መሆኑን፣ በአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ራምታኔ ላማምራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን በመቃወም በሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ጥሪ ወደ አካባቢው የዘመተው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል፣ ቡድኑን በታትኖ ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ መመለሱ የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ከፈረጀቻቸው አምስት የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች መካከል፣ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት አልሸባብ አንዱ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment