Wednesday, November 30, 2011

በሆስተሷ ላይ ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠረው የመከላከያ ምስክሬ ታስሯል አለ


•    ከሙያ ምስክር በስተቀር ምስክሮቹን አሰምቶ ጨረሰ
•    ተከሳሹ የ6,778,688 ብር የጉዳት ካሳ ክስም ተመሥርቶበታል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የበረራ አስተናጋጅ የነበረችውን ወ/ሮ አበራሽ ኃይላይን ዓይኖች በማጥፋት ተጠርጥሮ ክስ የተመሠረተበት የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ፣ የመከላከያ ምስክሩ መስክሮ ሲወጣ ከፍርድ ቤት በራፍ ላይ ተይዞ መታሰሩን በትናንትናው ዕለት ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ‹‹የማውቀው፣ የሰማሁት ወይም የደረሰኝ መረጃ የለም፤›› ብሏል፡፡

ተጠርጣሪ ተከሳሹ በትናንትናው ዕለት ቀሪ መከላከያ ምስክሮቹ ተሰምተው፣ ፍርድ ቤቱ ቀሪ የሙያ መከላከያ ምስክርና የሰነድ ማስረጃዎችን ለመስማትና ለመቀበል ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ፣ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻ ‹‹ክቡር ፍርድ ቤት መከላከያ ምስክሮቼን እያሳደዷቸው ነው፤ ፖሊሱ የመከላከያ ምስክሬ የምስክርነት ቃሉን ሰጥቶ ሲወጣ ከችሎት በራፍ ላይ ተይዞ ታስሯል፡፡ ማነው የሚጠብቀኝ?›› በማለት አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ‹‹ከጠበቆችህ ጋር ተነጋግረህ አመልክት›› ብሎታል፡፡ 

አቶ ፍሰሐ ያቀረበውን ክስ በሚመለከት የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙት ኃላፊ ኮማንደር አበበ ዘሚካኤልን አነጋግረናቸው፣ ‹‹ተፈጸመ ስለተባለው ነገር ምንም አናውቅም፡፡ እንደፌዴራል ፖሊስ ሕግ አስከባሪን ማሰር፣ ማንገላታትና ማስፈራራት የተከለከለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኮማንደር አበበ ጨምረው እንዳስረዱት፣ ድርጊቱ በተቋም ደረጃ ያልተፈጸመ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ነገር ከዓላማ ውጭ የሆነና በሪፖርትም ደረጃ ቢሆን ያልቀረበ ነው፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት 8፡45 ሰዓት ሲሆን ተሰይሞ፣ የተጠርጣሪ ተከሳሽ ፍስሐ ታደሰ ቀሪ ሁለት መከላከያ ምስክሮችን አድምጧል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን በይደር ለትናንትና ቀጥሮት የነበረው፣ በአደጋ ምክንያት አንድ ምስክር በመቅረታቸውና የተያዘው ጭብጥ በዕለቱ ቀርበው ከነበሩት ሁለት ምስክሮች ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ቢሆንም፣ አደጋ ደርሶባቸዋል የተባሉት መከላከያ ምስክር ለትናንትናም ባለመድረሳቸው፣ የተከሳሽ ጠበቆች ‹‹ሁለቱ ይበቁናል›› በማለታቸው ቃለ መሐላ ፈጽመው መስክረዋል፡፡

ለሁለቱም መከላከያ ምስክሮች የተከሳሽ ጠበቆች ባቀረቡት ‹‹የት ነው የምትተዋወቁት? ከመቼ ጀምሮ? እንዴትና በምን ሁኔታ?›› ለሚሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት መከላከያ ምስክሮቹ እንደገለጹት፣ ተከሳሽና ተጐጂ የቅርብ ጐረቤቶቻቸው ናቸው፡፡ ሁለቱንም የተዋወቋቸው በግምት ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ካወቋቸው ጀምሮ በጣም የሚዋደዱና የሚያስቀኑ ባልና ሚስት እንደነበሩ ገልጸው፣ ቤት ገዝተው ወደነሱ አካባቢ (ቦሌ አካባቢ) ሲመጡ ተጋብተው በመምጣታቸው መቼ እንደተጋቡ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ በዓመት ሦስት ጊዜ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተሰባስበው እንደሚወያዩ አስረድተው፣ ፀባቸውንም ሆነ የደረሰውን አደጋ የሰሙት ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች ለትናንትና በሦስተኛ መከላከያ ምስክርነት ሊያቀርቧቸው የነበሩ ግለሰብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ ሌላ ተለዋጭ የሙያ የመከላከያ ምስክር ለማቅረብ ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የሰነድ ማስረጃን በሚመለከት ከዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልና ከ22 ማዞሪያ ከፍተኛ ክሊኒክ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የሚያቀርቡትን ማስረጃ በሚመለከት ቢሮው ጠፍቶባቸው አፈላልገው ቢያገኙትም፣ ከሬጅስትራር የወጣው ደብዳቤ ቁጥር የተሳሳተ በመሆኑ በድጋሚ እንዲታዘዝላቸው ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል፤ በድጋሚ እንዲጻፍም ትዕዛዝም ተላልፏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች ቀሪ የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡና ተለዋጭ የሙያ ምስክርን ለመስማት ለኅዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተጠናቋል፡፡

ተጠርጣሪ ተከሳሽ ፍስሐ ታደሰ በሆስተሷ ላይ ባደረሰው ጉዳት ጥቅምት 8 ቀን 2004 ዓ.ም. የተጻፈ የ6,778,688 ብር የጉዳት ካሳ ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ፍትሐ ብሔር ቀጥታ ክስ ተመሥርቶበታል፡፡ ክሱ እንደሚያስረዳው ሆስተሷ ዕድሜዋ 36 ዓመት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ 11 ዓመታት ሠርታለች፡፡ በየወሩ 12 ሺሕ ብር ወርኃዊ ደመወዝና 500 የአሜሪካ ዶላር ይከፈላታል፡፡ በድምሩ በወር (ዶላሩ አሁን ባለው ምንዛሪ ታስቦ) 20,551 ብር ይከፈላታል፡፡

በመሆኑም አበራሽ የጠየቀችው ዳኝነት ዕድሜዋ 36 በመሆኑና የጡረታ መውጫ ጣሪያ ዕድሜ 60 ስለሆነ፣ ወርኃዊ ደመወዟ ዕድገት ሳይጨመርበት የ24 ዓመት ደመወዝ አሁን ባላት የወር ደመወዝ ተባዝቶ 5,918,688 ብር እና ጡረታ ከወጣች በኋላ የሚከፈላት የጡረታ አበል (ከማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ማረጋገጥ ይቻላል) በወር 7,000 ብር (አማካይ ዕድሜ 70 ዓመታት ታስቦ) ለአሥር ዓመታት 840,000 ብር እንዲከፈላት መጠየቋን የክስ አቤቱታው ያስረዳል፡፡

No comments:

Post a Comment