Wednesday, November 23, 2011

ደረጀ መኰንን ከዚህ አለም በሞት ተለየ


‹‹ነፍሱ ሙዚቃን ለመስጠት የተፈጠረች ነች፡፡ እያንዳንዱ ህዋሱም እንዲሁ፡፡ ደረጀ መኰንን የሙዚቃ ጂኒየስ ነበር፡፡ በጣም የሚያሳዝነው አሁን ከኛ ጋር የለም፡፡ ነፍሱን ያሳርፋት፡፡››

የታዋቂውን ሙዚቀኛ፣ አቀናባሪና ፕሮዲውሰር ደረጀ መኰንን (ዲጄን) ሞት ተከትሎ ሙኒት መስፍን የተናገረችው ነው፡፡

ደረጀ የተለያዩ ትውልዶችን ማስተሳሰር የቻለ ሙዚቀኛ እንደሆነ የሚቀርቡት ሙዚቀኞች ይናገራሉ፡፡ ከአስራ አንድ ልጆች መካከል አምስተኛው ልጅ ሲሆን፣ በኪቦርድ አጨዋወቱ ብዙዎች ያደንቁታል፡፡ አሁን ላሉ ሙዚቀኞችም መሠረት እንደሆነም ይመሰክራሉ፡፡

በዚያን ጊዜ ታዋቂ ከነበረው ዳሎል ባንድ ጋር ከመሥራቾቹ አንዱ ሲሆን፣ ከታዋቂው የቦብ ማርሌይ ልጅ ዚጊ ማርሌይ ጋር የሁለቱ አልበሞች ኮንሺየስ ፓርቲ እ.ኤ.አ በ1988 እና ዋን ብራይት ደይ በ1989 አልበሞቹ ጋር የሙዚቃ ጉዞ አድርጓል፡፡

ከሃያ ዓመት በፊት አካባቢ ችካጐ ውስጥ ‹‹ጊዜ›› የሚባል ባንድ ሲመሠረት በወቅቱም ሬጌ ሙዚቃ በመጫወት ከፍተኛ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን አትርፏል፡፡ ብዙ ሙዚቃ መሣርያዎችን በመጫወት የሚታወቀው ደረጀ ለጊታርም ጥልቅ ፍቅር ነበረው፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ሙዚቃዎችን በመሞከር በብዙ ሙዚቀኞች ሥራ አሳይቷል፡፡
የጂጂን የመጀመርያ አልበም ‹‹አንድ ኢትዮጵያ›› በ1970ዎቹ ፕሮዲውስ ያደረገው ደረጀ፣ የአይቤክስ ባንድ ኪ ቦርድ ተጫዋች ነበር፡፡

ማሕሙድ አሕመድን በሦስት አልበሞቹ ያጀበው አይቤክስ ባንድ ሥራዎቹ በኢትዮጲክስ ስድስተኛው፣ ሰባትና አሥራ ዘጠነኛው ቮሊዩም ላይ ይገኛሉ፡፡ የዳሎል ባንድም ቺካጐ ውስጥ ሬጌ በመጫወት ታዋቂነትን ሲያገኝ ዚጊ ማርሌይንም በሙዚቃ ጉዞ ከማጀቡም በላይ ማርሌይ ዓለም አቀፉን የግራሚ ሽልማት ሁለቴ ባሸነፈበት ሁለት አልበሞቹ ተሳትፏል፡፡ በዚህም ደረጀ መኰንን ዓለም አቀፉን የግራሚ ሽልማት ለመቀበል ችሏል፡፡

ደረጀ መኰንን ከታዋቂዎቹ ማህሙድ አህመድ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አስቴር አወቀ፣ ኤፍሬም ታምሩን ጨምሮ ሙዚቃዎችን የሠራ ሲሆን፣ ከአሁኖቹም አዲሶቹ ሙዚቀኞች ለቴዲ አፍሮ ሙዚቃ እየሠራ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሙሉጌታ ገሠሠን አልበም የሠራው እሱ ነው፡፡

ብዙዎች ደረጀን ከልቡ ወይም ከነፍሱ ሙዚቃ የሚጫወት ሲሉ ያሞግሱታል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የቅርብ ጓደኛው የሆነውና የጤዛን ፊልም ሙዚቃ በመሥራት የሚታወቀው ጆርጋ መስፍን አንዱ ነው፡፡ ጆርጋ እንደሚናገረው፣ ከደረጀ ጋር የሚተዋወቀው ከአሥራ ሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ ከመተዋወቃቸው በፊትም የሱን ሙዚቃ ያደንቅ ነበር፡፡ እንደአስተማሪዬ እቆጥረዋለሁ የሚለው ጆርጋ፣ ከሌሎቹም ሙዚቀኞች ለየት ያለ እንደነበር ጨምሮ ይናገራል፡፡

‹‹እንደ ታላቅ ወንድሜ ነው የምቆጥረው፡፡ ብዙ ሙዚቃን እንዲሁም ሕይወትን ያስተማረኝ ሰው ነው፤›› በማለትም ይገልጻል፡፡ እንደሱ አገላለጽ ከሆነ፣ ሙዚቃን በስሜት ሲሆን የሚሠራው ሰው እንዲያጨበጭብለት ሳይሆን፣ በተመስጦ ይሠራ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ‹‹የሚገርመው መድረክ ላይ ሲጫወት ፊቱ ይቀያየራል፡፡ ዓይኔን መንቀል አልችልም ነበር፤›› በማለት ጆርጋ ያስረዳል፡፡

‹‹ሙዚቃን የሚሠራው በጥልቀት ነው›› የሚባልለት ይኼ ሙዚቀኛ፣ ‹‹የማኅበረሰቡን ኑሮ በሙዚቃ ውስጥ ማንፀባረቅም ይችልበታል›› ይሉታል፡፡ አሁን ላሉት ሙዚቀኞች እንደነ አበጋዝ ሺዎታ፣ ሔኖክ ተመስገን መሠረት የጣለ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

የሞቱ ዜና ብዙዎችን ያስደነገጠ ሲሆን፣ ብዙዎችም ሐዘናቸውን ፊስ ቡክ ላይ የተጫወታቸውን ሙዚቃዎች በማስገባት ለማስታወስ እየሞከሩ ነው፡፡ ጆርጋ እንደሚለው ትልቅ ሙዚቀኛ ነው ያጣነው፡፡ ሌሎችም ይኼንን አስተያየት በማንፀባረቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ኅዳር 14 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደሚፈጸም ተገልጿል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment