Sunday, February 19, 2012

በኮንቴይነር ታሽገው ወደ ዓረብ አገሮች ሲጓጓዙ ከነበሩት 11 ኢትዮጵያውያን ሞተው ተገኙ


በሕገወጥ መንገድ ከ70 በላይ ዜጐችን በኮንቴይነር አሽጐ ጉዞውን ወደ ዓረብ አገሮች መሸጋገሪያ ድንበር ያደረገ ተሽከርካሪ አፋር ውስጥ በፖሊስ ክትትል ሲያዝ፣ 11 ዜጐች ሞተው መገኘታቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡ ሕገወጥ ተግባር እየፈጸመ በመሆኑ ፖሊሶች ክትትል እያደረጉበት እንደሆነ ሳይሰማ እንዳልቀረ የገመተው ሾፌር፣ ተሽከርካሪውን በአፋር ክልል ውስጥ ለጊዜው ትክክለኛ የቦታው ስም ባልታወቀ አካባቢ አቁሞ መሰወሩን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት ጥብቅ ክትትል እያደረገ ቢገኝም፣ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በብዛት ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከትግራይና ከደቡብ ክልሎች የተመለመሉ ከ70 በላይ ዜጐችን በሕገወጥ መንገድ በኮንቴይነር አሽጐ ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ፣ ለ10 ወንዶችና (አንዱ የአምስት ልጆች አባት ነው) ለአንዲት ሴት ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡

የአሥራ አንዱም ሟቾች አስከሬን ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ከገባና ከተመረመረ በኋላ ቤተሰቦቻቸው እየወሰዱ እንደሚገኙ ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ባደረገው ፈጣን ክትትል ደርሶ የታሸገውን ኮንቴይነር ባይከፍተው ኖሮ፣ ኮንቴይነሩ ውስጥ የነበሩት በሙሉ ከሟቾቹ በተወሰነ ልዩነት ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችል እንደነበር የተናገሩት ምንጮቹ፣ አሁንም ቢሆን ከሞት የተረፉት ቀሪዎቹ ዜጐች በሕክምና ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ጂቡቲ ለመግባት ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩትና ነፋሻማ በሆነ ቦታ ባይቆም፣ ፖሊስ በፍጥነት ባይደርስና አካባብው በረሃው ቢሆን ኖሮ ሁሉም ያልቁ እንደነበር የተረፉትን የሚያክሙ ዶክተሮች መናገራቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ዜጐችን በመመልመል ወደ ተለያዩ የዓረብ አገሮች ከሚልኩባቸው አካባቢዎች መካከል ከወሎ ከሚሴ በባቲ ወደ አፋር፣ ከዚያም በኦቦክ ወደብ አድርገው ወደ የመን ይጓጓዛሉ፡፡ ከመተማ ወደ ሱዳን፣ ከጅጅጋ ካራማራን በእግር አቋርጠው ወደ ሶማሊያ ሳሶ ወደብ በመሄድ ወደ የመን፣ ባህሬን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ወደ ሌሎችም የዓረብ አገሮች የሚጓዙባቸው ዋና ዋና ቦታዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በኮንቴይነር ታፍነው የሞቱትን 11 ዜጐችን በማስመልከት የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራና አሠሪዎች አገናኝ ኤጀንሲዎች ማኅበር በሰጠው አስተያየት፣ የዜጐቹ ሕይወት ማለፍ አሳዛኝና ለቀጣዩም አሳሳቢ መሆኑን ገልጾ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መንግሥት ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥርያ ቤቶች፣ ከማኅበሩና ከሁሉም ዜጐች ጋር ሆኖ ማስቀረት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

No comments:

Post a Comment