Sunday, December 25, 2011

የሽብር ወንጀል ክስ ተጠርጣሪዎች ተቀጠሩ


-    ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ጥፋተኛ ተብለዋል

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው እነ ኤልያስ ክፍሌ የክርክር ማቆሚያ ንግግር እንዲያደርጉ፣ እነ አንዱዓለም አራጌ ደግሞ ቀሪ የዓቃቤ ሕግን የኦዲዮና ቪዲዮ ማስረጃ ለማየት ለታኅሣሥ 17 እና 19 ቀን 2004 .. ተቀጠሩ፡፡ ለሁለቱም ተጠርጣሪ ተከሳሾች ለታኅሣሥ 13 ቀን 2004 .. ቀጠሮ የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የወንጀል ችሎት ሲሆን፣ በእነ ኤልያስ ክፍሌ ላይ የመከላከያ ምስክሮችን መስማት የጀመረው ታኅሣሥ 11 ቀን 2004 .. ከሰዓት በኋላ ነበር፡፡

በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸው የመኢዴፓ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፣ የአውራ አምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ሒሩት ክፍሌና መምህርትና አምደኛ ርዕዮት አለሙ ናቸው፡፡

የአምስተኛ ተከሳሽ ርዕዮት ዓለሙ ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ፣ የመከላከያ ምስክሮች ከመሰማታቸው በፊት ምስክሮቹ በምን ላይ እንደሚመሰክሩ ባስያዙት ጭብጥ፣ የሽብርተኝነት መሠረተ ሐሳብ ከዓለም አቀፍ ሕጎች አኳያ ለሙያዊ ማብራሪያ በምስክርነት ያቀረቧቸው የቀድሞው የቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት አባል የነበሩት / ያዕቆብ ኃይለማርያም ሲሆኑ፣ በፎቶ የተደገፈ ዘገባ ማቅረብ ከሕገ መንግሥታዊ መብቶች አንፃር ደግሞ ሙያዊ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ያቀረቧቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ፣ የኦህኮ ሊቀመንበርና የመድረክ ከፍተኛ አመራር / መረራ ጉዲና ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባለሙያዎቹ የሚሰጡት ማብራሪያ ከክሱ ጭብጥ ውጭ በመሆኑና የሕግ ትርጉም የሚሰጠውም ፍርድ ቤቱ በመሆኑ እንደሚቃወም በማመልከቱ፣ ፍርድ ቤቱም የጠበቃውን ጭብጥና ምስክሮችን ሳይቀበል በመቅረቱ፣ ሁለቱም ዶክተሮች ሳይመሰክሩ ወይም በቀረበው ጭብጥ አማካይነት ማብራሪያ ሳይሰጡ ተመልሰዋል፡፡

ተከሳቹ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ከማሰማታቸው በፊት በወንጀል ሕግ 142(1) መሠረት የተከሳሽነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

የመኢዴፓ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር በሰጡት የተከሳሽነት ቃል፣ በሕግ የተቋቋመና ፈቃድ ያለው የፖለቲካ መሪ መሆናቸውን፣ በሕጋዊ መንገድ እንደሚቃወሙ፣ የተቃውሞ ወረቀት እንደሚበትኑና ይኼም ከፓርቲው ፋይል ጋር የተያያዘ መሆኑን፣ ከውጭ አገር ከአጎታቸው ልጅ ገንዘብ እንደሚላክላቸው፣ ከኤልያስ ክፍሌ ጋር በፖለቲካ መሪነትና የጋዜጠኛነት ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኛ ውብሸት በሰጠው የተከሳሽነት ቃል ጋዜጠኛ መሆኑን፣ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደለትንና በአዲሱ የመገናኛ ብዙኀንና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ተከትሎ እንደሚሠራ፣ መከሰስም ካለበት በዚሁ አዋጅ መሠረት መከሰስ እንዳለበት፣ በኢሜል አድራሻ ተለዋውጧል የተባለው ጽሑፍ የትርጉም ስህተት እንዳለበት፣ እሱ ሰኔ 12 ቀን 2003 .. በቁጥጥር ሥር ውሎና 13 ፍርድ ቤት ቀርቦ እያለ፣ ሰኔ 23 ቀን 2003 .. ተጻጻፈ የተባለ ኢሜል እንደ ማስረጃ እንደቀረበበት፣ አባቱ ዓይናቸውን ታመው እሱ ዘንድ ሆነው ሲታከሙ፣ ውጭ አገር የሚኖረው ወንድሙ ስለ አባታቸው ሲጠይቀው ‹‹ኦፕሬሽን እየተደረገ ነው›› ያለውን፣ ጦርነት የሚመራ የጦር ጄነራል ተደርጎ መቅረቡን፣ ኤልያስ ክፍሌ አንድ ጊዜ እንደደወለለትና ጓደኛውም ስለነበር ሁለት ጊዜ በድምሩ 300 ዶላር እንደላከለት ተናግሮ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ትክክለኛ ፍርድ ይሰጠኛል›› የሚል እምነት እንዳለው በመግለጽ የተከሳሽነት ቃሉን አጠቃሏል፡፡ሒሩት ክፍሌም በሰጠችው የተከሳሸነት ቃል የማንም ፓርቲ አባል አለመሆኗን፣ 97 የቅንጅት አባል እንደነበረችና ዘመዶቿ በውጭ አገር ስላሉ ገንዘብ እንደሚልኩላት፣ ይህም ከግንቦት 7 እና ከኤርትራ ተልኮልሻል መባሉን ተናግራለች፡፡

መምህርትና አምደኛ ርዕዮት ዓለሙ በሰጠችው የተከሳሽነት ቃል ከመምህርነቷ በተጨማሪ በአዲስ ፕሬስ፣ በቼንጅ መጽሔት፣ በፍትሕ ጋዜጣ አምደኛና በኤፍኤም 96.3 ላይ መሥራቷን፣ ደበበ እሸቱ አገናኝቷት ከኤልያስ ክፍሌ ጋር ተዋውላ እየከፈላት በድረ ገጹ ላይ የፖለቲካ ዘገባዎችን ከሁለት ወራት በላይ መሥራቷን፣ 2003 .. መጋቢት ወር መጨረሻ ‹‹በቃ›› የሚል ጽሑፍ በከተማው ይጻፍ ስለነበር ፎቶ አንሺና ላኪልኝ ሲላት አንስታ መላኳን ተናግራለች፡፡

ፍርድ ቤቱ እንዲያውቀው በሚል የገለጸችው ደግሞ በማዕከላዊ ታስራ በነበረችበት ወቅት፣ የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዳነጋገሯት፣ በሌሎቹ ላይ ከመሰከረች ነፃ እንደምትሆን ስትጠየቅ አለመስማማቷን፣ 25 እስከ  ዕድሜ ልክ ትታሰሪያለሽ ብትባልም አለመስማማቷን፣ ‹‹ታዲያ ለምን ጫካ አትገቢም›› እንዳሏት፣ 13 ቀናት በጨለማ ቤት መቆየቷን፣ አንድ መርማሪ እያሳሳቃት ሌላዋ ተደብቃ ልትቀርፃት ስትል ስላየቻት ራሷን መሸፈኗንና ላለመቀረጽ መሞከሯን፣ በሰላማዊ መንገድ በግልጽ ስለምትቃወም ጥቃት እየደረሰባት መሆኑንና በኢሜል ተላልካለች የተባለውን የሰነድ ማስረጃ በተሳሳተና ከሕገ መንግሥቱ ጋር በሚጋጭ መልኩ መተርጎሙን፣ የማታውቀው መልዕክት በኢሜሏ ላይ መካተቱንና ተርጓሚውን በሚያስገምት መልኩ መተርጎሙንም ተናግራለች፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱን ጨምሮ የመከላከያ ምስክሮቹም ከተከሳሾቹ የተከሳሽነት ቃል ያልራቀ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው የመከላከያ ምስክሮቹ ቃል ተጠቃሏል፡፡ የክርክር ማቆሚያ ንግግር ለማድረግም ለታኅሣሥ 17 ቀን 2004 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በእነ አንዱዓለም አራጌ (በአገር ውስጥ ሆነው ጉዳያቸውን በሚከታተሉ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ) ለሦስት ቀናት 30 የሰዎች ምስክሮቹን ካሰማ በኋላ፣ ታኅሣሥ 12 ቀን 2004 .. የኦዲዮና ቪዲዮ ማስረጃዎችን ማሳየት የጀመረ ቢሆንም፣ አሰምቶና አሳይቶ ባለማጠናቀቁ ለታኅሣሥ 19 ቀን 2004 .. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

ሌላው ለአሸባሪው የኦብነግ ታጣቂ ድጋፍ በመስጠትና የሉዓላዊት አገርን ሕግ ጥሶ በመግባት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኛ መርቲን ካርል ሽብዬና ፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን ከርል ፐርሰን የተባሉት የስዊድን ጋዜጠኞች ታኅሣሥ 11 ቀን 2004 . ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

ጋዜጠኞቹ ጥፋተኛ በተባሉበት ሁለት የወንጀል ክሶች በድምሩ እስከ 18 ዓመታት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ ሐሳቡን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ጋዜጠኞቹ ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱ በመሆናቸውና የታሰሩትም ከአገራቸው ውጭ በመሆኑ ቅጣቱ ቀሎ እንዲወሰንላቸው ተከላካይ ጠበቆቻቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለታኅሣሥ 17 ቀን 2004 .. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡