Wednesday, October 8, 2014

በሎሚ፣ አዲስ ጉዳይና ፋክት መጽሔቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት ባስቻለው ችሎት በሎሚ፣ አዲስ ጉዳይና በፋክት መጽሔቶች ላይ የእስር ቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ።

ፍርድ ቤቱ መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎት መጽሔቶቹ ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳት፣ ሀሰተኛ ወሬዎችን በህትመት መልክ በማሰራጨትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር በሚል ክስ የቀረበባቸው ሶስት መፅሔቶችና የአሳታሚ ድርጅቶች ስራ አስኪያጆች የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፣ አንደኛ ተከሳሽ የፋክት መፅሔት ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ፋጡማ ኑሪዬ ላይ በፖሊስ ከሚያዙበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ በሶስት ዓመት ከአሥራ አንድ  ወር እስራትና የአሳታሚው ንብረት በመንግስት እጅ እንዲቆይ ወስኗል፡፡


ሌላኛው ተከሳሽ የሎሚ መፅሔትና የመፅሔቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ ላይ ፍርድ ቤት የሶስት ዓመት ከሶስት ወር እስራትና በተመሳሳይ የአሳታሚው ንብረት በመንግስት እጅ እንዲቆይ ውሳኔ አስተላልፏል።

ሶስተኛው ተከሳሽ የአዲስ ጉዳይ መፅሔትና የመፅሔቱ ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ ሲሆኑ ፍርድ ቤት በተመሳሳይ የሶስት ዓመት ከሶስት ወር እስራትና የአሳታሚው ንብረት በመንግስት እጅ እንዲቆይ ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ተከሳሾቹ በሌሉበት ሲሆን ሶስቱም ተከሳሾች በፖሊስ ተፈልገው ተይዘው ቅጣቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ለፖሊስ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የፈጸሟቸው ወንጀሎች በሂደት ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉና ህብረተሰቡን ከአደጋ ለመከላከል ታስቦ የተላለፈ ውሳኔ ነው ብሏል።

http://www.ertagov.com

No comments:

Post a Comment