Wednesday, February 5, 2014

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተከሰሱ ሙስሊሞች የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ሳያሰሙ ቀሩ

-477 የመከላከያ ምስክሮችን ቆጥረዋል

በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ግብ አስቀምጠው የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ተጠርጥረው ከታሰሩና ክስ ከተመሠረተባቸው ሙስሊሞች መካከል፣ አሥራ ዘጠኙ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማት የሚጀምሩት ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም ሳያሰሙ ቀሩ፡፡

በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ አላቸው በሚል የተከሰሱት ተጠርጣሪዎች፣ 477 ምስክሮቻቸውን ለማሰማት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የተገኙ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ የመከላከያ ምስክር በማን ላይ ምን እንደሚያስረዳ ጭብጥ ባለማስያዛቸው የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ማሰማት አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ምስክሮች ስለሚያስረዱት የምስክርነት ቃል ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ እንዳለባቸው ፍርድ ቤቱ ሲገልጽ፣ ዓቃቤ ሕግም የመከላከያ ምስክሮቹ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ዝርዝራቸውም እንዲደርሰው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለፍርድ ቤቱ አመልክቶ ነበር፡፡



የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የዓቃቤ ሕግን ማመልከቻ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮቹን ቁጥር ከመግለጽ ውጪ የአንዳቸውንም ስም ዝርዝር አላስታወቀም፡፡ በወቅቱ ግን እነሱም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ስም ዝርዝራቸው እንዲሰጣቸው ጠይቀው እንደነበር አስታውሰው፣ የዓቃቤ ሕግ ምላሽ ‹‹ለምስክሮቼ ደኅንነት ስል ስማቸውን መግለጽ አልችልም፤›› የሚል እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም እነርሱም በደንበኞቻቸው የመከላከያ ምስክሮች ላይ ተፅዕኖ እየደረሰ መሆኑን በመጠቆም፣ ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸውን መግለጽ እንደማይፈልጉ ለፍርድ ቤቱ በማሳወቅ የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያነሱት ሥጋት ስህተት መሆኑን በመጠቆምና እውነት ከሆነ እሱም መከታተልና ሁኔታውን ማጣራት እንደሚፈልግ በመግለጽ፣ ማን የትና በማን ላይ የማሰፈራራትም ሆነ ሌላ ተፅዕኖ ያደረሰ ካለ ተጠርጣሪዎች ወይም ጠበቆቻቸው ግልጽ እንዲያደርጉ ችሎቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪ ጠበቆች ምላሽ እንዲሰጡ ሲጠይቃቸው፣ የመከላከያ ምስክሮቻቸው ማን በማን ላይ ምን እንደሚያስረዳ ለማቅረብ የአንድ ወር ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጥያቄያቸውን በመቀበል ለመጋቢት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ለተከታታይ 15 ቀናት የመከላከያ ምስክሮችን ቃል እንደሚሰማ አስታውቋል፡፡
http://ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment