Monday, February 10, 2014

"መጡ አስወጡኝ..." አቶ ሰውነት ቢሻው፣ የቀድሞው ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ

አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ‹‹ሰውነት›› ሆነውት ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል በአስገራሚና በአነጋጋሪ ጉዞ ዋሊያዎቹን መርተዋል፡፡

ከቡድኑ ያልተጠበቁ ቁም ነገሮችም ተገኝተዋል፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በጀመረው መንገድ መቀጠል ያልቻለው የዋሊያዎቹ ስብስብ የጀመረውን የውጤት መንገድ መሳትና ጅማሬው ላይ እንደነበረው ላለመቀጠሉ ምክንያት ከተደረጉት መካከል፣ በአቶ ሰውነት የሚመራው የአሠልጣኞች ቡድን ተጠያቂ ሆኖ እንዲሰናበት መደረጉ ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ረቡዕ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ሆኗል፡፡ ስንብቱን ተከትሎ ነገሮች ግን በተቋማዊ ማንነት ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ ግለሰቦች ማነጣጠር ጀምረዋል፡፡ ግልጽ ለማድረግ የአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስንብት ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው እየተባለ ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ የስፖርት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር ሲነገር ተደምጧል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ ለአሠልጣኝ ሰውነትና ረዳቶቻቸው ስንብቱን ያደረገው ተገቢውን ግምገማ ካካሄደ በኋላ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይባስ ብሎም ‹‹በቻን ውድድር ዋንጫ እናመጣለን ግን ስንት ብር እንደምንሸለም ንገሩን›› በማለት ዋሊያዎቹ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ጭምር የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡ ያም ሆኖ በተቋሙ አሠራርና እግር ኳሱ በሚመራበት ደካማና ጠንካራ ጐን ላይ መነጋገር፣ መተቻቸትና መነቃቀፍ ሲገባ አቅጣጫውን ስቶ ወደ ግለሰቦች ሰብዕና ማዘንበሉ መነጋገሪያ መሆን ጀምሯል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው፣ በተለይም የእሳቸው ስንብት ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ስለሚባለውና በሌሎችም ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ባለፈው ዓርብ ከደረጀ ጠገናው ጋር ባደረጉት የአፍታ ቆይታ የሚከተለውን ብለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአሠልጣኝነትዎ መነሳትዎን ተከትሎ የተለያዩ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን ከፖለቲካ ጋር በማገናኘት እያስነበቡ ናቸው፡፡ ጐል ዶት ኮምና ሌሎችም ዘገባዎች አሠልጣኝ ሰውነት ከኃላፊነት እንዲነሱ ምክንያት የሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡዋቸው መግለጫዎች የተቋሙንና በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለውን ደካማ የስፖርት መሠረተ ልማት ስለሚተቹ ነው ይላሉ፡፡ የሚሉት ይኖርዎታል?

አቶ ሰውነት፡- ይኼን አላውቅም፣ ሲጀመርም እኔ የእግር ኳስ አሠልጣኝ እንጂ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ ለስንብቴም በዚህ መስመር የመጣ ውሳኔ ነው የሚል አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ሊሆንም እንደማይችል ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም የማውቀው ኳስና ኳስን ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለስንብትዎ ምክንያት የሚሉት ሌላ ተጨማሪ ነገር ይኖራል የሚል እምነት አለዎት?


አቶ ሰውነት፡- ተሰናብተሃል ከሚለው የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ውጪ የተለየ ምክንያት ስለሚባለው ነገር ደግሜ ደጋግሜ ላረጋግጥልህ የምችለው ምንም ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ እዚህ ላይ ሌላ የምጨምረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለምን አሰናበተኝም የሚል መከራከሪያ የለኝም፡፡ አንድ እንድታውቅ የምፈልገው እግር ኳሱ መመራት ያለበት በሙያተኞችና በሙያተኞች ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ በሙያተኞች እየተመራ አይደለም ብለው ያምናሉ?

አቶ ሰውነት፡- ይኼን ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? ምክንያቱም ባለፈው ቅዳሜ በተደረገው የብሔራዊ ቡድኑ ግምገማ ወቅት በግልጽ የተነገረ አይደለም እንዴ?

ሪፖርተር፡- በእርስዎ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማምራቱ በፊት ዋንጫውን ይዞ እንደሚመጣ፣ ይህንኑ መነሻ ያደረጉት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ዋንጫ ማግኘት ካልሆነ ደግሞ ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ያለውን ይዞ ለማጠናቀቅ ዕቅድ እንደነበራቸው ተነግሯል፡፡ እርስዎና ተጨዋቾቹ ደግሞ ‘ዋንጫ እናመጣለን፣ ነገር ግን ከዚያ በፊት እኛ ዋንጫ ብናመጣ ፌዴሬሽኑ ምን ያህል የገንዘብ ሽልማት ይሰጠናል?’ የሚል የመደራደሪያ ቅድመ ሁኔታ ማቅረባችሁም ተሰምቷል፡፡

አቶ ሰውነት፡- ብሔራዊ ቡድን ቀርቶ የትኛውም ሰው የዕለት ተዕለት ክንውኑን ለማስፈጸም ዕቅድ ይኖረዋል፡፡ ዕቅድ ለምን ታቀደ ብሎ ነገር የለም፣ ማቀድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በእግር ኳስ እንደ ፋብሪካ የተጠየቀው ሁሉ መቶ በመቶ ይሳካል ማለት አይቻልም፡፡ ፋብሪካ እንኳ በመብራትና በመሳሰሉት ምክንያቶች ያቀደውን ያህል ምርት የማያገኝበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እግር ኳስ ደግሞ ከእነዚህ ሁሉ ወጣ ያለ የራሱ መገለጫዎች ያሉት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ በእግር ኳስ ማሸነፍ፣ እኩል መውጣትና መሸነፍ የግድ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች መኖራቸው እየታወቀ ግን ‹‹እሸነፋለሁ›› ብሎ የሚያቅድ የለም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሰላማዊ ጦርነት ውስጥ የሚሆነውን ለመተንበይ ከባድ ነውና፡፡ ውጤትና ውድቀት የግድ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ማንም በሙያው የሚኖር ሰው የምሄደው ዋንጫ እወስዳለሁ ብሎ እንጂ እሸነፋለሁ ብሎ እንዳልሆነም ሊታወቅ ይገባል፡፡ እኔም የተከተልኩት ይህንኑ መንገድ ነው፡፡ ዋንጫ ለማግኘት ነው ብሎ መናገር ሌላው ጥቅሙ ደግሞ ዋንጫ ይዞ ለመምጣት ተብሎ ሳይሆን የተጨዋቾችን ሥነ ልቦና ለመገንባትም ተብሎ ነው፡፡ በውስጤ ያለውን ነገር ማወቅ ለሚፈልግ ሁሉ የምነግረው ለቻን ቀርቶ ለማንኛውም ውድድር ዝግጅት የማደርገው ለዋንጫና ዋንጫ ብቻ መሆኑን እንዲያውቅ ነው፡፡ በዚህ አባባሌ ዛሬ አይደለም ወደፊትም እንደማላፍር ቅንጣት ታህል አልጠራጠርም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ አመራሮች ለቻን ዝግጅት እያደረግን ባለንበት ወቅት መጥተው አነጋግረውናል፡፡ እደግመዋለሁ የምሄደው ዋንጫ ለማምጣት ነው ብዬ ነው የመለስኩላቸው፡፡ ተጨዋቾቹም ይህንኑ ነው ያረጋገጡት፡፡

ሪፖርተር፡- ለቅድመ መደራደሪያነት የተቀመጠውን የገንዘብ ሽልማት በተመለከተ አልመለሱልኝም እኮ?

አቶ ሰውነት፡- እንሸለማለን ወይ ብሎ መጠየቅ በየትም አገር የተለመአ ነው፡፡ ስለዚህ መጠየቅ ምን ነውር አለው?

ሪፖርተር፡- ያወሩት ሌላ የሆነው ደግሞ በተቃራኒው ነውና ዛሬስ ምን ይላሉ?

ሰውነት፡- ከቻን ውድድር ከምድብ ድልድል መውጣት ድክመትን ብቻ የሚያመላክት ሊሆን አይችልም፡፡ ለምን ለሚለው ተያይዘው መነሳት ያለባቸው በርካታ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ማለት ነው፡፡ እነዚያን ነገሮች በዚህ ወቅት አንስቶ ለመከራከር ጊዜው ስላልሆነ አልፈዋለሁ፡፡ ከዚሁ ጋር ሌላው ልንመለከተው የሚገባን፣ ሁሉም እንዳስተዋለውና እንደተከታተለው የቻንን ዋንጫ የወሰደው የሊቢያ ቡድን ነው፡፡ ሊቢያ ግን እ.ኤ.አ. ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ እንደ ኢትዮጵያ ቡድን ቀጥታ ምድብ ድልድል ሳይሆን የገባው የማጣሪያ ማጣርያ አድርጐ ወደ ምድብ ድልድሉ እንዲመጣ ነው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የወሰነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋንጫ ስላላገኘ ወደ ማጣሪያ ማጣሪያ እንዲገባ አልተደረገም፡፡ ምክንያቱም ዋንጫ ማግኘት አንድ ነገር ሆኖ፣ ነገር ግን ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ መሥፈርቶች መኖራቸውን እንረዳለን፡፡ እኛ ግን መሥፈርቶቻችን ዋንጫና ዋንጫ ብቻ ሆነው ብዙ ነገር እየተባለ ነው፡፡ ያውም ከቡድናችን ጀርባ ያለው እውነተኛ መገለጫ ሳይታይ ማለት ነው፡፡ የምናገረው ሳይቆራረጥ እንዲወጣ እፈልጋለሁ፡፡ ዋንጫና ደረጃ ውስጥ አልገባም ተብሎ የሚተቸው የሰውነት ቡድን ከአፍሪካ ምርጥ ሦስት ቡድኖች አንዱ ተደርጐ ተመርጧል፡፡ ካፍ 21 አገሮች ከማጣርያ ማጣርያ ውጪ እንዲሆኑና ቀጥታ ወደ ምድብ ድልድሉ እንዲገቡ ሲወስን፣ የኢትዮጵያ ቡድን በ12 ድምፅ 16ኛ ደረጃ አግኝቶ ነው ወደ ምድብ ድልድሉ የተካተተው፡፡ ይኼ የሆነው ሰውነትን ለመደገፍ ተብሎ አይደለም፣ እውነታው ነው፡፡ ይኼ የሚይሳየው እንደሚባለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ መውደቁን ነውን? በግሌ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ቡድንዎ ከውድድር መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ጐል ማስቆጠር እንኳ እንዳልቻለ ታይቷል፣ እየተተቸም ነው፡፡

አቶ ሰውነት፡- በውድድር ዓለም ያጋጥማል፡፡ ይኼ ታላላቅ የእግር ኳስ አገሮችን ሳይቀር የገጠመ ነው፡፡ ፈረንሳይ እ.ኤ.አ. በ2010 የዓለም ዋንጫ ለድል ከተጠበቁት አንዷ ሆና፣ ነገር ግን ከምድብ ድልድሉ እንኳ ማለፍ ተስኗት የተባረረችበት ሁኔታ ነበር፡፡ የሩቁን ትተን የእግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያለፈው ዓመት አሸናፊ ማንቸስተር ዩናይትድ ዘንድሮ የሚገኝበትን ደረጃ መመልከት በቂ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ሽንፈት እየደረሰበት አሠልጣኝ ዴቪድ ሞይስ አልተባረሩም፣ እየሠሩ ናቸው፡፡ ምክንያት ከተባለ አብሮ መታየት ያለባቸው ነገሮች ስለሚኖሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስንብቱ ተገቢ አይደለም እያሉ ነው?

አቶ ሰውነት፡- አልወጣኝም፣ እኔ ተባርሬ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማደግና የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ ከቻለ ስንብቱን በፀጋ የምቀበለው መሆኑን ደግሜ ደጋግሜ የምናገረው ነው የሚሆነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ሲቀጥረኝ፣ ስምምነታችን ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዳበቃ ነው፡፡ ያንን ደግሞ አሳክቻለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ የቻንን ዋንጫ በሚመለከት አልተነጋገርንም፣ ይኼ ለእኔ ቦነስ ነው፡፡ ሌላው ባለፈው ቅዳሜ በኢሊሌ ሆቴል በተደረገው የብሔራዊ ቡድኑ ግምገማ ላይ አሠልጣኝ ሰውነት በቻን ውድድር ላይ ዋንጫ ስላላመጣ መባረር አለበት የሚል ግምገማ አልቀረበም፡፡ ግምገማው በዋናነት ትኩረት ያደረገው የፌዴሬሽኑ አጠቃላይ አደረጃጀት፣ ጽሕፈት ቤቱና ቴክኒክና ልማቱ ላይ ያለው ድክመት ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽኑ አመራሮች ለስንብትዎ ከጠቀሱዋቸው ምክንያቶች አንዱ፣ በግምገማው ወቅት በእርስዎ ላይ የቀረበውን ትችት መሠረት አድርገው መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡

አቶ ሰውነት፡- እኔም እየነገርኩህ ያለው በግምገማው ላይ የተነሳውን ተጨባጩንና እውነታውን ነው፡፡ ስናገርም ለምን ተሰናበትኩ እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን ስሰናበትና እኔን ጠርተው ሲያነጋግሩኝ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ስለምንፈልግ፣ ለዚያ ደግሞ ጠንካራና ከፍ ያለ ደረጃ ያለው አሠልጣኝ ማምጣት እንፈልጋለን ምን ይመስልሃል ቢሉኝ፣ ውሳኔውን የምቀበለው በደስታ ነበር፡፡ ምክንያቱም የተባለው አሠልጣኝ ቢመጣ የአገሪቱ ወጣት አሠልጣኞች ጭምር ትምህርት ስለሚያገኙበት ማለት ነው፡፡ እውነትም ዓላማው ለዚህም ቢሆን ከተቋሙ ውሳኔ በፊት በክብር መሰናበት እንደሚገባኝ እኔ ራሴ ነበርኩ መልቀቅ እንደሚገባኝ የምጠይቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ንግግርዎ አሁንም በፌዴሬሽኑ የስንብት ውሳኔ ደስተኛ እንዳልሆኑ ያመላክታል፡፡

አቶ ሰውነት፡- መጡ አስወጡኝ፡፡ ከዚያ ውጪ መናገር ካለብኝ ይኼ አሁን ያለው አመራር ስለ ቻን ውድድር ምንም የሚይውቀው ነገር የለም፡፡ ሲጀመር ቡድኑን ለዚህ ሻምፒዮና እንዲበቃ ትልቁን ሚና የተጫወተው የቀድሞው አመራር ነው፡፡ ክብሩም ሆነ ትችቱ የሚገባው ለቀድሞው ነው፡፡ ስለተላለፈብኝ ውሳኔ ከሆነ ጥሩ ነው እቀበለዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አዳዲሶቹ አመራሮች ሲናገሩ እንደሚደመጡት ከሆነ ተቋሙ አዳዲስ አሠራሮችና አደረጃጀቶች ስለሚያስፈልጉት የግድ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ አለብን ነው፡፡ ደስ እያለኝ ነው ይህንንም የምቀበለው፡፡ በግምገማው ፌዴሬሽኑ አሁን ባለበት የትም መድረስ እንደማይችል ነው በአብዛኛው ሲያሳስብ የተደመጠው፡፡ እውነት ሆኖ መመልከት ደግሞ ሌላው የምጠብቀው መሆኑ እንደተጠበቀ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የተደረገው ለለውጥና ለጥሩ ነገር ነው ተብሎ ስለሚታመን እኔም ስንብቱን የምቀበለው በፀጋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎና የረዳትዎችዎ ስንብት ብቻውን መፍትሔ እንደማያመጣ የሚናገሩ አሉ፡፡

አቶ ሰውነት፡- ትልቁና መነሳት ያለበት እኔም መናገር ካለብኝ መናገር የምፈልገው እዚህ ላይ ነው፡፡ የምናወራው ስለ እግር ኳስ ነው፡፡ እግር ኳስ ደግሞ ሙያ ነው፡፡ ይህ ሙያዊ ተቋም ደግሞ መመራትና መተዳደር ካለበት በሙያተኞችና በሙያተኞች ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጪ አሠልጣኝ ማባረር ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡ መፍትሔው ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት መቻል ነው፡፡ ይኼ የተቋሙ መሪዎችና አስተዳዳሪዎችን ጭምር ይመለከታል፡፡ ለዚህ በርካታ ምሳሌዎች ለማንሳት እገደዳለሁ፡፡ አንድ ወታደራዊ ተቋም በአንድ የምህንድስና ሙያ ባለው ሰው አይመራም፡፡ አንድ ተዋጊ የጦር አውሮፕላን የሚያበርን ሙያተኛ አንድ የእግር ኳስ አሠልጣኝ ሊመራው አይችልም፡፡ እግር ኳሱም እንደዚያው ነው፡፡ ይኼ ጥሬ እውነት እስካልገባን ድረስ የምንፈልገው ለውጥ ከወዴትም አይመጣም፡፡ ማሰናበቱና መቅጠሩ ግን ይቀጥል ይሆናል፡፡ እግር ኳስ ኳሱን ጠንቅቀው በሚያውቁ ሙያተኞች መመራት መቻል ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ውሳኔው ከሙያው አኳያ አይመጥነኝም እያሉ ነው?

አቶ ሰውነት፡- እስከዛሬ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ለማሠልጠን ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ በርካታ አሠልጣኞች ተሞክረዋል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሠልጣኞችም ሆኑ የውጭ አሠልጣኞች መጥተው ተሰናብተዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ሙያተኛ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ይዘው ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁ ግን ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም መንግሥቱ ወርቁና ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ ይኼን የምለው ስለተሰናበትኩ አይደለም፣ ቅር የሚለው ካለ በማስረጃ መነጋገርም ይቻላል፡፡ የእግር ኳሱ ቤተሰብ ለውጥ ለውጥ እያለ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ተቋሙ በሙያተኞችና በሙያተኞች ብቻ እንዲመራ ካላደረግን ለውጡም ጩኸት ሆኖ ይቀራል፣ ተቋሙም እንደዚሁ፡፡ ተወደደም ተጠላ ለአገሪቱ እግር ኳስ መሠረቱ ላይ መሠራት አለበት፡፡ ኅብረተሰቡ ተተኪ ተተኪ እያለ ለሚናገረው መልስ የሚሆነው ከእኔ ጀምሮ ይመለከተናል የምንል የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዘን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ አሁን ባለው የሰውነትንም ሆነ የሚመጣውን የአሠልጣኞች ስብስብ በማሰናበትና በመሾም ለውጥ አይታሰብም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ እርስዎ ስንብትና ግምገማ እንመለስና እንዴት አገኙት? ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ በሙያተኞች መመራት እንዳለበት ሁሉ፣ እግር ኳሳዊ ግምገማም መደረግ ካለበት በሙያተኞች ሊሆን እንደሚገባ ደጋግመው አንስተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የበቀደሙ

ግምገማ በእርስዎ አተያይ ትክክለኛ ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ሰውነት፡- ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ከእኔም በላይ አሁን እየጠየቅከኝ ያለኸውም ሆነ ሌሎች የሚዲያ ተቋማት ሁሉ እንደተከታተላችሁት የግምገማ መድረክ ለመሆኑ እምነት አለኝ፡፡ የግምገማው አካሄድ ተሳታፊዎች በሲንድኬት (በቡድን) ተከፋፍለው እያንዳንዱ በብሔራዊ ቡድኑ የቻን ተሳትፎም ሆነ በሌሎች አስተዳደራዊና ቴክኒካዊ ክፍተቶች ላይ የሚመስለውንና ያመነበትን ብሏል፡፡ በዋናነት ግን ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት ማነቆ ተደርጐ በሁሉም የቡድን ተወካዮች እንደ ድክመትና ክፍተት ተደርጐ ሲነገር የተደመጠው፣ የተቋሙ ጽሕፈት ቤትና ቴክኒክና ልማቱ ላይ የተሠራ ሥራ እንዳልነበረ ነው፡፡ ሰውነት ዋሽቶ ከሆነ የግምገማውን ፊልም መመልከት ይቻላል፡፡ በዕለቱ የተገኙት የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አንበሳው እንየው ሳይቀር አስረግጠው ሲናገሩ የተደመጠው፣ ፌዴሬሽኑ በተደበላለቀ አሠራር ውስጥ እንደሚገኝ፣ በዚህ ሁኔታ ደግሞ ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት የሚፈልጉት የእግር ኳስ ልማት እንደማይመጣ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሰውነት በሠራው ቡድን ሕዝብና መንግሥት አፍረዋል፣ ስለዚህ ይኼ ሰውዬ መኖር የለበትም ብሎ የደመደመ የለም፡፡ ይልቁንም በተጀመረው መስመር ለመቀጠል በመተጋገዝ መሥራት ቢቻል ወደተሻለ ደረጃ መሸጋገር እንደሚቻል ነው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment