Wednesday, July 17, 2013

ኢሕአዴግ በመንግሥትና በፓርቲው መካከል ጥብቅ የሆነ ትስስርን የሚፈጥር የአደረጃጀት ለውጥ ሊያደርግ ነው

-    በመንግሥትና በፓርቲው መካከል ጥብቅ ትስስር ለመፍጠር ታቅዷል
-    ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባሩ ዋና ጸሐፊና የመንግሥት ምክር ቤት መሪ ይሆናሉ

ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አዲስና ልዩ የተባለ የአደረጃጀት ለውጥ ለማድረግ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተሰማ፡፡
የአዲሱ አደረጃጀት ዓላማ ጥብቅ የሆነ ትስስርን በመንግሥትና በፓርቲው መካከል መፍጠር እንደሆነ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የተደረገው የሥልጣን ሽግሽግና ሹመት እንዲሁም ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዘርፍ ተከፍሎ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ እንዲመራ መደረጉም፣ የዚሁ አዲሱ የፓርቲ አደረጃጀት አካል መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡



በፓርቲው ልዩ አደረጃጀት ከሚፈጥሩ አካላት መካከል ብሔራዊ የመንግሥት ምክር ቤት በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመረጡ ሚኒስትሮችና የክልል ፕሬዚዳንቶችን በአባልነት የሚያካትት ነው፡፡

ብሔራዊ የመንግሥት ምክር ቤቱ ቋሚ አባል የሚሆኑት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሁለት የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመሩት ተሿሚዎች ናቸው፡፡ የተቀሩት የምክር ቤቱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመረጡ ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎችና የክልል ፕሬዚዳንቶች መሆናቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የመንግሥት ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢሕአዴግ ዋና ጸሐፊ እንደሚሆኑ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

የዚህ ምክር ቤት ዋነኛ ሚና የመንግሥትን የዕለት ተዕለት የሥራ አፈጻጸም መከታተልና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ማገዝ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ የፖሊሲ ጉዳዮች እንደማይመለከተው ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኢሕአዴግ ይልቅ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በየክልሎቻቸው የበለጠ ጥንካሬና መዋቅር አላቸው፡፡ በአዲሱ የኢሕአዴግ አደረጃጀት መሠረት ግን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በእኩል የሚወከሉበት የኢሕአዴግ መዋቅር በክልሎችና በዋና ዋና ከተሞች እንደሚደራጅ ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡

የመንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት የዕለት ተዕለት የመንግሥት ክንዋኔን የመከታተል ኃላፊነት የሚሰጠው ቢሆንም፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትን የመከታተልና በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ተግባር እንደሚሆን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ የመንግሥት ምክር ቤት ውስጥ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚደራጁ ሲሆን፣ ተግባራቸውም እንደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም መከታተልና ለምክር ቤቱ ሪፖርት ማቅረብ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በተደረገው ሽግሽግ መሠረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከትምህርት ሚኒስትርነታቸው የተነሱት፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን ከኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት ተነስተው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የተደረጉት በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢሕአዴግ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሲሠሩ የቆዩት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው በትምህርት ምክንያት ኃላፊነታቸውን አስረክበዋል፡፡

አቶ ሴኩቱሬ ከትግል ወቅት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዚህ የግንኙነት ሥራ ላይ ሲሠሩ የቆዩ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የፓርቲ ኃላፊነታቸውን በማስረከብ ወደ ደቡብ ኮሪያ ለትምህርት ይሄዳሉ፡፡

በእሳቸው ምትክ አቶ መሐመድ ሰጠኝ የተባሉ የፓርቲው አባል ለጊዜው መተካታቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት ላይ የተጠየቁት አቶ ሴኩቱሬ፣ ‹‹ከሥራዬ በመልቀቄ ስለጉዳዩ ለመናገር አልችልም፤›› ብለዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment