“የማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” አባላት፤ ከቅዱሳን
አባቶች የተላክነውን የቅዱስ ኤልያስን መልዕክት ለአዲሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ፓትሪያሪክ
አቡነ ማቲያስ እንዳናደርስ ተከለከልን አሉ፡፡ አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን የተካተተችበት መልዕክት አድራሽ ቡድን፤
ባለፈው ማክሰኞ ረፋዱ ላይ መልዕክታቸውን ጋዜጠኞች ባሉበት ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ፓትሪያሪኩ ጽ/ቤት በር ላይ
ተገኝተው የነበረ ቢሆንም የጥበቃ አባላት “ለማነጋገር ፍቃድ የላችሁም” ብለው መልሰዋቸዋል፡፡ ከማህበሩ አባላት
መካከል አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን እና መ/ር ወልደመስቀል ፍቅረማርያም ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ለሁለት ጊዜያት
ያህል 4 ኪሎ በሚገኘው መንበረ ፓትሪያሪክ ጽ/ቤት በመሄድ ከአባቶች የተላኩትን መልዕክት ለማድረስ ቢሞክሩም
ከጽ/ቤቱ የጥበቃ ሃላፊዎች ማለፍ አልቻሉም።
“በመጀመሪያው ቀን ከማህበረ ስላሴ መልዕክት ይዘን መምጣታችንን
ለጥበቃዎች በመንገር ወደ ውስጥ እንድንገባ ከተፈቀደልን በኋላ ሌሎች በግቢ ውስጥ የነበሩ ጥበቃዎች በድጋሚ
አስቁመውን ከስላሴ ካቴድራል ማኅበር የመጣችሁ መስሎን ነው እንጂ እናንተ መግባት አትችሉም በማለት ፓትሪያሪኩን
እንዳናገኝ ተደርገናል” የሚሉት መ/ር ወልደመስቀል፤ በተለይ አንዲት ሴት የጥበቃ አባል ከአግባብ ውጭ ጀማነሽን
እየገፈታተረች እንድትወጣ ማድረጓን ገልፀዋል፡፡ በሚዲያ ሳይቀር ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ማንም ሰው ያለከልካይ በአካል
መጥቶ ሊያነጋግረኝ ይችላል ያሉትን መነሻ አድርገን በመጀመሪያ ቀን ያለቀጠሮ የሄድን ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ቀጠሮ
ለማስያዝ ብንፈልግም የሚያስተናግደን አካል በማጣታችን ለመመለስ ተገደናል የሚሉት መ/ር ወልደመስቀል፤ ጥበቃዎቹ
የሄድንበትን ጉዳይ ጠይቀውን ከተረዱ በኋላ ፈጽሞ መግባት አትችሉም፤ ቀጠሮ ማስያዝ ከፈለጋችሁ አንድ እማሆይ አሉ፤
እሣቸውን አነጋግሩ ተባልን፤ የተባሉት ግለሰብ ግን ፍቃድ ወጥተዋል የሚል ምላሽ አገኘን ብለዋል፡፡ “አሁንም
ለሶስተኛ ጊዜ ስንሄድ ጥበቃዎቹ ፈጽሞ መግባት አትችሉም፡፡ አካባቢውን ለቃችሁ ሂዱ አሉን” ብለዋል - የማህበሩ
አባላት፡፡
ባለፈው ማክሰኞ 10 የሚደርሱ ሴቶችና ወንዶች የማህበሩ መገለጫ
የሆነውን ነጭ ባለቀስተ ደመና ጥለት ልብስ ለብሰው ፓትሪያርኩ ጽ/ቤት በሩ ላይ ቆመው ነበር፡፡ የነብዩ ኤልያስ
መልዕክት ምንድነው ብለን የጠየቅናት አርቲስት ጀማነሽ ሠለሞን “መልዕክቱ ለፓትሪያሪኩ ስለሆነ እሳቸው ከሰሙ በኋላ
ለህዝብ እንድታደርሱ ይነገራችኋል” ብላለች፡፡ የመንበረ ፓትሪያሪክ ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ አበራ ከአዲስ
አድማስ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ተጠይቀው “እስካሁን ጥያቄ ያቀረበልን የለም፤ ቤተክርስቲያኒቷ የራሷ የቅሬታ አቀራረብ
ሥርዓት አላት፡፡ ለቅሬታም ሆነ ለቡራኬ የሚመጡትን በቀጠሮ እናስተናግዳለን፡፡ እስከ ሀምሌ 21 ቅዱስ ፓትሪያሪኩን
በስልክ ለማነጋገር የተያዙ ቀጠሮዎች አሉ” ብለዋል፡፡ ከነብዩ ኤልያስ መልዕክት አለን ያሉት ግለሰቦች
“ኦርቶዶክስ” የሚለው ስያሜ “ለተንኮል” የገባ ስለሆነ የቤተክርስቲያኒቱ ስያሜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተክርስቲያን መባሉ ቀርቶ “የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን” መባል አለበት በሚል አላማ እንደሚንቀሳቀሱ
ይታወቃል፡፡
http://www.addisadmassnews.com
No comments:
Post a Comment