Wednesday, April 10, 2013

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ


ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሽ ዞን ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉት በበታች አመራሮች ግብታዊ ዕርምጃ በመሆኑ፣ ወደነበሩበት እንዲመለሱ የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኪራይ ሰብሳቢ ያሉዋቸው የበታች አመራሮች በፈጠሩት ችግር የተፈናቀሉ 1,346 አባወራዎች ወደ ስፍራው እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የተንጣለለ መሬትና የአምስት ብሔረሰቦች ክልል የሆነው ቤኒሻንጉል ክልል፣ በተለይ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልል የመጡ በርካታ ሰፋሪዎች ይኖሩበታል፡፡ ከእነዚህ ክልሎች ከመጡ ዜጎች መካከል የእኩል እያረሱ የሚኖሩም በርካቶች ናቸው፡፡ ከዛሬ 28 ዓመት በፊት በክልሉ ውስጥ መኖር የጀመሩ ዜጎችም ተፈናቅለዋል፡፡ እነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ያለመጠለያ ከመቅረታቸውም በላይ ለልመና መዳረጋቸው ሲነገር፣ ዘመድ ያላቸው በየዘመዶቻቸው መጠለላቸው ታውቋል፡፡ በዚህ የማፈናቀል ዘመቻ ለበርካታ ዓመታት የኖሩና መታወቂያ ያላቸው ዜጎች መፈናቀላቸውን ከተፈናቃዮች ለመረዳት ተችሏል፡፡


የክልሉ መንግሥት ባወጣው የመሬት ፖሊሲ መሠረት ሕገወጥ ሰፋሪዎችን በአግባቡ ለማስፈር ዕቅድ የያዘ ቢሆንም፣ ይህ ዕቅዱ ባልተጠበቀ ሁኔታ መመርያ ሳይሰጥበት በበታች የወረዳና የቀበሌ ካድሬዎች ያልተገባ ተግባር የተፈጸመ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የአመራሮቹና የካድሬዎቹ ያልተገባ ውሳኔ 1,346 አባወራዎችን ጨምሮ 3,240 ቤተሰቦቻቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉንም አምነዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ግን ብዛታችን ከ5,000 ይበልጣል ይላሉ፡፡

ጉዳዩ ያሳሰበው የአማራ ክልል መንግሥት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥት ጋር ውይይት ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በውይይቱ ወቅት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተፈጠረው ስህተት ማዘኑን መግለጹን አቶ አህመድም ገልጸዋል፡፡ ዜጎችን በማፈናቀል ስህተት በፈጠሩ አመራሮች ላይ ግምገማ ተካሂዶ ዕርምጃ እንደሚወሰድና ሕገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለማስቀረት የተቀናጀና ዘላቂነት ያለው ሥራ እንደሚሠራ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

አቶ አህመድ በክልላቸው በርካታ የአማራ ተወላጆች እንደሚኖሩና ሥልጣን ይዘው የሚገኙ በተለያዩ የአመራር እርከኖች ላይ ያሉ መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ ክልሉ ዜጎችን የማፈናቀል ሐሳብ እንደሌለውና የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት ከውድመት ለመከላከል የግድ ሕገወጥ ሠፈራ አደብ መግዛት እንዳለበት ግን አስታውቀዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ክልሉ ባወጣው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ መሠረት ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀው፣ በሰሞኑ ሕገወጥ ዘመቻ የተፈናቀሉ ዜጎች ግን ተመልሰው ሰላማዊ ሕይወታቸውን መምራት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የሰማያዊ ፓርቲ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ከሌሎችም ክልሎች የአማራ ብሔራ ተወላጆች መፈናቀላቸውን አስመልክቶ ባስተላለፉት የተቃውሞ መግለጫ፣ እስከ አሥር ዓመታትና ከዚያም በላይ ከኖሩበት ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች፣ በአማራ ክልል በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች መሆናቸው እጅግ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ መንግሥት ሊያስብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሁለቱም ፓርቲዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከአንድ ዓመት በፊት ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከጉራፈርዳ ወረዳ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መፈናቀላቸውን፣ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ከጅጅጋ ከተማ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከኖሩበትና ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው መፈናቀላቸውን ያስታወሱት ፓርቲዎቹ፣ አሁን መታሰብ ያለበት ነገሮች ወዴት እያመሩ መሆኑንና በቀጣይ ሊፈጠር የሚችለውን ሁኔታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዜጎች የሚፈናቀሉበት ምክንያት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ወይም ብሔርተኝነት፣ የሚፈናቀሉበትም መንገድ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ  ደረጃ የተቀበለቻቸውንና ስምምነት ያደረገችባቸውን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ያላከበረ መሆኑን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 14 ስለሰብዓዊ መብቶች የሰፈረውን ድንጋጌና በአንቀጽ 25 የእኩልነት መብትን አስመልክቶ የተቀመጠውን መብት የሚፃረር ድርጊት እየተፈጸመ መሆኑን የገለጹት ፓርቲዎቹ፣ ዜጎች በአስገዳጅ ሁኔታ የተፈናቀሉት በአንድ ሕገ መንግሥትና ሉዓላዊነት አገር ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑን፣ መፈናቀላቸውንና ስደታቸውን ተከትሎ እየተከሰተባቸው ያለው ማዋከብና ድብደባ አሳሳቢና አነጋጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ፣ በሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆችና በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌና በሌሎችም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ያስከተለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ማኅበራዊ ቀውስ፣ በየክልሉ በሚኖሩ ቀሪዎቹ ዜጎች ላይ በሰላም ሠርተው የመኖር ፍላጎትና ሀብት ባፈሩበት ቀዬ የመኖር ጥያቄ ላይ ሥጋት እየፈጠረ መሆኑን መንግሥት ልብ ሊለውና ሊያስብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን መፈናቀል በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት እያካሄደ ያለውን ኢሰብዓዊና ሕገወጥ ተግባር እንዲያቆምና እንዲታቀብ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለተፈናቃዮቹ ዜጎች ጊዜያዊ መጠለያ፣ አልባሳትና ምግብ እንዲያገኙ እንዲያደርግ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ማፈናቀል ሕገ መንግሥቱን የጣሰና ኢትዮጵያን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ፣ ድርጊቱን የፈጸሙ ክልሎችም ሆኑ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment