Sunday, February 10, 2013

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዮናስ አድማሱ አረፉ

      ሐኪም ማሞም አርፈዋል

በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ሁነኛ ስፍራ ያላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር  የነበሩት ዶክተር ዮናስ አድማሱ ባለፈው ዓርብ በ69 ዓመታቸው ድንገት አረፉ፡፡
በ1936 ዓ.ም የተወለዱት ዶክተር ዮናስ ከቄስ ተማሪ ቤት በኋላ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲም (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት በ1959 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማዕርግ ካገኙ በኋላ፣ ዩኒቨርሲቲውን በአስተማሪነት አገልግለዋል፡፡ ከአሜሪካ ካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ  እንግሊዝኛ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ በሚል ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተው በመመለስ ዩኒቨርሲቲውን ያገለገሉት ዶክተር ዮናስ፣ በ1970 ዓ.ም. በስደት ወደ አሜሪካ በማቅናት  በአፍሪካ ጥናት ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ለማስተርስ ዲግሪያቸው ያዘጋጁት የመመረቂያ ድርሳን ‹‹Narrating Ethiopia- A Panorama of the National Imaginary›› የሚል ሲሆን፣ በዚያው ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ደግሞ በአንፃራዊ ሥነ ጽሑፍ (Comparative Literature) ነው፡፡

በአዲስ አበባና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ ደረጃ ያስተማሩት ዶክተር ዮናስ በጠሊቅ ጥናትና ምርምሮቻቸው ታዋቂ የነበሩና ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ  ለየት ያለ  የሐቲት (Discourse) መንገድ በማራመድ ይታወቃሉ፡፡ ከሠሯቸው ጥናቶች ሌላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያነት የሚያገለግለውን ‹‹አማርኛ በኮሌጅ ደረጃ›› ከሌሎች ምሁራን ጋር በመሆን ያዘጋጁት ይጠቀሳል፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ግጥሞቻቸው የኮሌጅ ቀን ግጥሞችን ጨምሮ የሚታወቁት ዶክተር ዮናስ  በአሜሪካ በ1980 ዓ.ም.  ‹‹ጉራማይሌ›› የተሰኘ የአማርኛ ግጥሞች መድበልም አሳትመዋል፡፡ ቀደም ሲል የወንድማቸውን የዮሐንስ አድማሱ ‹‹እስኪ ተጠየቁ›› የተሰኘውን የግጥም መድበል አሰናድተው ያሳተሙ ሲሆን፣ የባለቅኔና ጸሐፌ ተውኔት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የሕይወት ታሪክና ሥራ የሚያወሳውን የወንድማቸውን ሌላኛውን መጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን፣ ከ10 ቀናት በኋላ  ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡

ከአባታቸው አቶ አድማሱ ኃይለ ማርያምና ከእናታቸው ወይዘሮ ጌጤነሽ ቸኮል ኅዳር 6 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ዶክተር ዮናስ ሥርዓተ ቀብር እሑድ የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

በሌላ ዜናም በአዲስ አበባ በባህል ሕክምና ታዋቂ የነበሩት ሐኪም ማሞ ኃይሌ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ በ1910 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ቡልጋ የተወለዱት ሐኪም ማሞ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ በአርበኝነት ማሳለፋቸው ከዜና ሕይወታቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የሐኪም ማሞ ሥርዓተ ቀብር እሑድ የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment