Sunday, October 28, 2012

ሁለት እስረኞች ከአጃቢዎች ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ ተገደሉ

-    ሁለት እስረኞችና አንድ ፖሊስ ቆስለው ተርፈዋል
-    አንድ እስረኛ መሣሪያ ነጥቆ መሰወሩ ተገልጿል

በታምሩ ጽጌ ከአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ለመከላከያ ምስክርነት ኮልፌ በሚገኘው የፌዴራል ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩ እስረኞች፣ ከአጃቢ ፖሊሶች ላይ መሣርያ ነጥቀው ሊያመልጡ ባደረጉት ሙከራ፣ ሁለት እስረኞች መገደላቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ሁለት እስረኞችና አንድ ፖሊስ ቆስለው ሲተርፉ፣ አንድ እስረኛ ደግሞ መሣርያ ነጥቆ መሰወሩን ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡

የመከላከያ ምስክር ሆነው ፍርድ ቤት ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የቀረቡት እስረኞች፣ ሌላ እስረኛ በተከሰሰበት ወንጀል የመከላከያ ምስክር አድርጐ ስለቆጠራቸውና ፍርድ ቤቱም እንዲቀርቡ በማዘዙ መሆኑን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

እስረኞቹ በሰው መግደል ወንጀል፣ በከባድ ማታለልና በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸው ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የገለጹት ምንጮቹ፣ ወደማረሚያ ቤት ይመለሱበት የነበረ ተሽከርካሪ ጠባብ መሆኑን በመገንዘብ፣ ከመጀመሪያውም ለማምለጥ ተዘጋጅተው ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

እስረኞቹን የጫነው ተሽከርካሪ የቀድሞ ሦስት ቁጥር ማዞሪያ ቶታል አካባቢ ሲደርስ፣ ስምንት እስረኞችን መጫኑንና መጣበቡን የተረዱት እስረኞቹ በፖሊሶቹ ላይ ሚጥሚጣ በመበተን መሣርያ ነጥቀው ለማምለጥ ባደረጉት ግብግብ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ፣ ከእስረኞቹ በኩል ሁለቱ መገደላቸውንና ሁለቱ ደግሞ ቆስለው መያዛቸውን የገለጹት ምንጮቹ፣ መሣርያ ከቀሙ እስረኞች በተተኮሰ ጥይት አንድ ፖሊስ ከባድ ጉዳት ደርሶበት በሕክምና ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ተደራጅተውና ተዘጋጅተው በፖሊሶቹ ላይ ጉዳት በማድረስ መሣርያ ነጥቀው ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ ሙሉ በሙሉ ባይሳካላቸውም፣ አንድ እስረኛ ግን መሣርያ እንደያዘ መሰወሩን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ ስለተፈጠረው የእስረኞችና የፖሊሶች ግብግብ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ የቀረበለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደልና ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን፣ የተደራጁ እስረኞች በፖሊሶች ላይ ጥቃት አድርሰው ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን ገልጾ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ገና በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment