Sunday, January 26, 2014

ስዊስ ክሬዲት ለባቡር ፕሮጀክት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሊሰጥ ነው

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከስዊስ ክሬዲት ጋር ሲያካሂድ የቆየው የ1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ድርድር በመጠናቀቁ፣ የፊታችን ረቡዕ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡

ሰሞኑን ዘጠኝ አባላት ያሉት የስዊስ ክሬዲት ልዑካን ቡድን አባላት ለፕሮጀክቱ በሚሰጠው ብድር የወለድ ምጣኔና ብድሩ እንዴት እንደሚከፈል ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር የመጨረሻውን ውይይት አካሂደዋል፡፡

የስዊስ ክሬዲት ዳይሬክተሮች ቦርድ ቀደም ብሎ ይህንን ብድር ያፀደቀ በመሆኑ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር የስዊስ ክሬዲትን ማኔጅመንት ከሚወክለው የልዑካን ቡድን ጋር ስምምነቱን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ብድሩ የሚውለው ከመቐለ በወልድያና በሰመራ በኩል ጂቡቲ ታጁራ ወደብ ድረስ የባቡር መስመር አካል ለሆነው ከአዋሽ ወልዲያ (ሃራ ገበያ) ድረስ ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ፕሮጀክት ነው፡፡


የቱርክ ኩባንያ ያፒ ማርከንዚ 389 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የአዋሽ ወልድያ የባቡር መስመር ለመገንባት ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር ውል ገብቷል፡፡

የቱርኩ ኩባንያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የገባው ውል 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጣ ሲሆን፣ ስዊስ ክሬዲት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ያቀርባል፡፡ ቀሪውን 300 ሚሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፍን ታውቋል፡፡

ስዊስ ክሬዲት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄድ ፕሮጀክት ፋይናንስ ለማድረግ ሲዘጋጅ ይህ የመጀመርያው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የአውሮፓና የአሜሪካ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ ፕሮጀክትን ለማካሄድ ከተስማሙ ፋይናንስ እንደሚያደርግ ማስታወቁን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የቱርኩ ኩባንያ የሚገነባው የባቡር መስመር አካል የሆነውን የመቐለ ወልድያ ፕሮጀክት የቻይና ኩባንያ ሲሲሲሲ ለግንባታው ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር ውል መግባቱ ይታወሳል፡፡

ይህን ፕሮጀክት ፋይናንስ የሚደረገው በቻይናው የፋይናንስ ተቋም ኤግዝም ባንክ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ርዝመቱ 260 ኪሎ ሜትር ሲሆን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል፡፡ በአጠቃላይ ከመቐለ እስከ ታጁራ ወደብ ድረስ የሚገነባው የባቡር መስመር 675 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡ ባለአንድ መስመር ሆኖ የሚገነባው ይህ የባቡር መስመር የሰሜኑን የአገሪቱ ክፍል ከመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል ጋር የማገናኘት ዕቅድ ሲኖረው፣ መስመሩ በቀጣይነት ከሰሜን ሱዳን ጋር ይገናኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment