Wednesday, October 10, 2012

የኢሕአዴግ ታጋዮች ጡረታ ትግሉን ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ሊሰላ ነው


የቀድሞውን ወታደራዊ አገዛዝ የመገርሰስ ትግል ውስጥ የተሳተፉና በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች ጡረታ (ማኅበራዊ ዋስትና) ትግሉን ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ እንዲሰላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ አሳሰበ፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለመንግሥት ተቋማት የተሰራጨው ደብዳቤ ከሰኔ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነና ይህም ማለት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤውን ያሰራጨው በሕግ ላይ ተመሥርቶ ይሁን አይሁን በእርግጠኝነት ለመናገር እንደማይችሉ የሪፖርተር ምንጮች የገለጹ ቢሆንም፣ ምናልባት ለሕዝብ ይፋ ያልሆነ መመርያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ሊሆን እንደሚችልና ደብዳቤውም በዚህ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል፡፡ይህንን መረጃ በመንተራስ ሪፖርተር አንዳንድ በመንግሥት ሥራ ላይ የተሰማሩ የቀድሞ ታጋዮችን ለማነጋገር የሞከረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በአባልነት እያገለገሉ ያሉ ይገኙበታል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እነዚሁ የምክር ቤቱ አባላት የመረጃውን ትክክለኝነት ያረጋገጡ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ማንነታቸውን የሚገልጽ፣ ትግሉን የተቀላቀሉበትን ወቅትና በአሁኑ ጊዜ የሚያገለግሉበትን የመንግሥት ተቋምና ሌሎች ጉዳዮችን በተዘጋጀ ቅጽ ላይ መሙላታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ቅጽ ከሞሉ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ከሰሞኑ በድጋሚ ማስታወቂያ እንዳወጣ፣ ማስታወቂያውም የተሞላውን ቅጽ ተንተርሶ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ምላሽ እንዲሰጥበት የላከው ደብዳቤ በመኖሩ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥሪ የሚያቀርብ ነው ብለዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 የጡረታ መብት ሊኖራቸው የሚችሉ ሠራተኞችን ዓይነት የሚዘረዝር ሲሆን፣ በማንኛውም የሕዝብና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በቋሚነት የተቀጠሩ እንዲሁም የመንግሥት ሹመኞችን፣ የሕዝብ ተወካዮችን፣ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላትን የሚያካትት መሆኑን ይገልጻል፡፡

የዕርጅና ጡረታ ዕድሜ ጣሪያ 60 ዓመታትና ቢያንስ የ10 ዓመታት አገልግሎትን፣ የቅድመ ጡረታ ዕድሜ ደግሞ 55 ዓመታትና ቢያንስ 25 ዓመታት አገልግሎትን፣ እንዲሁም በውትድርና ለሚያገለግሉ 45 ዓመታት ዕድሜና 25 ዓመታት አገልግሎትን፣ ነገር ግን የአገልግሎት ጊዜው እንደ ማዕረግ ደረጃቸው ቢያጥርም የአገልግሎት ዘመናቸው ከ10 ዓመታት እንደማያንስ አዋጁ ይገልጻል፡፡

አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በጡረታ በሚገለልበት ወቅት 30 በመቶ የሚሆነውን የመጨረሻ ሦስት ዓመታት የወር ደመወዝ እንደሚያገኝ ያትታል፡፡ አነስተኛ የጡረታ ደመወዝም ከ160 ብር እንደማያንስ ይገልጻል፡፡ አዋጁ የቀድሞ ታጋዮችን አስመልክቶ የደነገገው እንደሌለ ለመረዳት ቢቻልም፣ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ግን አዋጁን ተንተርሶ መመርያ የማውጣት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይሁን እንጂ ኤጀንሲው ይህንን የተመለከተ መመርያ ወይም ደንብ አውጥቶ እንደሆነ ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com