Tuesday, April 8, 2014

መከላከያ ሚኒስቴር የህዳሴውን ግድብ ከማንኛውም ጥቃት የመከላከል አቅም እንዳለው አስታወቀ



-ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር ጠባቂ ጦር ሊመሠርቱ ነው

የመከላከያ ሠራዊቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብንና ሌሎች የአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ከማንኛውም ጥቃት የመከላከል ጠንካራ አቅምና ዝግጁነት እንዳለው፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለፓርላማ አስታወቁ፡፡

አቶ ሲራጅ የመከላከያ ሚኒስቴርን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ባለፈው ሐሙስ ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት፣ ሠራዊቱ የህዳሴውን ግድብ የመጠበቅ አቅሙና ዝግጅቱ ምን ያህል እንደሆነ እንዲያብራሩ ተጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ መስጠት የጀመሩት፣ በህዳሴው ግድብ ላይ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶች በሁለት መንገድ ብቻ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመተንተን ነው፡፡

ከተለዩት የጥቃት መንገዶች አንደኛው ቀጥታ በግድቡ ላይ የሚከፈት ቀጥታ ወታደራዊ ጥቃት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች በመጠቀም የሚከፈት ጥቃት ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ በህዳሴው ግድብ ላይ በቀጥታ የሚፈጸም ጥቃት ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ አስረድተዋል፡፡


‹‹አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ በቀጥታ የሚሰነዘር ጥቃት ይኖራል ብዬ አላምንም፣ ይከብዳል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዚህ እምነታቸው የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል፡፡

‹‹አንደኛ ከዓለም ሕዝብ ተደብቀን አይደለም የህዳሴው ግድብን እየገነባን ያለነው፡፡ የሚመለከታቸው የተፋሰሱ አገሮችን ባሳተፈና ግንባታው በማንም ላይ ጉዳት እንደማያደርስ በጥናት በተረጋገጠ መልኩ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ሁሉ አልፎ በድፍረት ቀጥታ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል ምክንያት ይኖራል ብሎ ለመገመት ይከብዳል፤›› ብለዋል፡፡

የግብፅ ባለሥልጣናት ጥቃት እንደሚከፍቱ ቢናገሩም ይህ ግን ከሚዲያ ፍጆታ ያልፋል ብሎ መገመት እንደማይቻል ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግድቡ ላይ ቀጥታ ጥቃት ለመፈጸም ከባድ ነው በማለት የሰጡት ምክንያት፣ በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ያሉ የተለያዩ አገሮች ዜጐች መኖራቸውን ነው፡፡

‹‹በዚህ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ያሉ አገሮች እነማን ናቸው ብሎ መመልከቱም ጥሩ ነው፡፡ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ቻይናና የመሳሰሉት አገሮች ዜጐች በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ እየሳተፉ ነው፤›› በማለት፣ ጥቃት ለመፈጸም እነዚህን አገሮች ማሰብ እንደሚያስገድድ በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

የተጠቀሱት ምክንያቶች በቀጥታ ጥቃት ለመፈጸም የማያስደፍሩ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እነዚህ ምክንያቶች በቂ ናቸው ብሎ በመገመት ሠራዊቱን የመገንባት ሥራውን ትቷል ማለት እንዳልሆነ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡


‹‹አገሪቱ ባላት አቅምና ሠራዊቱ ካለበት ተልዕኮ አንፃር ማድረግ ያለበትን ዝግጅት ያለማቋረጥ እያደረገ ነው ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ይህንን የምናደርገው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገባል ተብሎ ስለሚሰጋ ሳይሆን ዘወትር ማድረግ የሚገባን ሥራ ስለሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በህዳሴው ግድብ ላይ ሊሰነዘሩ ከሚችሉ ጥቃቶች ሌላኛው አማራጭ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎችን መጠቀም መሆኑን፣ ይህ ዓይነቱ ሥምሪት ለኢትዮጵያ አዲስ አለመሆኑንና ላለፉት 40 ዓመታት ሲሞከር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህንን ለመከላከል ከግንባር እስከ ማዕከል ድረስ የደኅንነት ተቋማት በከፍተኛ ቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚህ በላይ ደግሞ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከኤርትራ በስተቀር ከሁሉም ጐረቤቶቻችን ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ፈርመን ለጋራ ድንበሮቻችን የጋራ ዕቅድ አውጥተን እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተለይ ከወራት በፊት ከሱዳን ጋር የተፈረመው ስምምነት ሁለቱ አገሮች የጋራ ድንበር ጦር ለመመሥረት የሚያስችላቸው ነው ብለው፣ ይህ የጋራ ድንበር ጦር በሁለቱም አገሮች ድንበር ውስጥ የተወሰነ ዘልቆ ገብቶ ያሉትን ፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎች መቆጣጠር የሚችል እንደሆነ ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ፀረ ሰላም ኃይሎች የሁለቱንም አገሮች ድንበር ጥሰው ወደ መሀል ከመንቀሳቀሳቸው በፊት በዚህ የጋራ ድንበር ጦር ቁጥጥር ሥር ይወድቃሉ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የአገር ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመጠቀም የሚደረግ ጥቃትን ለማክሸፍ የመከላከያ ሠራዊቱ ከመላ የአገሪቱ የደኅንነት ተቋማት ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ይህንን አጠቃላይ ደምረን ስንመዝን የህዳሴው ግድብንም ሆነ አሁን ያሉንን ሜጋ ፕሮጀክቶች ከማንኛውም አደጋ የመጠበቅ ዝግጁነታችን በተጠናከረ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን ማየት ይቻላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment