-ተጠርጣሪው ገዳይ በቁጥጥር ሥር ውሏል
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አቦ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሦስት ዓመታት በፊት በተነሳ የመኖሪያ አዋሳኝ ድንበር ክርክር ምክንያት የሦስት ሕፃናት እናትና አባት፣ የመከላከያ ሠራዊት አባል ነበር በተባለ ተጠርጣሪ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡
የከባድ ተሽከርካሪ ሾፌር መሆናቸው የተገለጸው አቶ ዳንኤል ነጋሽና የቤት እመቤት ናቸው የተባሉት ወ/ሮ ምስለ ማሞ የመቶ እልቅና ማዕረግ በነበረውና እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ የመከላከያ ሠራዊት አባል እንደነበረ በተገለጸው ግለሰብ በጥይት ተደብድበው ሊገደሉ የቻሉት፣ በግልና በቀበሌ ይዞታነት ለሁለት በተከፈለ ከመኖሪያ ግቢ ጋር በተያያዘ ተፈጥሮ በከረመ የወሰን ውዝግብ ምክንያት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተጠርጣሪ ገዳይ ከሟቾች አጥር ጋር የተያያዘ የቀበሌ ቤት ተከራይቶ ሲኖር፣ መውጫና መግቢያው በሟቾች ግቢ ውስጥ እንዲሆን ለክፍለ ከተማው ወረዳ ሦስት በማመልከቱ ይፈቀድለታል፡፡
የወረዳውን ውሳኔ የተቃወሙት ባለይዞታዎች (ሟቾች) ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ተጠርጣሪውንና ወረዳውን ይከሳሉ፡፡ የክስ ሒደቱ ላለፉት በርካታ ወራት የተጓተተ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ወገኖች ማለትም ተጠርጣሪ ገዳይና ሟቾች ምንም ዓይነት ግንባታ ወይም የማፍረስ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ዕግድ ጥሎበት እንደነበርም ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ተጠርጣሪ ገዳይ ከወትሮ ለየት ባለ ሁኔታ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ዕግድ የተጣለበትን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመተላለፍ፣ አጥር ለማጠባበቅ ሲሞክሩ ሟች አቶ ዳንኤል ‹‹ዕግድ የተጣለበት ስለሆነ በሕግ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ አጥር ማጠርም ሆነ ማፍረስ ተከልክሏል፡፡ በሕግ አምላክ አትንካ፤›› በማለት ሲናገሩ መስማታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪው ቤቱ በመግባት ክላሽኒኮቭ ጠመንጃውን ይዞ በመውጣት አቶ ዳንኤልን ከአራት በላይ በሆኑ ጥይቶች ከገደለ በኋላ፣ የተኩስ ድምፅ ሰምተው ወደ ቤት በመግባት ተደብቀው የነበሩትን ወ/ሮ ምስለን በተመሳሳይ ደብድቦ መግደሉን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች የሁለቱን ውዝግብ ቀደም ብለው ያውቁ ስለነበር፣ በራቸውን ዘግተው ከመጠበቅና ከመሸሽ ያለፈ ምንም ዓይነት መከላከልም ሆነ ጩኸት ማሰማት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ የሟቾቹን ሦስት ሕፃናት በመያዝ የአካባቢው ሰዎች ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ሲወጡ፣ በፌደራል ፖሊሶችና የፀጥታ ኃይሎች መከልከላቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ሟቾች ተጠርጣሪው ‹‹አንድ ቀን ይገድለናል›› በማለት ማመልከታቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውም ጦሱ ለእነሱም ሊተርፍ እንደሚችል በማሰብ በቡድን ሆነው ያመለከቱ ቢሆንም፣ የሚመለከተው አካል ዝምታን በመምረጡ ውጤቱ የፈሩት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሟቾች አስከሬን በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ምርመራ ተደርጎለት፣ የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በለቡ ገብርኤል ቤተ ክርሲቲያን የቀብር ሥርዓታቸው ተፈጽሟል፡፡ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት ባልና ሚስት የሦስት ሕፃናት ወላጆች መሆናቸውን፣ ወ/ሮ ምስለ ከአቶ ዳንኤል የማትወለድ አንድ ሴት ልጅ ያላቸው መሆኑንና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዓመት ተማሪ መሆኗን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች መንግሥት በተጠርጣሪው ላይ የተፋጠነ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment